ፈልግ

አዲስ የተወለዱ ጨቅላ ሕፃናትን ከጋዛ ሆስፒታል ወደ ግብፅ ለማዘዋወር ዝግጅት ሲደረግ አዲስ የተወለዱ ጨቅላ ሕፃናትን ከጋዛ ሆስፒታል ወደ ግብፅ ለማዘዋወር ዝግጅት ሲደረግ  (ANSA)

በጋዛ ውስጥ የሚገኙትን ታጋቾች ለማስፈታት ድርድሩ ቀጥሏል ተባለ

በሐማስ የተወሰዱ ታጋቾችን ለማስፈታት ድርድሩ የቀጠለ ሲሆን፥ የዓለም ጤና ድርጅት በጋዛ አልሺፋ ሆስፒታል ውስጥ የሚገኙ ህሙማንን እና የህክምና ባለሙያዎችን ለማስወጣት እየሰራ እንደሆነ ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በሀማስ ታግተው ከነበሩት ከ200 በላይ እስራኤላውያን ታጋቾች መካከል ጥቂቶቹ በቅርቡ ሊፈቱ ይችላሉ የሚል ተስፋ እየጨመረ መጥቷል።

ኳታር በእስራኤል እና በሃማስ መካከል አሸማጋይ ሆና እየሰራች ሲሆን፥ በስምምነቱ ሂደት ላይ 'በጣም ጥቃቅን' ከሚባሉ መሰናክሎች በስተቀር በጥሩ ሁኔታ እየሄደ እንደሚገኝ ገልፃለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የእስራኤል ጦር ሃማስ የጋዛን ትልቁን ሆስፒታል አል ሺፋን እንደ ማዘዣ ማእከልነት ሲጠቀም መቆየቱን የሚያረጋግጡ ሁለት አዳዲስ ቪዲዮዎችን ለቋል።

በሌላ ዜና የዓለም ጤና ድርጅት ቀሪ ህሙማንን እና የህክምና ባለሙያዎችን ከአልሺፋ ሆስፒታል ለማስወጣት እቅዱን እያጠናቀቀ መሆኑን ገልጿል። ሪፖርቶች እንደሚገልፁት እሁድ ዕለት 31 ያለጊዜው የተወለዱ ህጻናት ከሆስፒታሉ ወደ ሌላ ቦታ እንደተወሰዱ እና በደቡባዊ ጋዛ ውስጥ እንክብካቤ እየተደረገላቸው እንደሆነ ተነግሯል።

በሌላ በኩል በሃማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እስራኤል በአንድ ሆስፒታል ላይ ባደረሰችው የአየር ጥቃት በትንሹ 12 ሰዎች መሞታቸውን ገልጿል። እስራኤል በሃማስ ላይ ዘመቻዋን ከጀመረች በኋላ በግዛቱ 13,000 ሰዎች መገደላቸውንም ይኸው ድርጅት ገልጿል።

መስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም. የሃማስ ተዋጊዎች ድንበር ጥሰው 1,200 እስራኤላውያንን ከገደሉ እና ከ200 በላይ ታጋቾችን ከወሰዱ በኋላ እስራኤል በጋዛ ላይ ጥቃት መሰንዘር መጀመሯ ይታወቃል።
 

21 November 2023, 15:10