ፈልግ

በፍልስጤሙ የጋዛ ታጣቂ እና በእስራኤል መካከል የሚደረግ ጦርነት በፍልስጤሙ የጋዛ ታጣቂ እና በእስራኤል መካከል የሚደረግ ጦርነት 

ፕሮ/ር ሙስጠፋ፥ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በጋዛ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ላደረጉት ጥረት ምስጋናን አቀረቡ

መቀመጫቸውን ኢየሩሳሌም ያደረጉት ፕሮፌሰር ሙስጠፋ አቡስዌይ በጋዛ ያለውን የማያቋርጥ የሰዎችን እልቂት በማስመልከት ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለተኩስ አቁም ስምምነት ላደረጉት ጥረት አመስግነው፥ ድምጻቸን የበለጠ መስማት ይኖርብናል ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ የሚያቀርቡትን ግልጽ ጥሪ የበለጠ መስማት አለብን” በማለት መቀመጫቸውን ኢየሩሳሌም ያደረጉት ፕሮፌሰር ሙስጠፋ አቡስዌይ ተናግረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከእስልምና ቅዱስ ሥፍራዎች መካከል አንዱ በሆነው እና ኢየሩሳሌም ውስጥ በሚገኝ አል-አቅሳ መስጊድ የአል-ጋዛሊ ኢማም እና በአል ቁድስ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ፍልስጤማዊ ፕሮፌሰር ሙስጠፋ አቡስዌይ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ በጋዛ ውስጥ ስላለው ሰብዓዊ ቀውስ፣ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በሰላም ግንባታ ላይ ያላትን ሚና እና የእርሳቸው የእስልምና እምነት በእነዚህ አስቸጋሪ ወቅት የሚያበረክተውን ዕርዳታ በማስመልከት ተወያይተዋል።

ጋዛ ውስጥ የሚታይ ያልተገራ እልቂት

መኖሪያቸው ኢየሩሳሌም ውስጥ እንደሆነ የሚናገሩት ፕሮፌሰር ሙስጥፋ አቡስዌይ፥ በአንጻራዊነት ሲታይ የሚኖሩበት አካባቢ  ደህና እንደሆነ ገልጸው፥ ነገር ግን በጋዛ እና በሰሜናዊ ዌስት ባንክ ያለውን ሁኔታ ከሩቅ ሲከታተሉት ሥነ ልቦናዊ ውጥረት፣ ሐዘን እና ብስጭት እንደሚሰማቸው ተናግረዋል።

ከቁጥጥር ውጭ የሆነው ይህ እልቂት በቀጥታ ወደ ዓለም ሁሉ እየተሰራጨ እንደሚገኝ፥ የሕዝቡን መከራ የሚያሳዩ ምስሎች ክስተቱን ካለፉት ጦርነቶች ልዩ እንደሚያደርጉትም አስረድተው፥ በጋዛ በየአስር ደቂቃዎች ልዩነት አንድ ሕጻን እንደሚሞት ተናግረዋል። ይህም ሆኖ ግን በጣም የሚገረመኝ የአንድ ሕጻን ሞት ሳይሆን የአንድ ሕጻን ከሞት መትረፍ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

እንዲህ ያለው የፍልስጤም መከራ በአብዛኛው የምዕራባውያን መንግሥታት ዘንድ ችላ መባሉ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ “የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኖአል፥ ጆሮአቸው ደንቁሯል፣ ዓይናቸውም ተጨፍኗል” ያለውን ያስታውሰኛል ብለዋል።

ፕሮፌሰር ሙስጠፋ አቡስዌይ
ፕሮፌሰር ሙስጠፋ አቡስዌይ

የቤተ ክርስቲያን ሚና

ብዙ የምዕራባውያን መንግሥታት የተኩስ አቁም ጥሪ ለማቅረብ ፈቃደኛ ባይሆኑም፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ለሚያቀርቡት ግልጽ ጥሪ ምስጋናቸውን አቅርበው፥ የቅዱስነታቸው ጥሪ ይበልጥ ልንናዳምጠው የሚገባን ሞራላዊ መልዕክት ነው ብለዋል።

በቤተልሔም ከሚገኝ ካቶሊካዊ ዩኒቨርሲቲ እና በቦስተን ከሚገኝ ካቶሊካዊ ኮሌጅ የተመረቁት ፕሮፌሰር ሙስጠፋ አክለውም፥ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የፍልስጤም ሕዝቦች ማኅበራዊ ሕይወት አካል እና ትስስርም ያላት እንደሆነች አስረድተው፥ የሰው ልጆች በተሰቃዩባቸው በእነዚህ አሥርተ ዓመታት በሙሉ ቤተ ክርስቲያን አብሮአቸው እንደ ነበረች አስታውሰው፥ የምታሰማው የሞራል ድምጿም ከሕዝቡ ድምጽ ጋር አንድ እንደሆነ ተናግረዋል።

በእስራኤል እና ፍልስጤም ግጭት ዙሪያ በተለያዩ የፍልስጤም የአብያተ ክርስቲያናት መሪዎች ተጽፎ የጸደቀውን የካይሮስ ሠነድንም ፕሮፌሰር ሙስጤፋ ጠቅሰዋል።

በችግር ጊዜ የሚገለጽ መንፈሳዊነት

የእስልምና እምነት አስቸጋሪ ጊዜያት ለመጓዝ እንዴት እንዳገዛቸው የተናገሩት ፕሮፌሰር ሙስጤፋ፥ መላ ቤተሰባቸውን በጦርነት አደጋ ያጡ በምዕራቡ ዓለም የሚገኙ ብዙ ሰዎች “አልሀምዱሊላህ” ወይም እግዚአብሔር ይመስገን ማለታቸውን በማስታወስ፥ “ሙስሊሞች ለምንድነው እንደዚህ ዓይነት አደጋ ሲደርስባቸው 'እግዚአብሔር ይመስገን' የሚሉት?” በማለት ጠይቀዋል።

“ሁሉም ነገር በእርሱ እጅ እንዳለ በማወቃችን እግዚአብሔርን እናመሰግነዋለን” ያሉት ፕሮፌሰር ሙስጤፋ፥ነገር ግን ይህን ሁሉ ዓመፅ ለማስቆም ሰዎች በእርግጥ እርምጃ ሊወስዱ እንደሚችሉ እናውቃለን፥ መንፈሳዊ ሃብትም አለን፤ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ያለው ነገር ሁሉ በእውነት በእግዚአብሔር ግዛት ውስጥ እንዳለ እናውቃለን፣ በመጨረሻም የእግዚአብሔር ፈቃድ ያሸንፋል” ብለዋል።

የወደፊት ተስፋ

ወደ ፊት ስለሚደረግ የሰላም ስምምነት ራዕያቸው የተመለሱት ፕሮፌሰር ሙስጠፋ፥ እነዚህ አሳዛኝ ክስተቶች በሙሉ የሰውን ልጅ ወደ ህሊናው እንዲመለስ እንደሚያደርግ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። “ለውጥን ማምጣት የሚችሉ ትክክለኛውን ውሳኔ እንደሚወስኑ እና በትክክለኛው የታሪክ ጎን እንደሚቆሙ ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።

ውሎ አድሮ የሰላም እልባቱ ግጭትን እና ወረራን ለማቆም የሚያግዝ፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ሰኔ 4/1967 ዓ. ም. የተቀመጠውን የድንበሮች ስምምነትን በማካተት፥ “ሁለት መንግሥታት” የሚለው የመፍትሄ ሃሳብ ተግባራዊ ሊሆን ይገባል ሲሉ አሳስበው፥ ሁለቱ ሕዝቦች በጉርብትና እየኖሩ በተቻለ መጠን ቁስሎችን ለመፈወስ ጊዜ መስጠት አለብን" በማለት መቀመጫቸውን ኢየሩሳሌም ያደረጉት ፕሮፌሰር ሙስጠፋ አቡስዌይ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል።

18 November 2023, 16:56