ፈልግ

የእስራኤል ወታደራዊ የቦምብ ድብደባ በሰሜዊ የጋዛ ሰርጥ የእስራኤል ወታደራዊ የቦምብ ድብደባ በሰሜዊ የጋዛ ሰርጥ  (AFP or licensors)

ዩኒሴፍ ጋዛ ውስጥ ለሚገኙት ህጻናት ጥበቃ እንዲደረግ ጠየቀ

የዩኒሴፍ ዋና ዳይሬክተር በእስራኤል ጦር በተከበበችው የጋዛ ሰርጥ ውስጥ ለሚገኙ እና ምንም አስተማማኝ መሄጃ ቦታ ለሌላቸው ህጻናት ጥበቃ እንዲደረግላቸው ጥሪያቸውን ካቀረቡ በኋላ፥ አፋጣኝ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ፣ የታገቱ ህጻናት እንዲፈቱ እንዲሁም ደህንነቱ የተጠበቀ እና ገደብ ያልተደረገበት የሰብአዊ ዕርዳታ እንዲደረግ ጠይቀዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

መስከረም 27 ቀን 2016 ዓ.ም. እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ላይ ጥቃት መውሰድ ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ከ4,600 በላይ ህጻናት እንደተገደሉ እና ወደ 9,000 የሚጠጉት ደግሞ መቁሰላቸው ተነግሯል።

የተባበሩት መንግስታት የህፃናት ፈንድ - ዩኒሴፍ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ካትሪን ራስል ህዳር 5 ቀን 2016 ዓ.ም. በጋዛ ጉብኝት ካደረጉ በኋላ እንደተናገሩት፥ በእስራኤል ጦር በተከበበው የጋዛ ሰርጥ ውስጥ የሚገኙ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ህጻናት በጣም አስከፊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ገልፀዋል።

ወደ ጋዛ በሄዱበት ወቅት ከህጻናቱ፣ ከቤተሰቦቻቸው እና ከዩኒሴፍ ሰራተኞች ጋር ተገናኝተው ያወሩት ሃላፊዋ “በተደጋጋሚ የሚደረገውን የቦምብ ድብደባ፣ ቤተሰብን ማጣት እና መፈናቀልን በጽናት ተቋቁመው እየኖሩ ያሉትን ልጆች” የሚደርስባቸውን መከራ ገልፀዋል።

ከባድ የህግ ጥሰቶች

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በግጭቱ ውስጥ በሁለቱም ወገኖች የሚፈጸመውን ከባድ የመብት ጥሰት፣ ግድያ፣ አካል ማጉደል፣ አፈና፣ ትምህርት ቤቶች እና ሆስፒታሎች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት እና የሰብአዊ አገልግሎትን መከልከልን ያካተቱ ጥሰቶችን እንደሚያወግዝ ተናግረዋል።

ወ/ሮ ራስል በመቀጠል “ብዙ ልጆች ጠፍተዋል” ካሉ በኋላ “ምናልባትም በፈራረሱ ሕንፃዎች እና ቤቶች ውስጥ ተቀብረዋል ተብሎ ይታመናል” ብለዋል።

ብዙ ሆስፒታሎች ሥራ አቁመዋል

ሃላፊዋ በጋዛ ውስጥ ካሉ ሆስፒታሎች በአንዱ፥ የኃይል እና የሕክምና አቅርቦቶች በማለቃቸው ምክንያት ልዩ እንክብካቤ የሚያስፈልጋቸው አዲስ የተወለዱ ጨቅላ ሕፃናት መሞታቸውን ተናግረዋል። ወ/ሮ ራስል እንዳሉት በካሃን ዩንስ ከተማ በሚገኘው በአል ናስር ኒዮናታል ሆስፒታል ውስጥ “ጨቅላ ሕፃናት በማሞቂያ መሳሪያዎች ውስጥ እንደሚገኙ እና ዶክተሮችም ማሽኖቹን ያለ ነዳጅ እንዴት ማቆየት እንደሚችሉ ሲጨነቁ አይቻለው” ብለዋል።

የዩኒሴፍ ጥሪ

የዩኒሴፍ ዳይሬክተሯ በተጨማሪም የሰብአዊ እርዳታ ሰጭ ሰራተኞችን ስጋት በማጉላት እንደተናገሩት የእርዳታ ኤጀንሲዎች በጣም አስፈላጊ የሆኑትን አቅርቦቶች ለማድረስ የተቻላቸውን ሁሉ እያደረጉ እንደሆነ፥ ነገር ግን ወደ ጋዛ የሚያስገቡት ማቋረጫ ድንበሮች አልፎ አልፎ ብቻ ስለሚከፈቱ ሰብአዊ አቅርቦቶችን ለማጓጓዝ እና በጣም እየጨመረ የመጣውን ፍላጎቶች ለማሟላት በቂ እንዳልሆነ ገልፀዋል።

በተጨማሪም “አፋጣኝ ሰብዓዊ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ፣ የታገቱት ሕፃናት በሰላም እንዲለቀቁ እና የሰብአዊ ዕርዳታ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ለተቸገሩት የተሟላ የህይወት አድን አገልግሎቶች እና አቅርቦቶች እንዲያደርሱ ደህንነታቸው የተጠበቀ፣ ቀጣይነት ያለው እና ዕገዳ የሌለበት መተላለፊያ መንገድ እንዲያገኙ” ተማጽነዋል።

ወ/ሮ ራስል በስተመጨረሻም በዓለም አቀፍ የሰብአዊ ህግ መሰረት ህፃናት ጥበቃ እንዲደረግላቸው እና አስፈላጊው ሁሉ ሰብአዊ ድጋፎች እንዲደረግላቸው ለሁሉም ወገኖች ጥሪ በማድረግ አጠናቀዋል።
 

16 November 2023, 14:21