ፈልግ

ጣሊያን ውስጥ በሚገኘው ሆስፒታል ወደ ድንገተኛ ክፍል መግቢያ በር ላይ - የፋይል ፎቶ ጣሊያን ውስጥ በሚገኘው ሆስፒታል ወደ ድንገተኛ ክፍል መግቢያ በር ላይ - የፋይል ፎቶ  (ANSA)

ሮም በሚገኘው ሆስፒታል ድንገተኛ ክፍል ውስጥ የፈነጠቀው የተስፋ ጭላንጭል

በሮም የሚገኘው “ሳን ካሚሎ” ሆስፒታል በሰፊው በተዘረጋው የህሙማን ድንገተኛ ክፍል ውስጥ ያለው የሥራ ልምድ ለደጉ ሳምራዊ ታሪክ ጥሩ ምሳሌ እንደሚሆን እንዲሁም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በተደጋጋሚ እንደ ደጉ ሳምራዊ እንድንሆን ያቀረቡት ጥሪ በግልጽ የሚታይበት ስፍራ ነው።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በቅርቡ የቫቲካን ዜና ጋዜጠኛ ሮም የሚገኘውን ሳን ካሚሎ ሆስፒታል ጎብኝታ ልምዷን እንደሚከተለው አቅርባለች፦
በህመምተኞች በተጨናነቀው የሮም ሆስፒታል ድንገተኛ ክፍል ውስጥ ያሳለፍኳቸው ሶስት ቀናት እጅግ አስፈሪ እና በሚያስገርም ሁኔታ ፈታኝ ተብለው ሊገለጹ ይችላሉ። ነገር ግን ጨለማ በዋጠው፣ የመኖር ዋስትና በጠፋት እና ፍርሃት በነገሰበት ዓለማችን ውስጥ በሰዎች ላይ ያለኝን የተመናመነ ተስፋ ባልተጠበቀ ሁኔታ ያደሱ የህይወት ትምህርቶች ነበሩ።

ታካሚዎች

በድንገተኛ ክፍል ውስጥ ሁሉም ሰው እኩል ነው፥ ሕመም ሁሉም ነገር እንዲያስጠላን ያደርጋል፣ ዝቅም ያደርገናል ብሎም ግርማ ሞገሳችንን ይገፋል። አብዛኛዎቹ ታካሚዎች አረጋውያን ሲሆኑ፥ ግራ መጋባት እና ፍርሃት ውስጥ የገቡ ናቸው። ልክ እንደሌላው ሰው ሁሉ ከሚወዷቸው ሰዎች ተለይተው ስላሉ ከሚሰማቸው ጭንቀት ለመውጣት ከሰዎች ጋር መገናኘትን እና የመጽናኛ ቃላትን መለዋወጥ ይፈልጋሉ። ስለዚህም ሌላ የበለጠ አቅም ያለው ታካሚ ሲመጣ የሞቀ ሰላምታ በመስጠት እና አብሮ በማውራት ለአፍታም ቢሆን የብቸኝነትን ጥላ ያባርራሉ።

ሰራተኞቹ

ዶክተሮች፣ ነርሶች፣ ሰልጣኞች፣ የጽዳት ሠራተኞች፣ ምግብ አብሳዮች፣ ሁሉም ስራውን በትጋት ይሰራል። ትርምሱ እና ግርግሩ የደራሲው 'ዳንቴ ኢንፌርኖ' መጽሃፍ ውስጥ ያሉትን ትዕይንቶችን ያስታውሱናል። ሁሉም ሰው በአንድ ጊዜ እየጮኸ ነው፥ ከህመም እፎይታ ለማግኘት እና ለጥያቄዎቻቸውም ምላሽን ይማጸናል።

ሁሉም ሰው የሆነ ነገር ይፈልጋል፥ ውሃ፣ ምግብ፣ ኦክሲጅን፣ የሚሰራ ስልክ፣ የጠፉ መነጽሮችን ለማግኘት እገዛ ይፈልጋል። እራሳቸውን እንዳይጎዱ ክትትል የሚያስፈልጋቸው ታካሚዎችም አሉ፥ ብዙዎች ይጮኻሉ፣ ጥቂቶች ያለቅሳሉ፣ ሌሎች ይጸልያሉ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ሙሉ በሙሉ የተረሱ ይመስል ተገልለው ለብቻቸው ሆነዋል።

የህፃናት የሽንት ጨርቆች በመተላለፊያዎች ውስጥ እና በክፍሉ መሃል ላይ እንኳን በጥንቃቄ የቀየራሉ። ሴቶች እና ወንዶች፣ ጎልማሶች እና በዕድሜ የገፉ አዛውንቶች፣ ከታጠቡ በኋላ በፎጣ በደንብ ይታበሳሉ፥ ከዛም በአግባቡ እና በጥንቃቄ ቁስሎቻቸው ይጠቀለላል።

የተገኘው ትምህርት

“ምህረት” የሚለው ቃል ለእኔ አዲስ ትርጉም የሰጠኝ እዚያ በድንገተኛ ክፍል ውስጥ ነበር። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እንደ ደጉ ሳምራዊ እንድንሆን ያቀረቡትን ግብዣ በድንገት ተረዳሁ። ይህም አንደ ሰው ለራሱ ሳይሆን ለሌሎች መኖርን፣ ለሰዎች በችግሮቻቸው ጊዜ መድረስን፣ በመንገዳችን ላይ የምናገኛቸውን እና የእኛን እርዳታ የሚፈልጉትን መርዳት የአኗኗራችን ዘይቤ ማድረግ እንዳለብን ተረዳሁ።

ከባንግላዲሽ የመጣ አንድ ወጣት ከክሮንስ ከተባለው የአንጀት በሽታ ፈጽሞ እንደማይድን ዶክተሮች በእንግሊዝኛ እንዲገልጹለት በረዳሁበት ወቅት ግራ ተጋብቶ አይን አይኔን ሲያየኝ የነበረው ልጅ እንዴት እረሳዋለሁ? ወይም የስትሮክ በሽታ እንዳለበት የተነገረውና ሚስቱንና ሴት ልጁን መሰናበት ሳይችል ሊሞት እንደሚችል ያወቀውን ሰው እንባ የማየት ፈታኝ ሁኔታ መቼም አይረሳም። ሰውዬው ስለልጁ ሲያወራ “ሙዚቀኛ ነች” በማለት በኩራት “በሮም ኦፔራ ቫዮሊን ትጫወታለች” ብሏል።

እኔ ራሴ ሁኔታዎቹ ከአቅሜ በላይ ሆነውብኝ አዙሮኝ ልወድቅ ስል በዚያ ቅጽበት ለእሱ ያለሁት ብቸኛው ሰው እኔ እንደመሆኔ እና በወቅቱ የመጨረሻው የተስፋው ገመድ ስለሆንኩ ከመውደቄ በፊት ቶሎ ብሎ እጄን ያዘኝ፥ መላቀቅም ፈታኝ ነበር። አጠገባችን ባለው በሌላኛው አልጋ ላይ አንዲት ሴት ምንም ዝምድና የሌላቸውን የ86 ዓመት አዛውንቷን በትዕግስት በማንኪያ ስትመግብ እና እናት ለልጇ የምታደርገውን እንክብካቤ ሁሉ ስትገልጽ እያየሁ እኔ ብሆን እንደዚህ አደርግ ነበር? ብዬ ራሴን እንድጠይቅ አደረገኝ።

ደጉ ሳምራዊ

በጣም ብዙ ታሪኮች፣ በጣም ብዙ መከራ፣ ነገር ግን በዚያ የድንገተኛ ክፍል ውስጥ፣ ልክ በሌላኛው የዓለም ክፍል እንዳለው፥ እንክብካቤ የሚያደርጉ እና የሚደረግላቸው ሁሉም በጋራ በመስጠት እና በመቀበል የተሳሰሩ ናቸው። ግጭት እና ትርምስ፣ ፍትህ ማጣት እና መለያየት ባለበት ዓለም አሁንም ብዙ ደጋግ ሳምራውያን የፈውስ እጆቻቸውን ይዘረጋሉ፥ እጆቻቸው በምሕረት እና በርኅራኄ የተሞሉ ናቸው። እናም ያ በራሱ በሰው ልጅ ላይ ያለኝን ተስፋ ለማደስ በቂ ነው።
 

20 March 2024, 12:39