ፈልግ

ንጉስ ቻርለስ ሶስተኛ ንጉስ ቻርለስ ሶስተኛ  (ANSA)

ር.ሊ.ጳ. ፍራንቺስኮስ እና ንጉሥ ቻርለስ 3ኛ በሥነ-ምህዳር ዙሪያ 'የጋራ ራዕይ' አላቸው ተባለ

'የንጉስ ቻርልስ ዘላቂ ገበያዎች ትሥሥር' መሪ የሆኑት ወ/ሮ ጄኒፈር ጆርዳን-ሳይፊ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እና ንጉሱ በአየር ንብረት ጉዳዮች ላይ 'ተመሳሳይ አጀንዳ' እንዳላቸው ተናግረዋል።

 አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በ2012 ዓ.ም. በዳቮስ በተካሄደው የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ዓመታዊ ስብሰባ በወቅቱ ንግስት ኤልሳቤት ሳይሞቱ በፊት የዌልስ ልዑል የነበሩት ያሁኑ ንጉስ ቻርልስ ሳልሳዊ ‘የዘላቂ ገበያዎች ተነሳሽነትን’ በግሉ ሴክተር ውስጥ ዘላቂነትን ለማስፈን በማለም ጀመሩ።

በቅርቡ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጄኒፈር ጆርዳን-ሳይፊ ከቫቲካን ባለስልጣናት ጋር ለመወያየት ሮምን ጎብኝተዋል። በዚህም ወቅት ስለ ንጉስ ቻርለስ ስነ-ምህዳር እይታ እና አመለካከታቸው ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺኮስ ጋር እንዴት እንደሚቀራረብ ለቫቲካን ዜና ተናግረዋል።

የጋራ እይታ

“አሁን ያለነው ቫቲካን ውስጥ ነው፥ ምክንያቱም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ከግርማዊነታቸው ጋር በአየር ንብረት እና በብዝሃ ህይወት ረገድ በጣም ተመሳሳይ ራዕይ ስላላቸው ነው” ሲሉ ወይዘሮ ጆርዳን ሳይፊ ገልፀዋል።

ሁለቱም መሪዎች በአካባቢ ጉዳይ ላይ ያዘጋጇቸውን ሰነዶች በተለይም የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ‘ላውዳቶ ሲ’ እና የንጉሥ ቻርለስ ‘ቴራ ካርታ’ “በጣም ተመሳሳይነት ያላቸው” መሆናቸውን አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።

ዓላማቸው በተለይም ተፈጥሮ፣ ጤና እና ኢኮኖሚው “በመሠረቱ የተሳሰሩ በመሆናቸው” በአየር ንብረት ጉዳዮች ላይ “መወሰድ ስላለባቸው አጣዳፊ እርምጃዎች ላይ” መመሪያ ለመስጠት እንደሆነ ገልጸዋል።

ወይዘሮ ዮርዳኖስ-ሳይፊ በሊቀ ጳጳሱ እና በንጉሱ መካከል ያለው ሌላው ተመሳሳይነት ሲገልጹ በሃይማኖቶች መካከል ለሚደረገው ግንኙነት ያላቸው ቁርጠኝነት ነው ብለዋል።

“እዚህ በቫቲካን ውስጥ መገኘታችን በጣም አስደናቂ ነገር ነው” ካሉ በኋላ፥ “በተለያዩ ተልእኮዎቻችን ውስጥ ‘ከፍተኛ ዕቅዶቻችንን’ እንዴት እንደምንመለከት መርምር እንችላለን” ብለዋል።

የእርምጃው አጣዳፊነት

ወ/ሮ ዮርዳኖስ-ሳይፊ ንጉስ ቻርለስ በአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ላይ “ከ50 ዓመታት በላይ” ሲሰሩ እንደ ነበር በመግለጽ፥ በዚያን ጊዜ “ዓለም ምን ያህል እንደተቀየረና ምን ያህል አጣዳፊ ለውጥ እንደመጣ ተገንዝበው ነበር” በማለት የንጉሱን ራዕይ አሳይተዋል።

ሃላፊዋ እንደሚናገሩት ይህ የጥድፊያ ስሜት “ሀገሮች በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ በግንባር ቀደምነት እንዲሰሩ” በንጉሱ የኮመንዌልዝ ሃገራት መሪነት ሥራ እንደተጠናከረ አብራርተዋል።

ስለ ዘላቂነት ሁሉም ሰው ማወቅ ያለበት አንድ ነገር ሲጠየቁ፥ ወ/ሮ ጆርዳን ሳይፊ “በእያንዳንዱ የሕይወታችን ዘርፍ” ላይ “ወጥ እና ዘላቂነት ያለው አቋም” መውሰድ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

“ቆሻሻን ስለማስወገድ ውሳኔ የምትወስን ልጅም ሆንክ ወይም የኩባንያው ዋና ስራ አስፈፃሚ፥ የአቅርቦት ሰንሰለቶችህ ዘላቂ መሆናቸውን ማረጋገጥ አለብህ” ካሉ በኋላ “በተቻለ መጠን ተስማሚ” የሆኑ ውሳኔዎችን ማድረግ ወሳኝ ነው ብለዋል።

'ቴራ ካርታ'

ንጉስ ቻርልስ “ዘላቂነትን በግሉ ሴክተር እምብርት ላይ ለማድረግ” በማለም በ2013 ዓ.ም. ‘ቴራ ካርታን’ ይፋ አድርገዋል። በሰነዱ መቅድም ላይ “የሰው ልጅ ባለፉት መቶ ዘመናት አስደናቂ እድገት አድርጓል፤ ሆኖም የዚህ እድገት ዋጋ እኛን የምትደግፈው ፕላኔት ላይ ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል። ይህንን ደግሞ በዚህ ሁኔታ ማስቀጠል አንችልም” ይላል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስን ሃዋሪያዊ ደብዳቤ በሆነው ‘ላውዳቶ ሲ' መግቢያ ላይ፥ “እህት ምድር ባደረግንባት ጥፋት ወደ እኛ በመጮህ ላይ ትገኛለች...፥ እኛ ራሳችን የምድር ትቢያ መሆናችንን ረሳነው። ሰውነታችን በንጥረ ነገሮችዋ የተዋቀረ ነው፣ አየሯን እንተነፍሳለን፣ ከውኃዋም ሕይወትንና ዕረፍትን እናገኛለን” በማለት መልዕክት ያስተላልፍልናል።
 

19 March 2024, 14:42