ፈልግ

የተፈናቀሉ የፍልስጤም ህጻናት በራፋ ጎዳና ዳር በሚገኝ ከጊዚያዊ ድንኳኖች ውስጥ የተፈናቀሉ የፍልስጤም ህጻናት በራፋ ጎዳና ዳር በሚገኝ ከጊዚያዊ ድንኳኖች ውስጥ   (AFP or licensors)

‘ሴቭ ዘ ችልድረን’ የጋዛ ህጻናት በጦርነቱ የደረሰባቸውን 'የአእምሮ ጉዳት' በማውገዝ መግለጫ አወጣ

የህጻናት አድን ድርጅት የሆነው ‘ሴቭ ዘ ችልድረን’ የጋዛ ህጻናት አምስት ወራትን ባስቆጠረው ጦርነት ምክንያት ስለሚደርስባቸው “ሙሉ የስነ-ልቦና ጉዳት” በማስጠንቀቅ፥ የሰብአዊ ዕርዳታ ድርጅቱ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ እና የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ ወደ ህዝቡ በፍጥነት እንዲደርስ በድጋሚ ተማጽኗል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ከብዙ ጥረቶች በኋላም ቢሆን የእርዳታ ቁሳቁሶችን የያዙ የጭነት መኪኖች የጋዛ ባህር ዳርቻ ላይ ከደረሱት እና አልፎ አልፎ በአውሮፕላን ከአየር ላይ ከሚለቀቁት ዕርዳታዎች በተጨማሪ፥ የበርካታ ሰዎችን ህይወት ለመታደግ ይቻል ዘንድ ብዙ የሰብአዊ ዕርዳታዎች በአስቸኳይ እንደሚያስፈልግ የእርዳታ ኤጀንሲዎች አሁንም እያስጠነቀቁ ይገኛሉ።

ከፍተኛ የሰብአዊ ዕርዳታዎችን ተደራሽ ለማድረግ ዋናው ስኬታማው መንገድ በድንበር ማቋረጫዎች በኩል በየብስ የሚደረገው አቅርቦት ቢሆንም፥ ነገር ግን በተለያዩ እገዳዎች ምክንያት በበቂ ሁኔታ ሰብአዊ ዕርዳታዎቹን ማሳለፍ እንዳልተቻለ ተነግሯል።

የበጎ አድራጎት ድርጅት የሆነው ‘ሴቭ ዘ ችልድረን’ ከሌሎች የረድኤት ድርጅቶች መካከል በተለየ መልኩ የምግብ እና የንፁህ ውሃ እጥረት እያስከተለ ያለውን ችግር ማሰማቱን ቀጥሏል።

በድጋሚ የቀረበው የተኩስ አቁም ጥሪ

የህጻናት አድን ድርጅቱ በዚህ ሳምንት በለቀቀው መግለጫ በጋዛ የህጻናትን ህይወት ለመታደግ እና ለመጠበቅ አፋጣኝ እና ፅኑ የሆነ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ በድጋሚ ጥሪውን ያቀረበ ሲሆን፥ የእስራኤል ባለስልጣናት “ገደብ የሌለበት የእርዳታ ፍሰትን እንዲፈቅዱ እና ህጻናት በረሃብ እና በበሽታ እንዳይሞቱ ለመከላከል ወደ ጋዛ የሚገቡ የንግድ እቃዎች መግባት እንዲጀምሩ” ጠይቋዋል።

የጋዛ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንደዘገበው በሐማስ የተመራው ታጣቂ ቡድን መስከረም 26 ላይ በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት በመክፈት ቢያንስ 33 ህጻናትን ጨምሮ 1200 ሰዎች ከተገደሉበት እና 253 ሰዎች ታግተው ከተወሰዱበት ጥቃት በኋላ በተቀሰቀሰው ጦርነት 12,550 ህጻናትን ጨምሮ ከ30,717 በላይ ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል።

የስነ-ልቦና ጉዳት

ሴቭ ዘ ችልድረን በተለይ በጋዛ ለአምስት ወራት በተካሄደው የቦምብ ድብደባ፣ ሞት፣ ውድመት እና መፈናቀል እንዲሁም በዚህም ሰበብ በደረሰው ረሃብ እና በሽታ ምክንያት በህፃናቱ ላይ እየደረሰ ስላለው “ያልተቋረጠ የአእምሮ ጉዳት” በማስጠንቀቅ፥ በተጨማሪም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ እየተባባሰ በመጣው ብጥብጥ፥ በጋዛ ውስጥ ቀደም ሲል የነበሩት የአእምሮ ጤና አገልግሎቶች ላይ አጠቃላይ ውድቀትን አስከትሏል ብሏል።

በጣም አልረፈደም

የፍልስጤም ሴቭ ዘ ችልድረን ዳይሬክተር የሆኑት ጄሰን ሊ እንደተናገሩት “የጋዛ ህፃናት እየደረሰ ካለው ጥቃት እና ከሚያስከትለው መጥፎ ውጤት ለመሸሽ በሚሞክሩበት ጊዜ በከፍተኛ ድንጋጤ እና ሀዘን ውስጥ ይገባሉ” በማለት ዬትኛውም ህፃን ይሄንን አሰቃቂ እውነታ መታገሥ እንደማይችል ገልጸዋል።

“ትክክለኛ ድጋፍ ከተደረገ፥ ህፃናቱ አሁን የሚፈልጉትን ወሳኝ እርዳታ እና የስነ-ልቦና ድጋፍ ሊያገኙ እንደሚችሉ ተስፋ አለ” ካሉ በኋላ ዳይሬክተሩ፥ “ነገር ግን ይህ እንዲሆን አስቸኳይ እና ቁርጥ ያለ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲሁም ሰብአዊ የእርዳታ ሰጪዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ አስተማማኝ እና ያልተገደበ የእርዳታ አቅርቦት ከሌለ ከእነዚህ ውስጥ አንዳቸውም ሊሳኩ አይችሉም” ብለዋል።

ሴቭ ዘ ችልድረን እ.አ.አ. ከ1953 ጀምሮ በክልሉ በሚካሄዱ ግጭቶች ምክንያት ለሚጎዱት የፍልስጤም ህፃናት ሕይወት አድን የሆነ የሰብአዊ ዕርዳታ እንዲሁም አስፈላጊ አገልግሎቶችን እና ድጋፍ ሲሰጥ ቆይቷል።
 

18 March 2024, 12:34