ፈልግ

ከስዊዘርላንድ የመጡ የአየር ንብረት ተሟጋቾች ስትራስበርግ በሚገኘው የአውሮፓ የሰብአዊ መብቶች ፍርድ ቤት ፊት ለፊት የተለያዩ ባነሮችን ይዘው ከስዊዘርላንድ የመጡ የአየር ንብረት ተሟጋቾች ስትራስበርግ በሚገኘው የአውሮፓ የሰብአዊ መብቶች ፍርድ ቤት ፊት ለፊት የተለያዩ ባነሮችን ይዘው   (ANSA)

የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት አየር ንብረት ለውጥን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ አስተላለፈ

የአውሮፓ የሰብአዊ መብቶች ፍርድ ቤት ባለፈው ማክሰኞ እንደገለጸው ስዊዘርላንድ የልቀት ቅነሳ ግቦችን ለማሟላት በበቂ ሁኔታ መስራት አለመቻሏ የሰብአዊ መብቶችን መጣስ እንደሆነ ገልጿል።

 አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የሰብዓዊ መብት ጥሰት አቤቱታዎችን የሚመለከተው ፈረንሳይ የሚገኘው የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት እ.አ.አ በ1950 የፀደቀውን የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ መሰረት አድርጎ እ.አ.አ በ1959 የተቋቋመ ፍርድ ቤት ነው። ይኽው ድንጋጌ ቁጥራቸው ወደ ስምንት መቶ ሚሊዮን ለሚጠጋ ዜጎች ብቻ ሳይሆን በአባል ሀገራት ግዛት ውስጥ ለሚገኙ ሁሉ መሰረታዊ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶችን ለማስጠበቅ የአውሮፓ ምክርቤት አባላት ቃል የገቡበት ዓለም ዓቀፍ ውል ነው።

ይህ ፍርድ ቤት ማክሰኞ ዕለት ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዙ ሶስት ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ያስተላለፈ ሲሆን፥ የመጀመሪያ ሁለቱን ውድቅ በማድረግ ሶስተኛውን ጉዳይ በተመለከተ ስዊዘርላንድ የልቀት ቅነሳ ግቦችን ለማሟላት በቂ ጥረት ባለማድረጓ በሃገሪቷ የሚገኙ የሴቶች ቡድን ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰት ፈፅማለች ሲል ውሳኔ ሰጥቷል።

የስዊዘርላንድ ጉዳይ ላይ ያተኮረው ፍርድ ቤቱ አብዛኛዎቹ አረጋውያን የሆኑ ወደ 2400 የሚጠጉ ስዊዘርላንዳውያን ሴቶችን በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በሚፈጠረው የሙቀት ማዕበል ጤናቸውን እና አኗኗራቸውን ይጎዳል እንዲሁም ለሞት የመጋለጥ እድላቸው ከፍ ያደርጋል በሚል ነው።

ፍርድ ቤቱ “የአየር ንብረት ለውጥ በህይወት፣ በጤና፣ በደህንነት እና በአኗኗር ዘይቤ ላይ ከሚያስከትላቸው ከፍተኛ አሉታዊ ተፅእኖዎች ውጤታማ ጥበቃ የማግኘት መብትን በተመለከተ መንግስት የአየር ንብረት ግዴታውን መወጣት ባለመቻሉ የሰብአዊ መብቶቻቸውን መጣስ ነው” በማለት ትዕዛዝ ሰጥቷል።

በፈረንሣይ ከንቲባ እና በፖርቹጋል ወጣቶች ቡድን በኩል የመጡ ሌሎች ሁለት ጉዳዮች ውድቅ የተደረጉ ሲሆን፥ የፖርቹጋላዊያኑ ወጣቶች ጉዳይ በአገራቸው ውስጥ ያሉትን ሁሉንም የህግ መንገዶች እስካሁን ያላሟሉ መሆናቸውን እና ከፖርቹጋል ውጭ ባሉ ሀገራት የይግባኝ ጥያቄያቸውን ለማቅረብ ምንም ዓይነት በቂ ምክንያት እንደሌላቸው ፍርድ ቤቱ ወስኗል።

የአውሮፓ ፍርድ ቤት ውሳኔዎች ለዬትኛውም ይግባኝ ክፍት ስላልሆኑ፥ ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ በሁሉም የ 46 አባል ሀገራት ላይ የሚተላለፉ ውሳኔዎች አስገዳጅ ናቸው ተብሏል። ይህ በመሆኑም የስዊዘርላንድ መሪዎች የፍርድ ቤቱን ውሳኔ መልሰው እንደሚያጤኑት ተናግረዋል።

ማክሰኞ ዕለት የተላለፉት ውሳኔዎች በተለይ ፍርድ ቤቶች የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ በህጋዊ ግዴታዎች ላይ ውሳኔ መስጠት እንደሚችሉ እና ከዚህ በኋላ ለሚወሰኑ ውሳኔዎችም የይግባኝ ጥያቄዎች ማንሳት እንዲቻል መንገድ ከፍተዋል ተብሏል።
 

11 April 2024, 14:00