ፈልግ

ስደተኞች ወደ አውሮፓ ህብረት ለመሻገር ሲሞክሩ መጀመሪያ ወደ ቱርክ እና ግሪክ አዋሳኝ ድንበር ይሄዳሉ ስደተኞች ወደ አውሮፓ ህብረት ለመሻገር ሲሞክሩ መጀመሪያ ወደ ቱርክ እና ግሪክ አዋሳኝ ድንበር ይሄዳሉ  (ANSA)

የአውሮፓ ህብረት አዲሱ የጥገኝነት እና የስደት ስምምነት የሰብአዊ መብት ቡድኖችን ቅር አሰኝቷል ተባለ

የአውሮፓ ፓርላማ ከዓመታት ድርድር በኋላ የህብረቱን የስደተኞች እና የጥገኝነት ደንቦችን የሚያጠናክር ትልቅ ማሻሻያ አጸደቀ። የእርዳታ ኤጀንሲዎች እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ህጉ የችግሩ ሰለባ የሆኑትን በጣም ለተቸገሩ ሰዎች ከለላ እንዳይሰጥ እንቅፋት ይሆናል በማለት በጽኑ ተቃውመውታል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የአውሮፓ ፓርላማ የህብረቱን የስደተኞች እና የጥገኝነት ደንቦችን የሚያጠናክር ማሻሻያ ሚያዚያ 2 ቀን 2016 ዓ.ም. አፅድቋል። አዲሱ ሕግ የጥገኝነት ሂደትን ለማፋጠን እና መደበኛ ያልሆኑ ስደተኞች ደግሞ ወደ አገራቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ ለማፋጠን ያለመ ሲሆን፤ ይህ ህግ በጎረጎሲያኑ በ2026 ተፈጻሚ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

የአውሮፓ ፓርላማ ዋና ዋና በሚባሉ የፖለቲካ ቡድኖች የተደገፈው አዲሱን የአውሮፓ ህብረት የስደት እና የጥገኝነት ስምምነት ለማፅደቅ ከአክራሪ ፓርቲ ተወካዮች የደረሰባቸውን ብርቱ ተቃውሞ በመቋቋም ያሸነፉ ሲሆን፥ ህጉ የፀደቀው በወግ አጥባቂ እና በለዘብተኛ ህግ አውጪዎች እንዲሁም በሰሜን እና በደቡብ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት መካከል ለአስር ዓመታት ያክል የዘለቀ ከፍተኛ ክርክር ከተረገ በኋላ ነው።

ረቡዕ ዕለት ለአስር ጊዜያት ያክል በተከታታይ በተሰጠ ድምጽ የፀደቀው አዲሱ የአውሮፓ ህብረት የጥገኝነት እና የፍልሰት ስምምነት ወደ ህብረቱ የሚደረገውን ፍልሰት ተፅእኖ ለመቆጣጠር ያለመ ሲሆን፥ ጥገኝነት ጠያቂዎቹ ወደ ሃገራቱ ሲደርሱ ማን ሃላፊነት መውሰድ እንዳለበት ለመወሰን እና የጥገኝነት ጥያቄዎችን የማስተናገድ ሸክም አባል ሀገራቱ በእኩል እንዲጋሩ ለማድረግ መሆኑ ተገልጿል።

የአውሮፓ ህብረት የሀገር ውስጥ ጉዳይ ኮሚሽነር በስምምነቱ ላይ ያላቸውን አስተያየት ሲሰጡ፣ ህብረቱ የውጭ ድንበሮችን፣ አቅመ ደካሞችን እና ስደተኞችን በተሻለ ሁኔታ ለመጠበቅ፣ ብሎም ጥያቄያቸው ተቀባይነት ያላገኙትን በፍጥነት ለመመለስ ያለመ ሲሆን፥ የስምምነቱ ፈራሚ አባል ሀገራት መካከል “አስገዳጅ የሆነ የትብብር ማዕቀፍ” እንደሚኖርም ያበረታታል ብለዋል።

በተጨማሪም በደቡባዊ አውሮፓ ላይ የሚደርሰውን ጫና ለመቅረፍ ሁሉም አባል ሀገራት መጠናቸው እና ቦታቸው ምንም ይሁን ምን የበኩላቸውን አስተዋፅዖ ያበረክታሉ ተብሏል።

የሰብአዊ መብት ቡድኖች በህጉ ቅሬታ አሰምተዋል

ካሪታስ አውሮፓ በአዲሱ ስምምነት ቅሬታ እንደተሰማው በመግለጽ፥ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ጥገኝነት ጠያቂዎች የመዘዋወር መብታቸው እንዳይከበር ቃል በቃል ውስብስብ በሆነው “አስገዳጅ የአብሮነት ዘዴ” ተብለው በተቀመጡ እርምጃዎች ላይ ይመረኮዛል ብሏል።

ሴቭ ዘ ችልድረን በበኩሉ የስምምነቱ ፈራሚዎች ለህፃናት ጥበቃ ቅድሚያ እንዲሰጡ እና መብቶቻቸውን የሚጎዱ አደጋዎችን ለመቀነስ እርምጃዎችን እንዲወስዱ የተጠየቁትን ጥያቄዎች ችላ ማለታቸውን ገልጿል። እንዲያውም ይላል የበጎ አድራጎት ድርጅቱ፣ ስምምነቱ በአውሮፓ ውስጥ የህጻናት እና ቤተሰቦችን ጥገኝነት የማግኘት መብትን የሚነፍግ፣ በድንበር ላይ ለእስር እንዲዳረጉ፣ ብሎም በግዳጅ ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ እና ለድህነት እንዲጋለጡ ያደርጋቸዋል ብሏል።

27ቱ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ምናልባትም ስምምነቱ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት በሚያዚያ ወር መጨረሻ ላይ በሚደረግ ድምጽ የማሻሻያ ስምምነቱን ማፅደቅ አለባቸው ተብሏል።
 

12 April 2024, 15:10