ፈልግ

የእስራኤል ዜጎች ቴላቪቭ በሚገኘው የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ፊት ለፊት በመውጣት ታጋቾችን ለማስፈታት ውይይት እንዲደረግ ጠይቀዋል የእስራኤል ዜጎች ቴላቪቭ በሚገኘው የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ፊት ለፊት በመውጣት ታጋቾችን ለማስፈታት ውይይት እንዲደረግ ጠይቀዋል  (AFP or licensors)

በእስራኤል በ10ሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰልፈኞች ታጋቾች እንዲፈቱ ጠየቁ

ከስድስት ወራት በፊት በሃማስ ታጣቂ ቡድኖች ታግተው የተወሰዱት ሰዎች እንዲፈቱ ለመጠየቅ በቴል አቪቭ ጎዳናዎች ላይ የተሰበሰቡትን በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የመንግስት ተቃዋሚዎችን የሃገሪቱ ፖሊስ በኃይል መበተኑን የእስራኤል የሚዲያ ተቋም ገልጿል።

 አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ፍልስጤማውያን ታጣቂዎች ደቡባዊ እስራኤል ውስጥ ዘልቀው በመግባት ጥቃት ካደረሱ ስድስት ወራትን ያስቆጠረ ሲሆን፥ በወቅቱ ታግተው ከተወሰዱ ሰዎች መሃል ከ100 በላይ እስራኤላውያን አሁንም ድረስ በምርኮ ይገኛሉ።

ሐማስ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት በፈጸመበት ወቅት 1ሺህ 200 ሰዎችን ገድሎ 253 ሰዎችን ደግሞ አግቶ ወደ ጋዛ መውሰዱ ይታወሳል።

ይህ ሰልፍ በእስራኤል መዲና ቴል አቪቭ እና በሌሎች ከተሞች የተደረገው የአገሪቱ ጦር ኤልዳ ካትዚር የተባለ ታጋች አስክሬንን ማግኘቱን ቅዳሜ ዕለት ይፋ ማውጣቱን ተከትሎ ነው። ሐማስ ከሦስት ወራት በፊት ባጋራው ተንቀሳቃሽ ምስል ኤልዳ በሕይወት ታይቶ እንደነበር ዘገባዎች ያሳያሉ።

የዋና ከተማዋ ቴል አቪቭን ዋና መተላለፊያዋ መንገድ ዘግተው የነበሩ ተቃዋሚ ሰልፈኞችን ፖሊስ በኃይል ለመበተን ባደረገው ሙከራ በተፈጠረው ግጭት ቢያንስ አራት ሰዎች መታሰራቸው ተነግሯል።

ተቃዋሚዎቹ ሐማስ እና አጋሮቹ በጋዛ ያገቷቸውን 130 ታጋቾች የእስራኤል መንግሥት ማስለቀቅ አለመቻሉ እንዳበሳጫቸው አስተያየት ሲሰጡ ነበር።

የዚህ የተቃውሞ ሰልፍ አስተባባሪዎች እንደገለጹት ድምጻቸውን ለማሰማት በቴል አቪቭ የተገኙ ሰዎች ቁጥር 100ሺህ እንደሚሆን ገልጸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሃማስ በጋዛ ሰርጥ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመወያየት እንዲሁም በታጣቂ ቡድኑ እና በእስራኤል መካከል የሚደረገውን የእስረኞች ልውውጥ ተግባራዊ ማድረግ በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ ለመነጋገር ከመሪዎቹ የተወጣጡ የልዑካን ቡድን ወደ ካይሮ ልኳል።

ሃማስ ከዚህ በፊት ማለትም መጋቢት 5 በተደረገው ውይይት ባቀረበው አቋም አሁንም እንደሚቀጥል የተናገረ ሲሆን፥ ከእነዚህም አቋሞቹ ውስጥ “ቋሚ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ፣ የእስራኤል ጦር ከጋዛ እንዲወጣ፣ የተፈናቀሉ ግለሰቦች ወደ መኖሪያ አከባቢያቸው መመለስ፣ የሰዎች የመንቀሳቀስ ነፃነት እንዲከበር፣ ሰብአዊ እርዳታ እና መጠለያ እንዲዘጋጅ፣ እንዲሁም ትክክለኛ የሆነ የእስረኞች ልውውጥ ስምምነት እንዲደረግ የሚሉ ይገኙበታል።

ከዚህ ቀደም በነበረው ውይይት ሃማስ ጦርነቱ ሙሉ በሙሉ እንዲቆም አጥብቆ የጠየቀ ሲሆን፥ እስራኤል ግን ለአጭር ጊዜ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ብቻ በመስማማት፥ ሃማስ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ያቀረበውን ጥያቄ ውድቅ አድርጋለች።

እስራኤል በጋዛ ላይ እየወሰደችው ባለው ጥቃት እስካሁን አብዛኛዎቹ ሕጻናት እና ሴቶች የሆኑ ከ33ሺህ በላይ ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል።
 

08 April 2024, 14:13