ፈልግ

ከሁለት ሳምንት ቆይታ በኋላ የእስራኤል ጦር ጋዛ ከሚገኘው አል-ሺፋ ሆስፒታል ለቆ ወጥቷል ከሁለት ሳምንት ቆይታ በኋላ የእስራኤል ጦር ጋዛ ከሚገኘው አል-ሺፋ ሆስፒታል ለቆ ወጥቷል  (ANSA)

የእስራኤል ጦር ከሁለት ሳምንታት በኋላ ጋዛ ከሚገኘው አል-ሺፋ ሆስፒታል ለቆ ወጣ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በጋዛ ሰርጥ ሰላም እንዲሰፍን የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ጥሪያቸውን ካቀረቡ ከአንድ ቀን በኋላ፣ የእስራኤል ወታደሮች ለሁለት ሳምንታት ተቆጣጥረው ከነበረው የጋዛ ትልቁ ሆስፒታል አል ሺፋን ለቀው መውጣታቸው ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የእስራኤል ወታደሮች የሆስፒታሉን ቅጥር ጊቢ ለቀው ሲወጡ መጠነ ሰፊ ውድመትን አድርሰው እንደነበር የተነገረ ሲሆን፥ ወታደሮቹ በሁለት ሳምንታት ቆይታቸውም ወደ 200 የሚጠጉ ታጣቂዎችን መግደላቸውን እና ወደ 900 የሚጠጉ ተጠርጣሪዎችን ማሰራቸው ተገልጿል።

በመቶዎች የሚቆጠሩ የእስራኤል ጦር ሠራዊት አባላት ከሁለት ሳምንታት በፊት ነበር የጋዛ ሰርጥ ትልቁ ሆስፒታልን የወረሩት።

እሑድ ጥዋት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ አል-ሺፋ “የሽብርተኞች መሸሸጊያ” ሆኗል ካሉ በኋላ፣ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ ከ200 በላይ የፍልስጤም ታጣቂ ቡድን አባላት መገደላቸውን ተናግረዋል።

በሆስፒታሉ ላይ ከተካሄደው ወረራ እና ጥቃት በኋላ የጋዛው ሆስፒታል ሕንፃ ባዶውን ቀርቶ ታይቷል።

የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት እንደገለጸው ወታደሮቹ በመቶዎች የሚቆጠሩ “ሽብርተኞችን” ገድለዋል እንዲሁም በቁጥጥር ሥር አውለዋል ያለ ሲሆን፥ ሠራዊቱ “በሆስፒታሉ ዙሪያ” የጦር መሣሪያዎች እና የደኅንነት መረጃዎች ማግኘቱን ገልጿል።

የእስራኤል ጦር፤ በአል-ሺፋ ሆስፒታል ላይ ወረራ እና ጥቃት የፈጸመው ሐማስ መልሶ ስለተደራጀበት መሆኑንም ይገልፃል።

በሌላ ዜና በመቶዎች የሚቆጠሩ እስራኤላውያን ተቃዋሚዎች በእየሩሳሌም በሚገኘው ፓርላማ ደጃፍ ጠቅላይ ሚኒስትር ናታንያሁ ከስልጣን እንዲወርዱ ጥያቄያቸውን ሲያቀርቡ ከቆዩ በኋላ ሲመሽም እዚያው በጊዜያዊ ድንኳኖች ውስጥ ማደራቸው የተነገረ ሲሆን፥ እስራኤላዊያን ሃማስ መስከረም 26 እስራኤል ላይ ለወሰደው ጥቃት በአግባቡ ምላሽ መስጠት አልቻሉም በሚል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ ማሰማት ከጀመሩ ሰነባብተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበኩላቸው በአሁኑ ሰዓት ምርጫ ማካሄድ እስራኤልን ሽባ ማድረግ ነው ሲሉ ይከራከራሉ።

እሁድ ዕለት በሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች የተሳተፉበት የተቃውሞ ሰልፍ፥ ጦርነቱ በጋዛ ሰርጥ ከተቀሰቀሰ በኋላ ከተደረጉት ሰልፎች ትልቁ ፀረ-መንግስት ሰልፍ ነው ተብሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የፍልስጤማውያን ራስ ገዝ ፕሬዚደንት የሆኑትን ማህሙድ አባስ የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ አማካሪያቸው በሆኑት በጠቅላይ ሚኒስትር መመሀድ ሙስጠፋ የቀረበውን አዲስ ካቢኔ ሐሙስ ዕለት አጽድቀዋል፡፡ አዲሱ መንግስት 23 ሚኒስትሮችን ያቀፈ ሲሆን ከነዚህም መካከል ሶስት ሴቶች እና 6 ካጋዛ የመጡ ፍልስጤማውያን ይገኙበታል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነትን ደርበው የሚያገለግሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በእስራኤል ቁጥጥር ሥር ባለችው ዌስት ባንክ ውስጥ ያለውን ውስን አገዛዝ የሚተገብረውን የፍልስጤም አስተዳደርን የማሻሻል ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል።

የፍልስጤም ራስ ገዝ አስተዳደር አንዳንድ ማሻሻያዎችን ማድረጉ አስፈላጊ ነው ስትል ዩናይትድ ስቴትስ አዲሱን ካቢኔ በደስታ ተቀብላለች።
 

02 April 2024, 13:08