ፈልግ

የሰብአዊ እርዳታ ለጋዛ ከአውሮፕላን ላይ (በፓራሹት) ሲወርድ  የሰብአዊ እርዳታ ለጋዛ ከአውሮፕላን ላይ (በፓራሹት) ሲወርድ   (AFP or licensors)

እስራኤል በወሰደችው ጥቃት የሞቱት የውጭ እርዳታ ሰራተኞች በተመለከተ ምርመራ እየተካሄደ ነው ተባለ

እስራኤል በጋዛ እየፈጸመችው ባለው የአየር ጥቃት “ለወርልድ ሴንትራል ኪችን ይሰሩ የነበሩ ሰባት የረድኤት ሰራተኞች ህይወት ማለፉን ተከትሎ የእሥራኤል ጦር ጥልቅ ግምገማ እያካሄድኩ ነው” ብሏል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

'ዎርልድ ሴንትራል ኪችን' የተሰኘው የዩናይትድ ስቴትስ የእርዳታ ድርጅት ባወጣው መግለጫ መሰረት አውስትራሊያዊ፣ እንግሊዛዊ፣ አሜሪካ-ካናዳዊ፣ ፍልስጤማዊ እና ፓላንዳዊ ዜግነት ያላቸውን ጨምሮ ሰባት ሰራተኞቹ በእስራኤል መከላከያ የአየር ጥቃት እንደተገደሉበት የተቋሙ መስራች ሼፍ ሆዜ አንድሬስ ገልጸዋል።

ከዚህም ባለፈ የበጎ አድራጎት ድርጅቱ በጋዛ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ማቆሙን ተናግሯል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ “ሆን ተብሎ ባልተፈጸመው” የእስራኤል ጥቃት “ንጹሃን” ሰዎች መሞታቸውን ካመኑ በኋላ፥ “ይህ ነገር ድጋሚ እንዳይከሰት ሁሉንም ነገር እናደርጋለን” ብለዋል።

የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ፎን ደር ሌየን ህይወታቸውን ላጡ የእርዳታ ሰራተኞች ስለ አገልግሎታቸው በማመስገን፥ 'ለቤተሰቦቻቸው እና ለጓደኞቻቸው የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን’ ገልጸዋል።

በተመሳሳይ ጊዜ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ዜናውን በሰሙ ጊዜ “በጣም መደናገጣቸውን እና ማዘናቸውን” ገልጸው፥ “በጉዳዩ ዙሪያ በግልጽ መመለስ ያለባቸው ጥያቄዎች አሉ” ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የቆጵሮስ ፕሬዝዳንት ኒኮስ ክሪስቶዱሊዴስ በጋዛ የእርዳታ ሰራተኞቹ መሞታቸውን ተከትሎ የዓለም መሪዎች ወደ ጋዛ ዕርዳታ ለማድረስ የሚያደርጉትን ጥረት “በእጥፍ” መጨመር አለባቸው ብለዋል።

የዎርልድ ሴንትራል ኪችን ሰራተኞች ከቆጵሮስ በባህር ተጉዘው ወደ ጋዛ ያመጡትን የምግብ እርዳታ ከጭነት መኪናዎቻቸው በማውረድ ላይ እያሉ ነበር ጥቃት የደረሰባቸው።
 

03 April 2024, 14:48