ፈልግ

በካርኪቭ ላይ በደረሰ የሮኬት ጥቃት የተጎዱ ቤቶች በካርኪቭ ላይ በደረሰ የሮኬት ጥቃት የተጎዱ ቤቶች  (ANSA)

ዩክሬን ሲቪል ዜጎቿ በብዛት እየሞቱባት እንደሆነ አሳወቀች

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በዩክሬን ሰላም እንዲሰፍን ጸሎት እንዲደረግ ያቀረቡት ጥሪ በሩሲያ ወረራ ምክንያት በጦርነት የምትታመሰው ሃገር ወታደሮቿን ብቻ ሳይሆን ሲቪል ዜጎቿንም ጭምር እያጣች በመሆኑ ሲሆን፥ በሳምንቱ መጨረሻ እንኳ ከ12 በላይ ሰላማዊ ሰዎች እንደሞቱ ተነግሯል። ሩሲያ በበኩሏ በአውሮፓ ትልቁ የሆነውን የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎቿ ላይ ጥቃት ፈፅማለች ስትል ዩክሬንን ወቅሳለች።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በዩክሬን ደቡባዊ ምስራቅ ዛፖሪዝሂያ ክልል ውስጥ በሚገኘው ጉሊያይፖሌ በምትባለው መንደር ባለፈው እሁድ ሩሲያ ባደረሰችው ጥቃት ቢያንስ 3 ንፁሀን ዜጎች መሞታቸውን ባለሥልጣናቱ ገልፀው፥ ዩክሬናዊያን አሁንም በጦርነት አረንቋ እየተሰቃዩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

ከሁለት ዓመት በላይ በዘለቀው ጦርነት ውስጥ በባለፈው ጥቃት የሞቱት ሁለት ወንድና አንዲት ሴት በቅርብ ጊዜ የታወቁት ሲቪላዊያን ሰለባዎች ናቸው ተብሏል።

የዩክሬን ጦር ሩሲያ በአንድ ጀምበር ብቻ ካሰማረቻቸው በርካታ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ውስጥ 17ቱን መትቶ ባይጥል ኖሮ የሟቾች ቁጥር ሊጨምር ይችል እንደነበር ባለስልጣናቱ ጠቁመዋል።

ከጥቃቱ ቀን ቀደም ብሎ ቅዳሜ ዕለት በሰሜን ምስራቃዊ ካርኪቭ አካባቢ ሁለት የሩስያ ሚሳኤል እና ሰው አልባ አውሮፕላኖች በፈጸሙት ጥቃት በትንሹ ስምንት ሰዎች ሲገደሉ፥ ወደ 10 የሚጠጉ ሰዎችን ደግሞ አቁስለዋል ሲሉ ባለስልጣናት ተናግረዋል።

በሌላ ዜና በዶኔትስክ ምስራቃዊ ክልል በምትገኘው በኩራኪቭካ መንደር ላይ በተደረገ የመድፍ ጥቃት የ38 ዓመት ሴት እና የ16 ዓመት ሴት ልጇን ጨምሮ አራት ሰዎች መሞታቸውን የአካባቢው ባለስልጣናት የገለጹ ሲሆን፥ በሌላ አከባቢ ደግሞ በክራስኖሆሪቭካ መንደር ውስጥ የ25 ዓመት ወጣት መገደሉ ተነግሯል።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ ሩሲያ የረዥም ርቀት የቦምብ ጥቃት ዘመቻዋን ከቀጠለች ዩክሬን የአየር ጥቃት መከላከያ ሚሳኤሎቿን እየጨረሰች ስለሆነ የሟቾች ቁጥር ሊያሻቅብ እንደሚችል ጠቁመዋል።

ኔቶ ቃል ገብቷል

የኔቶ ዋና ፀሃፊ ጄንስ ስቶልተንበርግ 75ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን እያከበረ የሚገኘው የኔቶ ወታደራዊ ህብረት ዩክሬንን እንደማይተው ቃል ገብተዋል።

በአምስት ዓመታት ውስጥ ለዩክሬን ሊሰጥ በታቀደው የ100 ቢሊዮን ዩሮ (107 ቢሊዮን ዶላር) የገንዘብ ድጋፍ ዙሪያ ውይይቶች የተደረጉ ሲሆን፥ ሃላፊው “ለረጅም ጊዜ የሚሆን ለዩክሬን አስተማማኝ እና ሊተነበይ የሚችል የደህንነት ድጋፍ ማረጋገጥ አለብን” ካሉ በኋላ “የኔቶ አጠቃላይ የእርዳታ ጥቅልን ወደ ባለብዙ ዓመት የእርዳታ ፕሮግራም እየቀየርን ነው” ብለዋል።

አቶ ስቶልተንበርግ አክለውም እንደተናገሩት “ይሁን እንጂ በጦር ሜዳ ላይ ያሉት የዩክሬን ወታደሮችም ሌሎች ፈተናዎች ይገጥሟቸዋል፥ በኬሚካል የጦር መሳሪያዎች ስምምነት መሰረት በጦርነት ወቅት የተከለከሉ ቢሆኑም ሩሲያ አስለቃሽ ጭስ የሚጥሉ ድሮኖች እና ሌሎች ኬሚካሎችን ትጠቀማለች” ብለዋል።

በምላሹ ሞስኮ በሩሲያ ይዞታ ስር የሚገኘውን በአውሮፓ ትልቁ የሆነውን ዛፖሪዝሂያ የኒውክሌር ጣቢያን እሁድ እለት አጥቅታለች ስትል ኪየቭን ከሳለች። በጥቃቱም በጣቢያው መመገቢያ ክፍል አጠገብ በቆመ መኪና ላይ ጉዳት አድርሷል የተባለ ሲሆን፥ ያስከተለው የጨረር ፍንጣቂም ሆነ በሰው ህይወት ላይ የደረሰ ጉዳት የለም ተብሏል።

ሩሲያ በኦሬንበርግ ክልል ውስጥ በሚገኘው ግድብ ላይ በተከሰተው ፍንዳታ ምክንያት ቢያንስ 900 ህጻናትን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለቀው እንዲወጡ ያስገደደውን ክስተት በማጣራት ላይ እንደሆነች ገልፃለች። ይሁን እንጂ ለዚህ ጉዳይ ዩክሬንን ተጠያቂ የሚያደርጉ እና የሚጠቁሙ ምልክቶች እስካሁን አልተገኙም ተብሏል።

የሰላም ጉባኤ

ጦርነቱ እየተባባሰ በሄደበት በአሁኑ ወቅት የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ እንደገለጹት እሳቸው እና የስዊዘርላንዱ ፕሬዝዳንት ቪዮላ አምኸርድ በስዊዘርላንድ የሚካሄድ “የዓለም የሰላም ጉባኤ” ሲሉ የጠሩትን ስብሰባ በቅርብ ቀናት ውስጥ እናዘጋጃለን የሚል ተስፋ አለኝ ብለዋል።

በስብሰባው ላይ ቢያንስ ከ80 እስከ 100 ሀገራት ይሳተፋሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፥ ሞስኮ የሰላም ጉባኤው ያለ ሩሲያ ተሳትፎ ትርጉም የለሽ ነው ስትል ተናግራለች።

ቀደም ሲል ኪየቭ ሩሲያን ወደ ስብሰባው እንደማትጋበዝ ግልጽ አድርጋለች።
 

09 April 2024, 16:07