ፈልግ

የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እና የዲፕሎማሲ ልዑካን የጣይቤ ከተማን በጎበኙበት ወቅት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እና የዲፕሎማሲ ልዑካን የጣይቤ ከተማን በጎበኙበት ወቅት 

አባ ኢብራሂም ፋልታስ፥ ከጣይቤህ ከተማ የሰላም ተማጽኗቸውን አቀረቡ

በፍልስጤም ሙሉ በሙሉ ክርስቲያን ሠፋሪዎች በሚገኙበት መንደር የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ የቅድስት አገር ረዳት ተከንከባካቢ አባ ኢብራሂም ፋልታስ የሰላም ተማጽኗቸውን አቅርበው፥ በአረብኛ ቋንቋ “ታይቤህ” ማለት ትርጉሙም “መልካም” ማለት ቢሆንም ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሙሉ በሙሉ ክርስቲያን ማኅበረሰብ በሚኖርበት የፍልስጤም መንደር ምንም መልካም ነገር አለመታየቱን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሰኞ ሐምሌ 7/2017 ዓ. ም. በቅድስት ሀገር የሚገኙ የአብያተ ክርስቲያናት አባቶች ከአምባሳደሮች እና ቆንስላዎች ጋር በመሆን ለሳምንታት በመቶዎች በሚቆጠሩ የእስራኤል ሠፋሪዎች ከፍተኛ ጥቃት እየደረሰባቸው ላለው የጣይቤህ ከተማ ነዋሪዎች እና ቀሳውስት ያላቸውን ቅርበት እና አጋርነት ገልጸዋል። የእስራኤል ሠፋሪዎች የፍልስጤማውያንን ቤት እና መሬት በኃይል ለመያዝ እየሞከሩ እንደሚገኙ ታውቋል።

ታይቤህ ወደ 1,500 የሚጠጉ ነዋሪዎች ያሉባት አካባቢ ስትሆን፥ ነዋሪዎቿ በሙሉ የልዩ ልዩ የክርስትና እምነት ተከታይ ማለትም የላቲን፣ የግሪክ ኦርቶዶክስ እና የመልቃይት እምነት ተከታዮች እንደሆኑ ታውቋል። ሰኞ ሐምሌ 7/2017 ዓ. ም. ማለዳ፣ የሃይማኖት መሪዎች ፣ ነዋሪዎች እና ከአጎራባች መንደሮች የመጡ ሰዎች ስቃያቸውን በትክክል የሚረዱት ወደ ሥፍራው በመምጣት ለሰጡት ወንድማዊ ድጋፍ አባ ኢብራሂም ፋልታስ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ከኢየሩሳሌም በስተሰሜን በኩል ወደ ታይቤህ ሲደርሱ መንደሩ የተለመደውን የእንግዳ ተቀባይነት ስሜት እንደሚገልጽ የገለጹት አባ ኢብራሂም ፋልታስ፥ የሦስቱ አብያተ ክርስቲያናት የደወል ማማዎች ከመሬት ገጽታው ከፍ ብለው ሰላም እና አንድነት ያለበትን ማኅበረሰብን የሚያመላክቱ መሆናቸውን አስረድተው፥ ከአካባቢው ጎልማሶች፣ ሽማግሌዎች እና ልጆች በፍርሃት፣ በሕመም የተዋጡ እና ያለፉት ሳምንታት ውጥረት የሚገልጹ ድምጾችን መስማት እንደሚቻል አባ ኢብራሂም ፋልታስ ተናግረዋል።

በአካባቢው በርካቶች መሞታቸውን እና በርካቶችም መቁሰላቸውን የገለጹት አባ ኢብራሂም ፋልታስ፥ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን፣ ሕንፃዎች መፍረሳቸውን፣ ሜዳዎች በእሳት መቃጠላቸውን ተናግረው፥ እነዚህ ጥቃቶች ባልታጠቁ ሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ የፈሪ ጥቃቶች ናቸው” ሲሉ ገልጸው፥ ለብዙ መቶ ዓመታት የኢየሱስ ክርስቶስ ዘመን ባሕል ባላት አገር ውስጥ ለአባቶቻቸው እምነት ታማኝ ሆነው በቆዩት ሰዎች ላይ የደረሰ ጥቃት እንደሆነ አስረድተዋል።

ነገር ግን አንድም የጥላቻ ወይም የበቀል ቃል ሳይወጣ በምድራቸው ላይ በሰላም መኖር እንዲፈቀድላቸው ከልብ የመነጨ ልመና ብቻ ማቅረባቸውን አባ ኢብራሂም ፋልታስ ገልጸው፥

ቅድስት ምድር ስቃይ ውስጥ እንደምትገኝ፣ እያንዳንዱ ነዋሪ እና እያንዳንዱ አካባቢ በግፍ እየቆሰለ እንደሚገኝ አስረድተዋል። በጋዛ እልቂቱ ቀጥሏል ያሉት አባ ኢብራሂም ፋልታስ ሰዎች የምግብ ዕርዳታ ለማግኘት ተሰልፈው ወረፋቸውን ሲጠብቁ እንደሚገደሉ፣ የሚበላ ምግብ ስለጠየቁ ብቻ እንደሚዋረዱ ሕጻናት የሕይወት እና የመጽናኛ ምንጭ የሆነውን ውሃ በማጣት ብቻ እንደሚሞቱ አስረድተዋል።

“በዌስት ባንክ በተለይም በቤተልሔም የዕለት ተዕለት ኑሮን መቋቋም የማይችል እየሆነ መጥቷል” ያሉት አባ ኢብራሂም ፋልታስ፥ የአካባቢው ክርስቲያኖች ለደህንነታቸው ሲሉ ትውልድ አገራቸውን ለቀው እንዲወጡ መገደዳቸውን ገልጸው፥  እንደ እምነት ሰዎች ማንነታቸውን ለመጠበቅ በቤታቸው ለመቆየት እንደሚናፍቁ አስረድተዋል። ነገር ግን የማያቋርጥ ትንኮሳ እና ያልተቋረጠ የእስራኤል ሠፋሪዎች ጥቃት እንደሚፈጸምባቸው ተናግረው፥ ከመቼውም ጊዜ በላይ የተጣለባቸው ጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደብ ሕይወትን  የማይቻል አድርጎታል ሲሉ አባ ኢብራሂም ፋልታስ ተናግረዋል።

በቅርቡ በደማስቆ ቤተ ክርስቲያን ላይ የተፈፀመው ጥቃት እና ያደረሰው እልቂት በታይቤህ እና በዌስት ባንክ እየሆነ ያለውን ነገር 'የሃይማኖት ጦርነት' ማለት እንደማይቻል የተናገሩት አባ ኢብራሂም ፋልታስ፥ የተቀደሱ ሥፍራዎች ሲጣሱ እና በአመጽ ሲረከሱ ማየት እጅግ እንደሚያሳዝን ገልጸው፥ ከሁሉም በላይ የንጹሃን እና መከላከያ የሌላቸውን የሰው ልጆች ሕይወት ከአደጋ መከላከል እና መጠበቅ አለብን ብለዋል።

በቅድስት ሀገር እየተፈጸመ ያለው ነገር አሳሳቢነት በሚገባ ተመዝግቧል ያሉት አባ ኢብራሂም ፋልታስ፥ ከአካባቢው የሚወጡ ምስሎች እና ዘገባዎች አስደንጋጭ እና የሚያስቆጡ መሆናቸውን ተናግረው፥ ሁላችንም በቅርብ ጊዜ የተካሄዱት ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ይህንን ሁኔታ እንደሚያስቆሙ ተስፋ ብናደርግም ነገር ግን ምንም አለማምጣቱን ገልጸው፥ ዓለም አቀፍ አካላት እየጨመረ የመጣውን የሞት ቁጥር ለማስቆም አቅም የሌላቸው እንደሚመስሉ እና የጋራ ሰብዓዊነታችን ውድቀት ለማጉላት ብቻ መሰብሰባቸውን ተናግረዋል።

“ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚፈልገው ሃላፊነት እንደጎደለው ያሳያል” ያሉት አባ ኢብራሂም ፋልታስ፥ ማኅበረሰቡ ብዙውን ጊዜ በራስ ፍላጎት እና በግብዝነት የተሞላ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

“የሰላም ድርድሮች በተስፋ እና በብስጭት መካከል ይገኛል” ያሉት አባ ኢብራሂም ፋልታስ፥ “የሚቀርበው የተኩስ አቁም ጥሪ በአስቸኳይ ሁከትን ለማስቆም እና ከዚህ በፊት ከመጠን በላይ በተሰቃዩት ሰዎች ላይ የበለጠ መከራ እንዳይደርስባቸው ማድረግ አለበት” ብለው፥ ረሃብ እና ጥማት ይብቃ!” ያሉት አባ ኢብራሂም ፋልታስ፥ አንድን ሕዝብ በገዛ ምድሩ ወደ ጥግ እንዲወጣ የማድረግ ዓላማ እንዲቆም አሳስበዋል።

በአረብኛ “ታይቤህ” የሚለው ቃል “መልካም” ማለት እንደሆነ የተናገሩት አባ ኢብራሂም ፋልታስ፥  ሙሉ በሙሉ ክርስቲያን ማኅበረሰብ በሚገኝበት የታይቤህ መንደር ጥሩ መልዕክት እንደሚመጣ ያላቸውን ተስፋ በመግለጽ፥ አንድነትን እና ሰላምን በቅድስት ሀገር ለሚኖሩ ሕዝቦች በሙሉ ተመኝተዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደባ ምድር የሚገኙ ክርስቲያኖች በቁጥር አናሳ እንደሆኑ እና የቤዛውን ተስፋዎች ከሁለት ሺህ ዓመታት በላይ ይዘው መጓዛቸውን የገልጹት አባ ኢብራሂም ፋልታስ፥ የታይቤህ አካባቢ ለሁሉም ክፍት፣ እንግዳ ተቀባይ እና በሰላም ንጉሥ ምድር ውስጥ በሰላም አብሮ የመኖር ተስፋ መሆኗን አስረድተዋል።

 

 

 

15 Jul 2025, 17:17