የእስራኤል የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች እስራኤል በጋዛ የዘር ማጥፋት እየፈጸመች ነው ማለታቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የእስራኤል ጦር በጋዛ እያካሄደ በሚገኘው ወታደራዊ ዘመቻ ወቅት ሲተገብራቸው በነበሩት ተግባራት ብዙ ውዝግብ እያስነሳ ስለነበር ‘የዘር ማጥፋት’ የሚለው ቃል በአሁኑ ወቅት በእስራኤል ውስጥ እና በእስራኤላዊያን አይሁዶች ዘንድ እንኳን ሳይቀር በተደጋጋሚ እየተነሳ የሚገኝ ቃል ሲሆን፥ ሰኞ ማለዳ ሁለት ስመ ጥር የእስራኤል የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እስራኤል ጋዛ ውስጥ በፍልስጤማውያን ላይ የዘር ማጥፋት እየፈጸመች እንደሆነ ገልጸዋል።
'ቤትሰሌም' እና 'ፊዚሻን ፎር ሂውማን ራይትስ' የተሰኙት በእስራኤል ተቀማጭነታቸውን ያደረጉ የሰብዓዊ መብት ተቋማት የጋዛን ጦርነት አስመልክቶ ባወጡት ሪፖርት እስራኤል በፍልስጤም ሕዝብ ላይ እየፈጸመችው ያለው ድርጊት በዘር ማጥፋት የሚፈረጅ ነው ብለዋል።
ሁለቱ ተቋማት በጥንቃቄ እና በሰነድ መልክ የተዘጋጀውን ሪፖርቶቻቸውን ለጋዜጠኞች ይፋ ባደረጉበት ወቅት እንደገለጹት፥ እስራኤል “በጋዛ የፍልስጤም ማህበረሰብን ለማጥፋት የሚሰራ የዘር ማጥፋት አገዛዝ መዘርጋቷን” ገልጸዋል።
በእስራኤል ውስጥ መቀመጫቸውን ለአስርት ዓመታት ያደረጉት እና በንቁ ተሳትፏቸው የሚታወቁት ተቋማቱ በጋራ ባወጡት መግለጫ "ወንጀሎች በአስቸኳይ እንዲቆሙ ጥሪ ከማድረግ በተጨማሪ፤ በዚህ የጨለማ ወቅት ድርጊቶችን በስማቸው መጥራት መሠረታዊ ጉዳይ ነው" ብለዋል።
‘ቤትሰሌም’ ተብሎ የሚጠራው ተቋም ከ 1981 ዓ.ም. ጀምሮ እስራኤል በያዘቻቸው የፍልስጤም ግዛቶች ውስጥ የፈፀመችውን የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ሪፖርት ያደረገ ሲሆን፥ ይህ ድርጅት በተቋሙ ውስጥ የህግ ባለሙያዎችን፣ ጋዜጠኞችን እና የእስራኤል ፓርላማ አባላትን ያካተተ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ነው።
“ይህ ለእኛ በጣም አሳዛኝ ጊዜ ነው” ያሉት የቤትሰሌም ዋና ዳይሬክተር ዩሊ ኖቫክ፥ በየቀኑ እየሆነ ላለው ነገር እማኝ የሆኑት እና በዚህ አከባቢ የሚኖሩት እስራኤላውያን እና ፍልስጤማውያን በተቻለ መጠን እውነቱን በግልፅ የመናገር ግዴታ እንዳለባቸው አሳስበው፥ ‘እስራኤል በፍልስጤማውያን ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈፀመች’ ነው ብለዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ አክራሪው የቀኝ ዘመም መንግስት ሃማስ መስከረም 26 በእስራኤል ላይ ባደረሰው አሰቃቂ ጥቃት ምክንያት የተፈጠረውን ፍርሃት የፍልስጤም ህዝብን ከጋዛ የማባረር አጀንዳ ለማራመድ እየተጠቀመበት ይገኛል በማለት አብራርተዋል።
በጋዛ ሰርጥ ውስጥ ስላለው ሁኔታ በጤና ላይ ያተኮረ ዝርዝር የሕግ ትንታኔ ያቀረበው 'ፊዚሻን ፎር ሂውማን ራይትስ' የተባለው ተቋም በበኩሉ ባወጣው 65 ገጽ ሪፖርቱ፥ እስራኤል የጋዛን የጤና አጠባበቅ ሥርዓት "በተሰላ እና ስልታዊ በሆነ መልኩ" ዒላማ ማድረጓን አስታውቋል።
የድርጅቱ ሥራ አስፈፃሚ ጋይ ሻሌቭ መረጃዎቹ የጋዛን የጤና እና የሕይወት አድን ሥርዓቶች ሆን ተብሎ ስልታዊ በሆነ መንገድ እንዲወድሙ መደረጉን የሚያሳይ እንደሆነ ጠቁመው፥ ለእነዚህም ማሳያዎቹ በሆስፒታሎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች፣ የሕክምና እርዳታዎች ክልከላ፣ የጤና ባለሙያዎች ላይ የተፈጸሙ ግድያዎች እና እስሮች” እንደሆኑ በአጽንኦት አመላክተው፥ “እውነትን ከመናገር ግዴታ ራሳችንን ነፃ ማድረግ አንችልም” ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ሁለቱም ድርጅቶች የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለሁኔታው የሰጠውን አነስተኛ ትኩረት አውግዘዋል።
በጋዛ የተካሄደውን የእስራኤል ወታደራዊ ዘመቻ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተብሎ መፈረጁ ባለፉት ወራት ከፍተኛ ውዝግብ ማስነሳቱን የሚታወቅ ሲሆን፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ያነሱት ተመሳሳይ ስጋት ከእስራኤል እና በምዕራብ ሃገራት ካሉ የአይሁድ ማህበረሰቦች አባላት ከባድ ትችት እንደደረሰበት ይታወሳል።
‘ላ ኦዘርቫቶሬ ሮማኖ’ የተባለው የጣሊያን ጋዜጣ መጋቢት 2 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣው ጽሁፉ ለእስራኤል የሲቪል ማህበረሰብ አባላት ድምጽ በመስጠት ጉዳዩን አስቀድሞ ገልፆ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፥ በዚህም ወቅት የኢየሩሳሌም የዕብራይስጥ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ምሁር የሆኑት ሊ መርዶክዮስ በጋዛ ውስጥ እየተካሄደ ያለው ተግባር የዘር ማጥፋት ወንጀል መሆኑን በህግ አስደግፈው በማቅረብ አረጋግጠዋል።
በተመሳሳይ መልኩ የሥነ ልቦና ባለሙያ የሆኑት ሲቪያ ፔሬስ ዋልደን በጋዛ ሰርጥ በእስራኤል ጦር የተፈፀመውን ከባድ ወንጀል በማውገዝ የዘር ማጥፋት የሚለውን ቃል መጠቀማቸው ከፋፋይ ሊሆን እንደሚችል እና ግጭቱን በጽንፈኝነት አይን ማየቱን ሊያጠናክር እንደሚችል ጠቁመዋል።