ፈልግ

በደቡብ ኮርዶፋን ግዛት የተጠለሉ የካርቱም ከተማ ተፈናቃዮች  በደቡብ ኮርዶፋን ግዛት የተጠለሉ የካርቱም ከተማ ተፈናቃዮች  

በሱዳን ሰሜን ኮርዶፋን በተፈጸመ ጥቃት 35 ሕጻናት መገደላቸው ተነገረ

በሱዳን ሰሜናዊ ኮርዶፋን ግዛት ባራ አቅራቢያ በሚገኙ ማኅበረሰቦች ላይ በተፈጸመ ጥቃት 35 ሕጻናትን እና ሁለት ነፍሰ ጡር ሴቶችን ጨምሮ ከ450 በላይ ሰላማዊ ሰዎች እንደተገደሉ፣ በደርዘን የሚቆጠሩ እንደቆሰሉ እና በርካቶች የደረሱበት አሁንም እንዳልታወቀ ተነግሯል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሱዳን እየተካሄደ ባለው የእርስ በርስ ጦርነት ባለፈው ቅዳሜ እና እሁድ በሀገሪቱ ሰሜን ኮርዶፋን ግዛት ውስጥ በሚገኙ በርካታ ማኅበረሰቦች ላይ በተፈጸመ ወረራ ከ450 በላይ ንፁሃን ዜጎች ተገድለዋል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የአስቸኳይ ጊዜ ጠበቆች እንደገለጹት፥ ድርጊቱን የፈጸሙት በሱዳን የሚገኘው የፈጥኖ ደራሽ ሃይል ታጣቂዎች መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ዳይሬክተር ወ/ሮ ካትሪን ራስል፥ በሱዳን ያለውን ሁኔታ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ሐምሌ 9/2017 ዓ. ም. መግለጫ አውጥተዋል።

“ጥቃቶቹ አስፈሪ ናቸው” ሲሉ የገለጹት ዳይሬክተሯ፥ “እነዚህ ጥቃቶች የሰው ሕይወት፣ የዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ሕግ እና የሰው ልጅ መሠረታዊ ሥርዓቶች መባባስን የሚያመላክቱ ናቸው” ሲሉ ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት ፈንድ (ዩኒሴፍ)፥ “ጥቃቱ ሲቪሎችን በተለይም ሕጻናትን በፍጹም ዒላማ ሊያደርጋቸው አይገባም” ብሎ፥ ለቤተሰቦቻቸው እና በቅርብ ጊዜ በተከሰቱት አደጋዎች ለተጎዱት የተሰማውን ሐዘን ገልጿል።

በሰሜን ኮርዶፋን ሕዝብ ላይ የሚፈጸሙ ጥሰቶች በሙሉ በገለልተኛ አካል እንዲመረመሩ እና “ጥሰቶችን የሚፈጽሙትም ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባል” ሲል አሳስቧል።

በሱዳን የተፈፀመው ግፍ ታሪክ

ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በሰሜን ኮርዶፋን ያለው ሁኔታ እየተባባሰ በመምጣቱ መፈናቀል፣ የሲቪሎች ሰለባነት እና የሰብዓዊ ተደራሽነት ገደቦች መጨማራቸው ታውቋል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ሚያዝያ ወር 2023 ዓ. ም. የፈጥኖ ደራሽ ሃይል ታጣቂዎች ወደ ኮርዶፋን ግዛት ከተስፋፉት የሱዳን ጦር ኃይሎች (ኤስኤፍኤ) ጋር የእርስ በርስ ጦርነት የጀመረ ሲሆን፥ ባለፈው ቅዳሜ እና እሁድ የተፈፀመው ጥቃት ካለፉት ዓመታት ከተፈጸሙት መካከል አንዱ እንደሆነ ታውቋል።

በእነዚህ ጥቃቶች ምክንያት የሰሜን ኮርዶፋን ሕጻናት ደህንነት በእጅጉ እያሰጋ እንደሚገኝ ሲነገር፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ እስከ 2024 ዓ. ም. ድረስ በሱዳን ውስጥ በህፃናት ላይ ከተፈጸሙ ጥሰቶች መካከል 6 በመቶው የሚሆነው በሰሜን ኮርዶፋን ውስጥ መሆኑ ታውቋል።

ሕጻናትን መግደል እና አካል ማጉደልን ጨምሮ እነዚህ ጥሰቶች ወደ ጾታዊ ጥቃት እና አፈና የዘለቁ ሲሆን፥ በያዝነው ዓመት ውስጥ እነዚህ አዝማሚያዎች እየጨመሩ መምጣታቸው ይበልጥ አሳሳቢ ሆነዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት ፈንድ (ዩኒሴፍ)፥ “ይህ በሕጻናት ላይ የሚፈጸም ጥቃት ሊታሰብ የማይችል እና ቶሎ መቆም ያለበት ነው” ሲል ገልጿል።

የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ዳይሬክተር ወ/ሮ ካትሪን ራስል በመግለጫቸው፥ በግጭቱ የሚሳተፉ አካላት በሙሉ ሕጻናን ጨምሮ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚፈጽሙትን ማንኛውንም ዓይነት ተጨማሪ ጥቃት እንዲያቆሙ ጠይቀዋል።

 

17 Jul 2025, 13:11