ዩኒሴፍ፡ ግጭቶች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህፃናትን ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ ወይም እንዲገደሉ አድርጓል ማለቱ ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በያዝነው ዓመት ብቻ በግምት 45 ሚሊዮን ህጻናት በመካከለኛው ምስራቅ እና ሰሜን አፍሪካ (MENA) የሰብአዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው መረጃዎች የሚያሳዩ ሲሆን፥ ይህም አሃዝ ባለፉት አምስት ዓመታት ከታዩት 41 በመቶ መጨመሩ ተነግሯል።
ዩኒሴፍ ላለፉት 70 ዓመታት በመካከለኛው ምስራቅ እና ሰሜን አፍሪካ ሃገራት ውስጥ የሚገኙ ጉዳት የደረሰባቸውን ህጻናት እና ቤተሰቦችን ለመርዳት ጥረት ሲያደርግ እንደነበረ የተነገረ ሲሆን፥ ሆኖም ግን በአሁኑ ወቅት ባጋጠመው ከባድ የገንዘብ እጥረት ምክንያት ሥራዎቹ ለአደጋ የተጋለጡ መሆናቸውን አስጠንቅቋል።
ቀውሶቹን ተከትሎ ይፋ የተደረጉ አሃዞች
የመካከለኛው ምስራቅ እና ሰሜን አፍሪካ ክልል በአሁኑ ጊዜ የእስራኤል-ፍልስጤም ግጭት፣ የሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት እና የየመን ጦርነትን ጨምሮ በርካታ የተለያዩ ግጭቶች እያጋጠሙት እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን፥ በአካባቢው ከሚኖሩት ሁለት ህፃናት አንዱ በእነዚህ ግጭቶች በተጠቁ ሀገራት ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፥ በአጠቃላይ ወደ 100 ሚሊዮን የሚጠጉ ህጻናት ለጥቃት የተጋለጡ መሆናቸው የዩኒሴፍ መረጃ ያመላክታል።
ከ 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ከ12 ሚሊዮን በላይ ህጻናት በግጭቶቹ ምክንያት ከመኖሪያ ቤታቸው ለመፈናቀል የተገደዱ ሲሆን፥ ከ 40,000 በላይ የሚሆኑት ደግሞ መቁሰላቸው ወይም ቋሚ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው እንዲሁም 20,000 የሚሆኑት ደግሞ መገደላቸው ይፋ ተደርጓል።
ተግባራዊ እርምጃ እንዲወሰድ የተደርገ ጥሪ
በመካከለኛው ምስራቅ እና ሰሜን አፍሪካ ሃገራት የዩኒሴፍ ክልላዊ ዳይሬክተር ኤድዋርድ ቤይ-ግደር እንደተናገሩት ‘በክልሉ በተፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት በየአምስት ሰከንድ የአንድ ሕፃን ህይወት እንደሚያልፍ’ ጠቁመው፥ ‘ለህፃናት ሲባል ግጭቶችን ማቆም አማራጭ ሳይሆን በአስቸኳይ መፈጸም የሚገባው፣ የሞራል ግዴታ እና ለተሻለ ጊዜ ብቸኛው መንገድ መሆኑን’ በአጽንዖት አብራርተዋል።
ዩኒሴፍ የህፃናት ስቃይ እንዲያበቃ በክልላዊ ግጭቶች ውስጥ የሚሳተፉ አካላት ሁሉ እርስ በእርስ እንደ ጠላት መተያየትን እንዲያቆሙ ብሎም የዓለም አቀፍ እና የሰብአዊ መብት ህጎችን እንዲያከብሩ አሳስበው፥ የሰላም ኃይልን እና የሕፃናት ጥበቃን እንዲያበረታቱ በግጭቶቹ ላይ ተጽእኖ ላላቸው አጎራባች ክልሎች ጥሪ አቅርበዋል።
ዩኒሴፍ ከዚህም በተጨማሪ ለጋሾች በመካከለኛው ምስራቅ እና በሰሜን አፍሪካ ላሉ ተጋላጭ ህጻናት ሲሉ ድጋፋቸውን እንዲቀጥሉ ወይም እንዲያሳድጉ፥ እንዲሁም በአካባቢው ለአደጋ የተጋለጡ ወጣቶችን ለመጠበቅ አዳዲስ ለጋሾች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቋል።
የገንዘብ ድጋፍ እና የሰብአዊ ፍላጎቶች
የተባበሩት መንግስታት የህጻናት ኤጀንሲ በመካከለኛው ምስራቅ እና ሰሜን አፍሪካ ክልል ውስጥ በተከሰተው ከባድ የገንዘብ እጥረት ምክንያት የተለመደው ሥራውን ማከናወን አለመቻሉን የገለጸ ሲሆን፥ ሶሪያ የ78 በመቶ የገንዘብ ድጋፍ ክፍተት እንዳሳየች እንዲሁም ፍልስጤም በአውሮፓዊያኑ 2025 ዓ.ም. የገንዘብ ድጋፍ ጥያቄዋ ላይ 68 በመቶ ክፍተት እንዳላት በመግለጽ፥ እ.አ.አ. በ 2026 ዓ.ም. ከ 20-25 በመቶ የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ እንደሚቀንስ ስለሚገመት የዩኒሴፍ ፕሮግራሞች በከባድ ጫና ውስጥ እንደሚወድቁ ይፋ ተደርጓል።
በቅርብ ጊዜያት እየታዩ በሚገኙት የገንዘብ ድጋፍ ቅነሳዎች ምክንያት ለሰብአዊ ድጋፍ የሚውል 370 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ አደጋ ላይ እንደሆነ የተነገረ ሲሆን፥ እነዚህ ቅነሳዎች ዩኒሴፍ ለህጻናት እና ለተቸገሩ ቤተሰቦችን ጠቃሚ ግብአቶችን ለሚያቀርብበት ፕሮግራሞቹ ከባድ ስጋት እንደሆኑ ገልጿል።
እነዚህ ፕሮግራሞች ለተጎጂዎች ከሚያቀርቡት አገልግሎቶች መካከል ከፍተኛ የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን መቅረፍ፣ ለተጎጂዎች ንፁህ ውሃ ማቅረብ እና ገዳይ በሽታዎችን ለመከላከል የሚደረጉ ክትባቶች ዋና ዋናዎቹ እንደሆኑ ተገልጿል።