ፈልግ

የቻድ ሀይቅ ከሰማይ ላይ ሲታይ የቻድ ሀይቅ ከሰማይ ላይ ሲታይ   (AFP or licensors)

በሰሜን ናይጄሪያ ረሃብ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ መሆኑ ተነገረ

ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ በሰሜናዊ ምስራቅ ናይጄሪያ ከ 3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለረሃብ መጋለጣቸውን ይፋ ያደረገ ሲሆን፥ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በበኩሉ በአጠቃላይ የሃገሪቱ ክፍል 30 ሚሊዮን ሰዎች ለአደጋ ሊጋለጡ እንደሚችል አስጠንቅቋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

እንደ ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ መረጃ ከሆነ በሰሜን ምስራቅ ናይጄሪያ ከ3.3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በአሁኑ ወቅት የምግብ ዋስትና እጦት እንዳጋጠማቸው የተገለጸ ሲሆን፥ አብዛኛዎቹ አርሶ አደሮች በክልሉ በተከሰተው የጸጥታ ችግር ምክንያት ዋነኛ መተዳደሪያቸው የነበረውን መሬታቸውን ጥለው እንደሄዱ እና ዓሣ አጥማጆችም ሳይቀር የችግሩ ሰለባ መሆናቸው ተገልጿል።


የቫቲካን የዜና ወኪል የሆነው ፊደስ እንደዘገበው በአከባቢው በተከሰተው የጸጥታ ችግር ምክንያት እረኞች ከብቶቻቸውን ወደ ግጦሽ ቦታ መውስውድ እንዳይችሉ ማድረጉን እና አሳ አጥማጆችን ደግሞ የቻድ ሃይቅ እንዲሁም ኒጀር እና ታራባ ወደመሳሰሉ ዋና ዋና ወንዞች እንዳይደርሱ ማድረጉን በመግለጽ፥ በሰሜናዊ ናይጄሪያ ከፍተኛ ጥፋት በማድረስ ላይ በሚገኙት ታጣቂ ቡድኖች እና ሽፍቶች እንቅስቃሴ ምክንያት ሁለቱም ቡድኖች ላይ ከፍተኛ ስቃይ እየደረሰባቸው እንደሚገኝ ዘግቧል።

የተባበሩት መንግስታት የምግብ እና ግብርና ድርጅት (FAO) በበኩሉ በዚህ የዝናብ ወቅት ማለትም ከመከሩ በፊት ባሉት ወራት ከ30 ሚሊዮን በላይ ናይጄሪያውያን ለምግብ እጦት ሊጋለጡ እንደሚችሉ ሲያስጠነቅቅ፥ የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል አጠቃላይ ችግሩን ለመፍታት አሁን ላይ እየተደረገ ያለው ጥቂት የእርዳታ ጥረት ብቻ በቂ ላይሆን እንደሚችል አስጠንቅቋል።

በናይጄሪያ ታጠቂ ቡድኖች በሚያደርሱት የማያቋርጥ ጥቃት ምክንያት የሚመጣው የምግብ ዋስትና እጦት ጥልቅ እና መፍትሄ ያልተገኘለት ችግር ምልክት መሆኑን የገለጸው የቀይ መስቀል ድርጅት፥ ከዚህም በተጨማሪ ቀውሱን የሚያባብሰው የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ በመላ አገሪቱ የውስጥ መፈናቀልን እያስከተለ እንደሆነ ገልጿል።

ናይጄሪያ በሰሜን ምዕራብ ድርቅ፣ በምስራቅ ደግሞ የጎርፍ መጥለቅለቅ ያጋጠማት ሲሆን፥ እነዚህ ሁለት ክስተቶች የሀገሪቱን የእርሻ መሬቶች ማውደማቸውን ከአከባቢው የሚወጡ መረጃዎች ያመላክታሉ።

13 Aug 2025, 14:25