ፈልግ

በፔሩ የሚገኙ የማሽኮ ፒሮ ጎሳዎች በፔሩ የሚገኙ የማሽኮ ፒሮ ጎሳዎች  

በዓለም አቀፍ የነባር ተወላጆች ቀን ላይ ከሌላው ተለይቶ የመኖር መብት ሊከበር እንደሚገባ ተገለጸ

በፔሩ የዓለም አቀፍ የአገሬው ተወላጆች መብቶች ቀን በተከበረበት ወቅት ተወላጆች ከሌላው ዓለም ተለይተው የመቆየት መብታቸው ሊከበር እንደሚገባ በአጽንዖት የተገለጸ ሲሆን፥ ከዚህ ጋር ተያይዞ የአማዞን ጫካ የማይታዩ ጠባቂዎች ተብለው የሚጠሩት በፔሩ የሚገኙ የማሽኮ ፒሮ ማህበረሰቦች በአሁኑ ወቅት በአምራች ኢንዱስትሪዎች ምክንያት ስጋት ውስጥ እንደሚገኙ ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የአገሬው ተወላጆች የሚኖሩባቸው መሬቶች ወደር የለሽ የብዝሀ ሕይወት ሀብት እንዳላቸው የተነገረ ሲሆን፥ በአሁኑ ጊዜ ከ470 ሚሊዮን በላይ ነባር ተወላጆች በ90 ሃገራት ውስጥ እንደሚኖሩ ተገልጿል።

በየዓመቱ ነሃሴ 3 ከሚከበረው የዓለም አቀፍ የዓለም የተወላጆች ቀን ዓላማዎች መካከል የአካባቢ ጥበቃ አንዱ ሲሆን፥ በዚህ ዓመት የተከበረው የነባር ተወላጆች መብቶች ቀን “የአገሬው ተወላጆች እና ሰው ሰራሽ አስተውሎት ወይም አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፡ መብቶችን መጠበቅ እና መጪውን ጊዜ መቅረጽ” የሚል ጭብጥ ላይ እንደሚያተኩር፥ ይህም ማለት የብዝሀ ህይወትን ለመጠበቅ እና የአየር ንብረት ለውጥን ተፅእኖ ለመቅረፍ የሀገር በቀል ዕውቀት ያለውን ጥቅም መገንዘብ እንደሚገባ ለማጉላት እንደሆነ ተነግሯል።

በፔሩ የሚገኙት የማሽኮ ፒሮ ጎሳዎች
በፔሩ የአማዞን ጫካ ውስጥ በላስ ፒድራስ እና በአልቶ ማድሬ ደ ዳዮስ ወንዞች አቅራቢያ የሚኖሩት የማሽኮ ፒሮ ጎሳ አባላት ማንነታቸውን፣ እውቀታቸውን እንዲሁም በባህል እና በተፈጥሮ መካከል ያለውን ደካማ ሚዛን ለመጠበቅ ከዘመናዊው ዓለም ተለይተው መቆየትን የመረጡ ሲሆን፥ ድምፃቸውንም የሚያሰሙት በክልሉ የሚገኙ ተወላጆችን ከሚወክለው ‘ፌናማድ’ በተባለው ተቋም በሚወጡ ሪፖርቶች እንደሆነ ተገልጿል።

የማሽኮ ፒሮ ተወላጆች ‘ፒያቺ’ ተብለው ከሚጠሩት በፈቃደኝነት ተገልለው ከሚኖሩ ጎሳዎች መካከል አንዱ ሲሆኑ፥ ብዙ ጊዜ ድንገተኛ እና አስፈላጊ ያልሆኑት ከውጪው ዓለም ጋር የሚደረጉ ግንኙነቶች ውጤታቸው አስከፊ፣ ሁለቱንም ከባድ የጤና አደጋዎችን እና የባህል መበረዝን ሊያመጡ እንደሚችሉ ይነገራል።

አስጊ የህልውና አደጋ
ፔሩ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ቢያንስ ለ25 የሃገሬው ተወላጅ ቡድኖችን በይፋ እውቅና የሰጠች ሲሆን፥ እ.አ.አ. ከ 2006 ዓ.ም. ጀምሮ የተወሰኑ የክልል ይዞታዎችን ከመፍጠር ጎን ለጎን ጣልቃ ያለመግባት መብት በማጽደቅ አበረታች ሥራዎች የተሰሩ ቢሆንም፥ ነገር ግን እስካሁን ከተጠየቁት 25 ሥፍራዎች ውስጥ 5ቱ ብቻ በይፋ የተቋቋሙ ሲሆን ይህም የጥበቃ ስርዓቱን ድክመቶችን ያሳያል ተብሏል።

‘አይዲሴፕ’ የተሰኘው በፔሩ የሚገኝ አንድ የሰብአዊ መብት ተቋም በሃገሪቷ ውስጥ አዳዲስ መጠባበቂያዎችን ለመፍጠር የታዩ መዘግየቶችን በተደጋጋሚ የተቸ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ ያሉትን ጥበቃዎች ሊያዳክሙ ከሚችሉ የህግ እርምጃዎች መቆጠብ እንደሚያስፈልግ አስጠንቅቋል።

በተለየ ሁኔታ የማሽኮ ፒሮ ጎሳዎች ወደ ክልሎቻቸው እየመጡ ደኖቻቸውን ለሚያወድሙ እና ለማዕድን አውጪዎች በጩኸት እና በቀስት ተቃውሟቸውን የገለጹ ሲሆን፥ ይህ ድርጊታቸው የበርካታ አሥርተ ዓመታት ግጭት፣ ባርነት እና በሽታ የወለደው ራስን የመከላከል ምላሽ ነው ተብሏል። እነዚህ ጎሳዎች በአሁኑ ወቅት በአደን፣ አሳ በማጥመድ እና ምግቦችን በመሰብሰብ ከጫካው ጋር ተስማምተው እና ጥፋት ሳያደርሱ በወንዞች ዳርቻ ከወቅቶች ጋር እየተንቀሳቀሱ እንደሚኖሩ ተነግሯል።

አምራች ኢንዱስትሪዎች ስጋት መሆናቸው
ትላልቅ የማምረቻ ኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች የነባር ማበረሰቦች ይዞታ እና አከባቢ ላይ ጉዳት ከሚያደርሱ ነገሮች ውስጥ አንዱ ስጋት እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፥ ‘አይዲሴፕ’ የተባለው የሰብአዊ መብት ተቋም ይህን አስመልክቶ ከነባር ማህበረሰቦች ጋር ውይይት ሳይደረግ ከደን መጨፍጨፍ የሚፈጠረውን ልቀትን ለመቀነስ የወጡ ዓለም አቀፍ እቅዶችን የመሳሰሉ ጫና የበዛባቸው የአካባቢ ፕሮግራሞች መተግበራቸውን በማውገዝ፥ ከአካባቢ ጥበቃ የሽምገላ ውይይቶች በስተጀርባ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች እና “አካባቢያዊ ቅኝ ግዛት” የመሳሰሉ ሸፍጦች እንዳሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ብዙ ጊዜ እንደሚያስጠነቅቁ ገልጿል።

“የተገለሉ ህዝቦች ስምምነቶችን መፈረም ወይም መስማማት አይችሉም” ያለው ተቋሙ፥ ይህም በመሆኑ ማህበረሰቡ ጠንካራ ጥበቃ እንደሚያስፈልጋገው በመግለጽ፥ ለሃያ ዓመታት ያህል ሲጠበቅ የነበረው የመጠባበቂያ አከባቢዎች ምስረታ ያለማቋረጥ መራዘሙ እነዚህን ማህበረሰቦች ለከባድ የጤና እና የባህል አደጋዎች ማጋለጡን ይፋ አድርጓል።

አዲሱ የ‹ተፅእኖ ፈጣሪዎች ቱሪዝም› አደጋ
ከታሪካዊ እና ተቋማዊ ስጋቶች በተጨማሪ አዲስ የመጣው የዲጂታል-ዘመን ሌላ ተግዳሮት መሆኑን ያነሳው ተቋሙ፥ ዛሬ ላይ ከሌላው ህዝብ ጋር ግንኙነት ከሌላቸው ሰዎች ጋር ያለው መማረክ፤ ምስሎች፣ ቪዲዮዎች እና የግል ጉዳይ የሆኑ ልጥፎች ጎልተው ወደ ሚወጡበት ማህበራዊ ሚዲያ የተዛወሩ ሲሆን፥ አንዳንድ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች በቀጥታ ከነባር ማህበረሰቡ ጋር መገናኘትን እንደሚፈልጉ እና ከአገሬው ተወላጆች ጋር የሚያደርጉትን ቆይታ ለተከታዮቻቸው ግብአት አድርገው እንደሚጠቀሙበትም ተገልጿል።

ከዚህም ጋር በተያያዘ እንደ ‘ሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል’ ያሉ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሰዎች ሳይታዩ የመቆየት መብትን የሚጥሱ ምስሎችን ወይም ቪዲዮዎችን እንዳያጋሩ አሳስበዋል።

አደጋው በተጠቃሚዎች አመክንዮ ብቻ የሚመራውን ‘ውድ ሀብት ፍለጋ’ እያቀጣጠለ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ ማንኛውም ያልተፈለገ ግንኙነት አደጋ ሊያመጣ እንደሚችል፥ ለተለመዱ በሽታዎች የመከላከል አቅም ከሌለ በየወቅቱ የሚነሳው ጉንፋን እንኳን ወደ ገዳይነት እንደሚለወጥ፥ ብሎም ጉዳቱ አካላዊ ብቻ ሳይሆን ማንኛውም ጣልቃ ገብነት ለሺህ ዓመታት የዘለቀውን የባህል ሚዛን ሊያፈርስ እንደሚችል ተገልጿል።

በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለው ተግዳሮት የሰብአዊ መብት ጥበቃን ከተፈጥሮ ራዕይ ጋር አንድ ለማድረግ አለመቻል እንደሆነ የተነገረ ሲሆን፥ ለመገለል መብት እውቅና መስጠት የመስማት፣ የመከባበር እና የመጠበቅ ተግባር እንደሆነ፥ ብሎም ባህላዊ ተመሳሳይነትን እንደሚከላከል እና በዝምታም ቢሆን የመኖር ሙሉ መብት እንዳለን ይገልፃል ተብሏል።

11 Aug 2025, 14:40