ፈልግ

በሰሜን ዳርፉር ግዛት በተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ ምክንያት ከ640,000 የሚበልጡ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት ለችግር ተጋልጠዋል ሲል በቅርቡ የወጣው የዩኒሴፍ ሪፖርት አመልክቷል በሰሜን ዳርፉር ግዛት በተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ ምክንያት ከ640,000 የሚበልጡ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት ለችግር ተጋልጠዋል ሲል በቅርቡ የወጣው የዩኒሴፍ ሪፖርት አመልክቷል  (AFP or licensors)

በሱዳን ከ600,000 በላይ ህጻናት በግጭቱ ምክንያት ከፍተኛ ስጋት ውስጥ መሆናቸው ተገለጸ

የተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት - ዩኒሴፍ አዲስ ባወጣው ሪፖርት በሱዳን ውስጥ የሚገኙ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ህጻናት በሃገሪቱ ተጠናክሮ በቀጠለው ጦርነት ምክንያት ለምግብ እጦት እና ለኮሌራ በሽታ በከፍተኛ ደረጃ መጋለጣቸውን ይፋ አድርጓል።

   አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ከሁለት ዓመታት በላይ ባስቆጠረው ጥቃት፣ ውድመት እና መፈናቀል በኋላ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና ሌሎች የእርዳታ ድርጅቶች እንደገለጹት ሱዳን በዓለም ትልቁ የሰብአዊ ቀውስ ያለባት ሃገር ሆና መቀጠሏን ገልጸዋል።

በተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) በቅርቡ ያወጣው ሪፖርት እንደሚያመላክተው በሰሜን ዳርፉር ግዛት በተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ ምክንያት ከ640,000 የሚበልጡ ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ህጻናት ለአደጋ መጋለጣቸውን ይፋ ያደረገ ሲሆን፥ በሱዳን አምስቱ የዳርፉር ግዛቶች እስከ ሀምሌ 30 ድረስ ቢያንስ 80 ሰዎች በኮሌራ ህይወታቸውን እንዳጡ፣ ከ 2,100 በላይ ሰዎች ደግሞ በበሽታው መያዛቸውን አረጋግጧል።

የኮሌራ በሽታዎች ቁጥር መጨመር
ዩኒሴፍ ባወጣው መግለጫ ከሰኔ 21 ጀምሮ በሰሜን ዳርፉር ግዛት በታዊላ ከተማ ብቻ 20 ሰዎች በወረርሽኙ ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን፥ ከ 1 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ በበሽታው መያዛቸውን ገልፆ፥ ከእነዚህ ውስጥ 300 ያህሉ ሕፃናት ሲሆኑ ቢያንስ 20 ሰዎች መሞታቸውን ይፋ አድርጓል።

ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ተፈናቃዮችን ተቀብላ እያስተናገደች ለምትገኘው የታይላ ከተማ ይህ የኮሌራ ወረርሽኝ ተጨማሪ ስጋት እንደፈጠረባት እየተገለጸ ይገኛል።

መጪው ጊዜ አደጋ ላይ ነው
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንዳስታወቀው ከሚያዝያ ወር 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በሰሜን ዳርፉር እየተባባሰ የመጣውን ሁከት ተከትሎ ከ6መቶ40 ሺህ በላይ ህጻናት ለጥቃት፣ ለረሃብ እና ለኮሌራ የተጋለጡ መሆናቸውን አስጠንቅቋል።

በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናዊያን ወደ ታዊላ ከተማ ቢሰደዱም ግጭቶች አሁንም ድረስ ተጠናክሮ መቀጠላቸው እና በአከባቢው ያለው ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ አስጊ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፥ የምግብ እጥረት፣ በቂ ያልሆነ ንጹህ ውሃ፣ የመጠለያ ውስንነት እና የበሽታ ስጋት እየጨመረ መምጣቱ ተነግሯል።

ከዚህም ባለፈ በሰሜን ዳርፉር ግዛት ውስጥ የሚገኙ ሆስፒታሎች በቦምብ መደብደባቸው እና በግጭት ቀጠና አቅራቢያ የሚገኙ የጤና አጠባበቅ ተቋማት መዘጋታቸው የተገለጸ ሲሆን፥ በዚህም ምክንያት የሕክምና አገልግሎት ማግኘት በጣም ከባድ መሆኑ፣ ከንጹህ ውሃ እጥረት እና ከንጽህና ጉድለት ጋር በተያያዘ የኮሌራ እና ሌሎች ገዳይ በሽታዎች ስርጭት በተለይም የተፈናቀሉ ሰዎች በብዛት በሚገኙባቸው የተጨናነቁ አካባቢዎች እየተስፋፋ እንደሚገኝ የተባበሩት መንግስታት አረጋግጧል።

እንደ ዩኒሴፍ ሪፖርት መሰረት በቅርብ ጊዜ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት በሰሜን ዳርፉር በከፋ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት የሚሰቃዩ ህፃናት ቁጥር ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በእጥፍ መጨመሩን ያመላከተ ሲሆን፥ ከኮሌራ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት የተዳከሙ ህጻናት ለበሽታ እና ለሞት የተጋለጡ መሆኑን ሪፖርቱ በመግለጽ፣ ‘በአፋጣኝ እና ደህንነቱ በተጠበቀ መንገድ ሕይወት አድን የተመጣጠነ ምግብ፣ የጤና እንክብካቤ እና የንጹህ ውሃ አቅርቦት በአስቸኳይ ካልቀረበ፥ መከላከል የሚቻለው የሕፃናት ሞት እየጨመረ እንደሚሄድ’ አጽንኦት ሰጥቷል።

አስፈላጊ ቁሳቁሶች ህይወትን ሊታደጉ ይችላሉ
በሱዳን የዩኒሴፍ ተወካይ የሆኑት ሼልደን ዬት “ህመሙ ምንም እንኳን መከላከል የሚቻል እና በቀላሉ ሊታከም የሚችል ቢሆንም፥ ኮሌራ በታዊላ እና በሌሎች የዳርፉር አካባቢዎች በፍጥነት በመዛመት የህጻናትን በተለይም የትንንሾችን እና በጣም ተጋላጭ የሆኑትን ህይወት አደጋ ላይ እየጣለ ይገኛል” ብለዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ወረርሽኙን ለማስቆም ከአጋር ቡድኖቻቸው ጋር ሌት ተቀን እየሰራ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን፥ ነገር ግን ‘በአከባቢው ተጠናክሮ በቀጠለው ግጭት ምክንያት በፍጥነት እየጨመሩ የመጡት ፍላጎቶች፣ ማቅረብ ከሚቻለው በላይ እየሆኑ መምጣታቸውን’ ጠቁመው፥ ዩኒሴፍ “ይህን አካሄድ በአስቸኳይ ለመቀልበስ እና የተቸገሩ ህጻናትን ለመድረስ” ደህንነቱ የተጠበቀ እና ክልከላ የሌለበት መንገድ እንዲኖር ጥሪ በማቅረብ፥ “ተጎጂዎቹ ሌላ ተጨማሪ ቀን መጠበቅ አይችሉም” በማለት በአጽንዖት ገልጸዋል።

በሁሉም አቅጣጫዎች እርዳታ ማቅረብ
ዩኒሴፍ በሁሉም አከባቢዎች በግጭቱ ምክንያት ለተፈናቀሉት በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች የጤና፣ የውሃ፣ የንፅህና አጠባበቅ አቅርቦቶችን ሲያቀርብ እንደቆየ የገለጹት ተወካዩ፥ በዩኒሴፍ ለሚደገፉ የውሃ መኪናዎች፣ እድሳት የተደረገላቸው የውሃ ጉድጓዶች እና አዲስ ለተገነቡ የውሃ ማከማቻ ስርዓቶች ምስጋና ይድረሳቸውና በአሁኑ ወቅት በቲዊላ 30,000 ሰዎች ንፁህ፣ ክሎሪን የተቀላቀለበት የመጠጥ ውሃ ማግኘት እንደቻሉ የገለጹ ሲሆን፥ ከዚህም ባለፈ ተቋማቸው በዳባ ናይራ ለሚገኙ 150,000 ቤተሰቦች በቤት ውስጥ ውሃ ማከም የሚያስችላቸው የክሎሪን ታብሌቶችን እና የንፅህና መጠበቂያ ዕቃዎችን ማከፋፈሉን ገልጸው፥ ወረርሽኙን ለማስቆም እና የኮሌራ በሽታ ለመከላከል ቁርጠኛ የሆነው ዩኒሴፍ 1.4 ሚሊዮን በአፍ የሚወሰዱ የኮሌራ ክትባቶችን ለመስጠት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ሱዳን ከሚያዝያ 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በዋናው የሃገሪቱ ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል በተፈጠረ ውጊያ ስትታመስ የቆየች ሲሆን፥ በተባበሩት መንግስታት እና በአካባቢው ባለስልጣናት መረጃ መሠረት ግጭቱ ከ20 ሺህ በላይ ሰዎችን ህይወት መቅጠፉ እና 14 ሚሊዮን ሰዎችን ደግሞ ማፈናቀሉን ይገልፃሉ።

05 Aug 2025, 12:54