ፈልግ

ከእስራኤላዊው ታጋች ኤቪያታር ዴቪድ ቪዲዮ የተወሰደ ምስል ከእስራኤላዊው ታጋች ኤቪያታር ዴቪድ ቪዲዮ የተወሰደ ምስል   (AFP or licensors)

በጋዛ ተይዘው በሚገኙት ረሃብ ያጎሳቆላቸው ታጋቾች ላይ የሚታየው የጦርነት አስፈሪነት

የፍልስጤም ታጣቂዎች በጋዛ ተይዘው የሚገኙት ታጋቾች በረሃብ እየተሰቃዩ መሆናቸውን የሚገልጹ ቪዲዮዎች በዚህ ሳምንት መልቀቃቸውን ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት አሁንም በጋዛ ሰርጥ ታግተው የሚገኙትን ሰዎች ለማስፈታት የሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ለመወያየት አስቸኳይ ስብሰባ እንዳደረገ ተገለጸ።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በጋዛ ታግተው የሚገኙ እና በርሃብ ሰውነታቸው የከሳ ሁለት እስራኤላውያንን የሚያሳይ ቪድዮ መለቀቁን ተከትሎ በጋዛ ሰርጥ ያለው ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፥ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ ለመወያየት ሃምሌ 29 አስቸኳይ ስብሰባ እንዳደረገ ተነግሯል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ሃማስ የእስራኤል ታጋቾች በእስላማዊ ቡድኑ እጅ ውስጥ እንዳሉ የሚያሳዩ ቪዲዮዎችን በመልቀቃቸው “በጣም ተደናግጠዋል” ሲሉ ቃል አቀባዩ ፋርሃን ሃክ የገለጹ ሲሆን፥ “ተቀባይነት የሌለው እና የሰውን ልጅ ክብር መጣስ ነው” በማለት አክለዋል።

ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል በበኩሉ ‘በጋዛ የሚገኙ ሁሉም ታጋቾች በአስቸኳይ እና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መፈታት እንዳለባቸው’ ጥሪ በማቅረብ፥ ነፃነታቸውን የተነፈጉ ሰዎችን የሚያዋርድ ማንኛውም አይነት ድርጊት ሊወገዝ እንደሚገባ በማሳሰብ ቁጣውን ገልጿል።

ርሃብ ያጎሳቆላቸው ታጋቾች
ሰሞኑን የተለቀቁት ቪዲዮዎች በሁለቱ ታጋቾች ላይ በሚታየው አስከፊ ሁኔታ ምክንያት ባለፉት 22 ወራት ውስጥ ከተለቀቁት ቪድዮዎች በብዙ መልኩ እንደሚለይ የተገለጸ ሲሆን፥ የመጀመሪያው ተንቀሳቃሽ ምስል የተለቀቀው ሃምሌ 24 ቀን 2017 ዓ.ም. በጋዛ ሰርጥ በሚንቀሳቀሰው ታጣቂ እስላማዊ ጂሃድ እንደሆነ እና ሮም ብራስላቭስኪ የሚባለው በምስሉ ላይ የሚታየው የ 22 ዓመቱ ታጋች የጎድን አጥንቱ እስከሚታይ ድረስ እጅግ በጣም ከስቶ እና ተዳክሞ፥ በጣም ከመድከሙም የተነሳ መቆም እንደማይችል ሲናገር እንደነበር ይታወሳል።

ሃምሌ 25 ቀን 2017 ዓ.ም. በሃማስ የተለቀቀው ሁለተኛው ቪዲዮ የ24 ዓመቱን ታጋች ኤቪያታር ዴቪድን የሚያሳይ ሲሆን፥ እሱም በጣም የተዳከመ እና በዋሻ ውስጥ የተቀረጸ ይመስላል ተብሏል።

ሁለቱም ቪዲዮዎች የተቀረጹት በማስገደድ እና ግልጽ የሆነ የፕሮፓጋንዳ ዓላማ እንዳላቸው አስተያየት ሰጪዎች የሚናገሩ ሲሆን፥ ሃማስ የኤቪያታር ዴቪድን ቪዲዮን ተከትሎ በሰጠው መግለጫ ሆነ ብሎ ታጋቾችን እያስራበ ነው የሚለውን ክስ ውድቅ በማድረግ፥ ቡድኑ በጋዛ የርሃብ ቀውስ መከሰቱን በመጥቀስ ታጋቾች፤ ታጣቂዎች እና ህዝቡ የሚመገቡትን እየተመገቡ ነው ብሏል።

እስራኤላውያን ታጋቾች የሆኑት የ21 ዓመቱ ብራስላቭስኪ እና የ24 ዓመቱ ዴቪድ ከኖቫ የሙዚቃ ፌስቲቫል ታፍነው የተወሰዱት ሀማስ መስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም. በደቡብ እስራኤል የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ እንደሆነ ይታወቃል።

ማለቂያ የሌለው ቀውስ?
የእነዚህ ቪዲዮዎች መለቀቅ በጋዛ ሲቪል ፍልስጤማዊያን ህዝቦች ላይ እየደረሰ ያለው ስቃይ ላይ ተደምሮ ዓለም አቀፍ ቁጣን የተቀሰቀሰ ሲሆን፥ የሁለቱ ቪዲዮዎች መለቀቅ ግልጽ የሆነ የፕሮፓጋንዳ ዓላማ ቢኖራቸውም በጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ መንግሥት ላይ ከፍተኛ ትችት እንዲፈጠር አድርጓል ተብሏል።

የሆሎኮስት ታሪክ ምሁር የሆኑት ሃና ያብሎንካ ‘ሌ ሞንዴ’ ለተሰኘው የፈረንሳይ ጋዜጣ እንደተናገሩት “እነዚህን ምስሎች ያዩ እስራኤላውያን በሙሉ፣ ከኦሽዊትዝ በሕይወት የተረፉ ሰዎች ነፃ በወጡ ማግስት የሚያሳየውን ምስል እንዲያስታውሱ ያደርጋቸዋል” ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ከጋዛ የሚወጡት አስጨናቂ ምስሎች ‘እስከ መቼ?’ የሚለውን ጥያቄ እንደ አዲስ የሚያስነሱ እንደሆነም ጭምር ተገልጿል።

06 Aug 2025, 15:26