የተ. መ. የሰብአዊ መብት የህግ ባለሙያ በጋዛ እየደረሰ ያለውን ሞት ለመታደግ ሰብዓዊ እርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል አሉ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የቅርብ ጊዜ መረጃ እንደሚያሳየው ከአንድ ሶስተኛ በላይ የሚሆኑት የጋዛ ነዋሪዎች ለቀናት ያለ ምግብ እንደሚቆዩ እና ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከረሃብ ጋር ተያያዥነት ባላቸው ችግሮች እንደሚጠቁ፣ ብሎም አብዛዎቹ ደግሞ ለአስቸኳይ ጊዜ የረሃብ አደጋ መጋለጣቸውን የሚያሳይ ሲሆን፥ በአከባቢው አስቸኳይ የምግብ እርዳታዎችን የሚያቀርበው፣ ብሎም ለጨቅላ ህጻናት እና ታዳጊዎች በአመጋገብ ሥርዓት እና በመድሀኒት አቅርቦት በርካታ ሥራዎችን እየሰራ የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኤጀንሲዎች የረሃብ ሁኔታዎች እየተስፋፋ በመምጣቱ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ ጥሪውን አቅርቧል።
ኤጀንሲዎቹ እንደገለጹት የጅምላ ረሃብን ለመከላከል ከሚያስፈልገው የእርዳታ መጠን ከአምስት በመቶ በታች ብቻ ወደ ጋዛ እንዲገባ ስለሚፈቀድ አፋጣኝ እና የተሟላ ሰብአዊ ምላሽ ካልሰጠ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በቅርቡ ለሞት እንደሚዳረጉ አስጠንቅቀዋል።
የምግብ እና ግብርና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ኪዩ ዶንግዩ “ጋዛ በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛ ረሃብ አፋፍ ላይ ነች" ያሉ ሲሆን፥ ሰዎች እየተራቡ ያሉት ምግብ ባለመኖሩ ሳይሆን ተደራሽነቱ በመዘጋቱ እና የአካባቢው የግብርና ሥርዓቶች በመፍረሳቸው እንደሆነ ገልጸው፥ ይህም በመሆኑ ቤተሰቦች ከአሁን በኋላ በጣም መሠረታዊ የሆኑትን መተዳደሪያዎቻቸውን እንኳን ማስቀጠል እንደማይችሉ አስጠንቅቀዋል።
ዳይሬክተሩ ተጨማሪ ሞትን ለመከላከል ብቸኛው መንገድ የሆነውን ደህንነቱ የተጠበቀ እና ቀጣይነት ያለው ሰብአዊ አቅርቦት እንዲኖር ማድረግ እንደሆነ ጠቅሰው፥ በአከባቢው የምግብ ምርት እና ኑሮን ለማስቀጠል አፋጣኝ ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ በማቅረብ፥ “ምግብ የማግኘት መብት መሰረታዊ የሰው ልጅ መብት ነው” በማለት አክለዋል።
ምስራቅ እየሩሳሌምን እና እስራኤልን ጨምሮ በእስራኤል በተያዘው የፍልስጤም ግዛት ላይ የተባበሩት መንግስታት ገለልተኛ ዓለም አቀፍ አጣሪ ኮሚሽን ኮሚሽነር የሆኑት አውስትራሊያዊው የህግ ባለሙያ ክሪስ ሲዶቲ ከቫቲካን ረዲዮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ፍልስጤምን በሚመለከቱ የሰብአዊ መብት ጥያቄዎች ላይ ያተኮሩ ሲሆን፥ በሺዎች የሚቆጠሩት ሰዎችን ከሞት ለመታደግ ጊዜው በጣም እያለፈ በመሆኑ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ በአስቸኳይ እንዲፈቀድ ተማጽነዋል።
“ይህ እርምጃ በአጭር ጊዜ ውስጥ መወሰድ እንዳለበት በአጽንኦት ያሳሰቡት ክሪስ፥ ግድያውንም ለማስቆም ዘላቂ የሆነ የተኩስ አቁም እንደሚያስፈልግ እና የፍልስጤም መንግስት እና እስራኤል በሰላምና በፀጥታ አብረው እንዲኖሩ የሚያስችለውን የሁለት ሀገራት የመፍትሄ ህሳብ እንደሚመጣ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
ዮርዳኖስ ከተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ጋር በመተባበር 25 ቶን እርዳታ ከአየር ላይ መጣሏን ተከትሎ ተስፋዎች ቢኖሩም በጋዛ ስላለው ሰብአዊ ሁኔታ አስመልክቶ በአጠቃላይ በጋዛ ሰርጥ ያለውን ሁኔታ የተጠየቁት የህግ ባለሙያው፥ አሁን ካለው ችግር አንፃር በጣም አነስተኛ መሆኑን ጠቁመው ሆኖም ግን ጥሩ ጅማሮ እንደሆነ አመላክተዋል።
ነገር ግን በጭነት መኪናዎች የሚደረጉ የእርዳታ አቅርቦት ላይ ምንም ፍንጭ እንዳልታየ እና እዚያ ያለውን ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ለማቃለል ከተፈለገ የጭነት መኪናዎችን ወደ ጋዛ ማስገባት እንደሆነ ጠቁመው፥ ይሄ ጦርነት ከመጀመሩ ከመስከረም 26 ቀን 2017 ዓ.ም. በፊት ከፍተኛ ቁጥጥር እየተደረገባቸውም ቢሆን በቀን እስከ 2,000 የሚደርሱ የጭነት መኪናዎች ወደ ጋዛ ይገቡ እንደነበር አስታውሰዋል።
ከመስከረም 26 በኋላ አቅርቦቶቹ በአስደናቂ ሁኔታ መቋረጣቸውን እና በዚህ ዓመት ተደረጎ በነበረው የአጭር ጊዜ የተኩስ አቁም ስምምነት ወቅት እንኳን ከጥር እስከ መጋቢት መጨረሻ ድረስ በቀን 600 የጭነት መኪናዎች ብቻ ወደ ጋዛ ይገቡ እንደነበር አስታውሰው፥ በአሁኑ ወቅት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኤጀንሲዎች እና ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መሠረታዊ የሆነ የምግብ አቅርቦትን ለማሟላት በቀን ቢያንስ 2,000 የጭነት መኪናዎች እንደሚያስፈልጉ መገመታቸውን ጠቁመዋል። ስለዚህ ይህ በተኩስ አቁም ጊዜ ከገቡት ቁጥር በስድስት እጥፍ ያነሰ እንደሆነ፥ ብሎም ለጋዛ ህዝብ መሰረታዊ የምግብ እና የውሃ መጠን እንዲኖር ከሚፈለገው ቁጥር በ 5 በመቶ ያነሰ በመሆኑ ሙሉ በሙሉ በቂ እንዳልሆነ በመግለጽ፥ ይህ የእስራኤል ድርጊት እጅግ የከፋ የጦር ወንጀል ነው የሚሉ ሰዎችን ሃሳብ እንደሚያጠናክር አስምረውበታል።
አንዳንድ ሃገራት ይህ መጠነኛ መሻሻል ሊያመጣ የሚችለው አዎንታዊ ተጽእኖ ጉዳይ የተጠየቁት የህግ ባለሙያው በእርግጠኝነት ይህ ሃሳብ ወደዚህ ወደ ሚወራው 'ትንሽ መሻሻል' የመራ ቢሆንም፥ ሆኖም ግን ይሄ በቂ እንዳልሆነ ጠቁመው፥ ሃሳቡ የዓለም አቀፍ ጫና እንዲኖር ግፊት ሊያደርግ እንደሚችል ገልጸዋል።
“አሁን የሚያስፈልገው መናገር ብቻ ሳይሆን በእስራኤል መንግስት ላይ እውነተኛ ጫና የሚፈጥር ትክክለኛ እርምጃ መውሰድ ነው” ያሉት ክሪስ፥ የእስራኤል መንግስትን በቂ የምግብ አቅርቦት ወደ ጋዛ እንዲገባ ለማስገደድ የተቻለውን ያክል ህጋዊ አሰራሮች መተግበር እንደሚያስፈልግ ገልጸው፥ በሺዎች የሚቆጠሩ የጭነት መኪኖች ከጋዛ ድንበሮች ውጭ ቆመው የእስራኤል ባለስልጣናት ፍቃድ እየጠበቁ እንደሚገኝ አስታውሰዋል።
ጊዜው እየገፋ በሄደ ቁጥር ከፍተኛ አደጋ ስለሚከሰት ከሰብአዊነት አንፃር ሁኔታው ትንሽ እንኳን እንዲሻሻል ከዚህ ሌላ ምን መደረግ እንዳለበት ተጠይቀው፥ በጣም አስፈላጊው ነገር መሆን ያለበት በቂ መጠን ያለው ምግብ እና ውሃ፣ እንዲሁም የህክምና አቅርቦቶች መግባት እንዳለባቸው፣ ነገር ግን ይህ እንዳልሆነ አመላክተው፥ አንዳንድ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኤጀንሲዎች በሺዎች ወይም በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሳይሞቱ በፊት ሁኔታውን ለማሻሻል ከቀይ መስመሩ እንደታለፈ እና እንደዘገየ መግለፃቸውን አስታውሰዋል።
“እኔ የሰብአዊ እርዳታ ባለሙያ እንዲሁም ሰዎች ምን እንደሚመገቡ እና ምን ያህል እንደሚያስፈልጋቸው የማውቅ ባለሙያ አይደለሁም” ያሉት የህግ ባለሙያው፥ ነገር ግን በጋዛ የጅምላ ረሃብን ለማስቆም ጊዜው አልረፈደም ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል። አክለውም የመጀመሪያው እና በጣም አስቸኳዩ ነገር ምግብ፣ ውሃ፣ ትክክለኛ የህክምና አቅርቦቶች እና ሆስፒታሎች መልሰው ሥራ እንዲጀምሩ ለማድረግ ነዳጅ ማቅረብ ወሳኝ እንደሆነ ጠቁመዋል።
የእስራኤል ባለስልጣናት ይህንን ለመፍቀድ ምንም አይነት ምልክት እንዳላሳዩ የገለጹት ክሪስ፥ ሐምሌ 20 የወጣው እና ሐምሌ 21 ተግባራዊ መሆን የጀመረው ከፊል ፍቃድ እጅግ በጣም ትንሽ እና የተከሰተውን ረሃብ በበቂ ሁኔታ ለመፍታት የሚያስችል እንዳልሆነ ጠቁመዋል።
ነገር ግን ሌሎች መንግስታት በዓለም አቀፍ የፍትህ ፍርድ ቤት ባለፈው ሀምሌ በግልፅ የተቀመጡትን ግዴታዎቻቸውን በቁም ነገር የሚወስዱበት ጊዜ አሁን እንደሆነ ገልጸው፥ የዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት በማያሻማ መልኩ በማንኛውም ሃገራት የሚፈጸሙ ሰብዓዊ ዕርዳታዎችን የማገድ እርምጃዎች ትክክል እንዳልሁኑ ስለሚገልጽ፥ የእስራኤል መንግስት እያደረገ ያለውን ህገወጥ ድርጊቶች ማቆም እንዳለበት ማሳሰቡን ገልጸዋል።
ከዚህም ባለፈ ባለፈው ሐምሌ ወር በዓለም ዙሪያ ያሉ መንግስታት ከእስራኤል መንግስት ጋር ያላቸውን ግንኙነት ሁሉንም ገፅታዎች አስቸኳይ ምርመራ እንዲያደርጉ እና በማንኛውም መልኩ የእስራኤልን ሕገ-ወጥነት የሚያግዝ እና የሚያበረታታ የግንኙነቱ ገጽታዎች ምን እንደሆኑ ለመወሰን እንደሚያግዝ፣ ብሎም ሌሎች መንግስታት የዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት የለየውን ህጋዊ ግዴታዎች በቁም ነገር የሚወስዱበት እና ከእስራኤል ጋር ያለውን ግንኙነት በማቆም በማንኛውም መንገድ የእስራኤልን ህገ-ወጥነት የሚረዱ ወይም የሚያግዙበት ጊዜ ላይ ተደርሷል ብለዋል።
በተለይ የዓለም አቀፍ ተቋማትን ህጋዊነት የሚጠራጠሩ ሰዎች እየበዙ ባለበት በአሁኑ ወቅት የዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤትን ውሳኔ ለመተግበር አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል የተጠየቁት ክሪስ፥ ተቋማቱ ላይ እየደረሰ ያለው ትችት ከሁለት አቅጣጫ እንደሚመጣ አስታውሰው፥ በአንደኛ ደረጃ ዓለም አቀፍ ሕግንና ዓለም አቀፍ ተቋማትን ለማጥፋት የተነሱ ጥቂት አገሮችና የፖለቲካ መሪዎች እንዳሉ ገልጸው፥ አብዛኛው ሰው ዓለም አቀፉ የህግ ስርዓት አቀርባለሁ ብሎ ቃል የገባውን ነገር ባለመተግበሩ እንደሚበሳጭ እና በዓለም አቀፉ ህግ ላይ ጥርጣሬ እንደመጣ አስረድተው፥ ይህ ቀውስ ሊፈታ የሚችለው በዓለም አቀፍ ስርዓት አማካይነት እጅግ በጣም ከባድ ለሆነ የዓለም አቀፍ ህግ ጥሰቶች ምላሽ መስጠት የሚችል መሆኑን በማሳየት ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል።
በእርግጥ አሁን ላይ በዓለም አቀፍ ስርዓት ውስጥ ቀውስ እንዳለ ቢታወቅም አሁን ያለንን ስርዓት ለመመስረት እርምጃዎች የተወሰዱበት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ባሉት 80 ዓመታት ውስጥ ይህ ዓለም አቀፋዊ የሕግ ሥርዓት ካጋጠመው እጅግ አሳሳቢ ቀውሶች አንዱ እንደሆነ ገልጸዋል።
ሃምሌ 21 እና 22 በኒውዮርክ በተካሄደው ጉባኤ የተነሳው የሁለት ሀገራት የመፍትሄ ሃሳብ አጠቃላይ ሂደቱን ሊያወሳስበው ይችል እንደሆን እና አጠቃላይ ሂደቱን ደግሞ እንዴት እንደሚያዩት የተጠየቁት የህግ ባለሙያው፥ በእርግጥ ያንን ሂደት ሊያወሳስበው እንደሚችል ጠቁመው፥ ሃገራት ከንግግር ወደ ተግባር ለመሸጋገር ካልተዘጋጁ የሁለት ሃገራት መፍትሄዎች ላይ ምንም አይነት እድገት እንደማያመጣ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
“ዓለም አቀፍ እርምጃ እንደሚያስፈልግ ግልጽ ነው” ያሉት ክሪስ፥ በመካከለኛው ምሥራቅ ላለፉት 80 ዓመታት፣ ማለትም ለ75 ዓመታት ያህል በመካከለኛው ምሥራቅ ለተፈጠረው ሁኔታ እንደ መፍትሄ የሚታየውን በተጨባጭ ተግባራዊ ለማድረግ በተለየ ሁኔታ በእስራኤል መንግሥት እና በፍልስጤም ባለሥልጣናት ላይ ጫና ማድረግ እንደሚያስፈልግ በአጽንዖት ገልጸዋል።
የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ እ.አ.አ. በ 1947 ዓ.ም. ለመካከለኛው ምስራቅ የሁለት ሃገራት የመፍትሄ ሃሳብ አቀራረብ እንዲተገበር ውሳኔውን አሳልፎ እንደነበር ያስታወሱት የህግ ባለሙያው ክሪስ በመጨረሻም ፥ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የተደረጉት ነገሮች ሁሉ ምናልባትም በ 1990 ዎቹ መጀመሪያ ላይ የተደረገውን የኦስሎ ስምምነትን ሳይጨምር የተደረገው ነገር ሁሉ አንድ እርምጃ እንደሆነ ጠቁመው፥ ችግሩ ሕጉ እና ንግግር ማድረግ ሳይሆን፣ ትልቁ ችግር እርምጃ አለመውሰድ መሆኑን ጠቁመዋል።