የሱዳን ንፁሀን ዜጎች በጦርነት፣ ረሃብ፣ መፈናቀል እና በሽታ እየተሰቃዩ እንደሆነ ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ዓለም አቀፋዊ ግድየለሽ በሚመስል ሁኔታ ይህ አውዳሚው ጦርነት ሞትን እና ውድመትን ማስከተሉን በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት፥ የኮሌራ በሽታ በመላ ሀገሪቱ በመስፋፋት ላይ የሚገኝ ሲሆን፥ በተለይ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ህጻናት ለበሽታው ተጋላጭ መሆናቸው እየተነገረ ይገኛል።
በ 2015 ዓ.ም. ሚያዚያ ወር ላይ የተጀመረው የሱዳን ግጭት በሱዳን ጦር ሃይሎች (SFA) እና በፈጣን የድጋፍ ሰጪ ሃይሎች (RSF) መካከል በተፈጠረ ጭካኔ የተሞላበት የስልጣን ሽኩቻ ምክንያት እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን፥ የእርስ በርስ ጦርነቱ ከተነሳበት ጊዜ አንስቶ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መፈናቀል፣ ለሺዎች ሞት እና ከባድ ሰብዓዊ ቀውስን አስከትሏል፥ ብሎም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ለከፍተኛ ምግብ እጦት ተዳርገዋል።
ይህ ግጭት በምዕራብ ዳርፉር ክልል የዘር ማጥፋት ወንጀል እንዲፈጸም እንዲሁም ህዝቡ ለረሃብ እንዲጋለጥ፣ ብሎም ለዓለም አቀፍ ህግ እና ለሲቪሎች መብት መከበር ግድየለሽነትን ማስከተሉ ተነግሯል።
በጦርነት በተጎዳችው ሱዳን፤ ምስራቃዊ ዳርፉር ግዛት በሚገኝ የስደተኞች ካምፕ በተፈጠረ ከባድ የምግብ እጥረት ምክንያት ባለፈው ወር 13 ህፃናት መሞታቸውን የህክምና ባለሙያዎች መግለፃቸው ይታወሳል።
የአፍሪካ ህብረት ስጋት
የፈጣን ድጋፍ ሰጪ ሃይሎች 15 አባላት ያሉት የአስተዳደር ምክር ቤት እና ትይዩ መንግስት ማቋቋምን ይፋ ካደረገ ከጥቂት ቀናት በኋላ በዚህ ሳምንት ሊካሄድ የታቀደው የሰላም ድርድርን የአፍሪካ ህብረት ወደኋላ እየጎተተው እንደሆነ እየተነገረ ይገኛል።
ህብረቱ አባል ሀገራት እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለተቀናቃኙ መንግስት እውቅና እንዳይሰጡ እያሳሰበ ሲሆን፥ የፈጣን ድጋፍ ሰጪ ሃይሎች እርምጃ ሱዳንን የበለጠ ሊበታተን የሚችል እና ችግሩን በድርድር ለመፍታት የነበረውን ቀሪ ተስፋ ሊያጨልም እንደሚችል አስጠንቅቋል።
በአሁኑ ወቅት ዋናው የሱዳን ጦር ሰራዊቱ ካርቱምን እና አብዛኛውን የሰሜን፣ ምስራቅ እና ማዕከላዊ ክልሎችን ተቆጣጥሮ እንደሚገኝ፥ የፈጣን ድጋፍ ሰጪ ሃይሎች ደግሞ አብዛኛውን የዳርፉር እና የኮርዶፋን ክፍሎች ይዞ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን፥ በቅርብ ጊዜ በተፈጸሙት ጥቃቶችም በመቶዎች የሚቆጠሩ መሞታቸውን የሃገር ውስጥ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ገልጸዋል።
በዓለም ላይ ካሉ በጣም ድሃ አገሮች አንዷ
ከጦርነቱ በፊት ሱዳን ምንም እንኳን የወርቅ አምራች የነበረች ሀገር ብትሆንም በዓለም ላይ ካሉት ድሃ ሃገራት መካከል አንዷ ስትሆን፥ ባለፉት አስር ዓመታት ወይም ከዚያ በላይ፣ ኃይለኛው የፈጣን ድጋፍ ሰጪ ሃይሎች መሪ ጄኔራል ዳጋሎ በሊቢያ እና በየመን ግጭቶች ውስጥ ድርሻ የነበረው ፈርጣማ ጦር መገንባታቸው የሚነገር ሲሆን፥ አንዳንድ የሱዳን የወርቅ ማዕድን ማውጫዎችን በመቆጣጠር ወደ በለጸጉ የባህረ ሰላጤው ሃገራት እንደሚያሸጋግር ተነግሯል።
የፈጣን ድጋፍ ሰጪ ሃይል ተቀናቃኝ መንግስት ለመመስረት ያለው እቅድ፥ ደቡብ ሱዳን በ 2003 ዓ.ም. ከተገነጠለች ወዲህ ሀገሪቱ ለሁለተኛ ጊዜ ልትከፋፈል ይችላል የሚል ስጋትን ፈጥሯል።