ፈልግ

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ታጣቂዎች በንቶዮ መንደር ላይ ጥቃት ካደረሱ በኋላ በርካታ ቤቶች ፈርሰዋል በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ታጣቂዎች በንቶዮ መንደር ላይ ጥቃት ካደረሱ በኋላ በርካታ ቤቶች ፈርሰዋል 

በምስራቃዊ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ‘እልቂቱ እንዲቆም እና ሰላም እንዲሰፍን’ ጥሪ ቀረበ

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ውስጥ የተከሰተው ብጥብጥ ተጠናክሮ በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት የ ‘ድንበር የለሽ ሚሲዮናውያን ቤተሰቦች ማህበር’ ዳይሬክተር ለቫቲካን ዜና እንደተናገሩት በሀገሪቱ ምስራቃዊ ክፍል በየቀኑ በርካታ ጭፍጨፋዎች እንደሚፈጸሙ በማንሳት ስለ አካባቢው ነዋሪዎች ስቃይ አጋርተዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በቅርቡ በሰሜን ኪቩ በምትገኘው ንቶዮ ወረዳ በደረሰ ጥቃት በትንሹ 89 ሰዎች መሞታቸው እና በሲቪሎች ላይ ተጨማሪ መፈናቀል ምክንያት መሆኑን ከአከባቢው የሚወጡ መረጃዎች የሚያሳዩ ሲሆን፥ የቡቴምቦ-ቤኒ ጳጳስ የሆኑት ብፁእ አቡነ መልከሴዲቅ ሲኩሊ ጉዳዩን አስመልክተው እንደተናገሩት “ሌላ አሰቃቂ ጭፍጨፋ” በማለት ገልጸውታል።

ጳጉሜ 3 ቀን 2017 ዓ.ም. ምሽት የታጠቁ ሰዎች በአቅራቢያው ካለ ጫካ ወጥተው በአብዛኛው የካቶሊክ እና የፕሮቴስታንት ክርስቲያኖች የሆኑት የንቶዮ ነዋሪዎች ለቀብር ሥነ ሥርዓት በተሰበሰቡበት ሥፍራ ላይ ጥቃት ሰንዝረው ቢያንስ 89 ሰዎች መገደላቸው እና በደርዘን የሚቆጠሩ ቤቶችና ተሽከርካሪዎች መቃጠላቸው የሚታወስ ሲሆን፥ ድንገተኛ ጥቃቱ እስላማዊ መንግስት ከሚባለው ቡድን ጋር አጋርነት ካለው እና በኡጋንዳ ውስጥ በተፈጠረው ኤ.ዲ.ኤፍ ወይም የአሊያድ ዲሞክራሲያዊ ሃይል በሚባል አማፂ ቡድን እነደተፈጸመ ተነግሯል።

ይህ ታጣቂ ቡድን በምስራቃዊ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ግጭት ውስጥ ከሚገኙት በርካታ ታጣቂ ቡድኖች መካከል አንዱ እና አራት አስርት ዓመታትን ያስቆጠረ ቡድን ሲሆን፥ የኪጋሊ መንግስት ክሱን ያለማቋረጥ ውድቅ ቢያደርግም የተባበሩት መንግስታት ባለሙያዎች ቢያንስ በ4,000 የሩዋንዳ ወታደሮች እንደሚደገፍ ከሚናገሩለት ከኤም 23 ሚሊሻ ወይም ‘የማርች 23 ንቅናቄ’ ተብለው ከሚታወቁት አማፂያን ጋር ተባብሮ እንደሚሰራ ይነገራል።

ዕለታዊ ጥቃት እና መፈናቀል
ከንቶዮ ጥቃት በኋላ ወደ 2,500 የሚጠጉ ነዋሪዎች 7 ኪሜ በሚርቀው እና የኮንጐ ሰራዊት ክፍሎች የነበሩበት፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ እ.አ.አ. ከ 2021 ዓ.ም. ጀምሮ የኡጋንዳ ወታደሮች ወደ ሚገኙበት ማንጉሬ-ድጂፓ የማዕድን ማውጫ ሰፈር እንደሸሹ ተነግሯል።

ከቡቴምቦ አከባቢ የመጣው ጀስቲን ሙሂንዶ ከ 2006 ዓ.ም ጀምሮ በየሳምንቱ፣ አልፎ ተርፎም በየቀኑ ማለት በሚቻል ደረጃ እልቂቶች እንደሚከሰቱ ገልፆ፥ እሱ የሚሰራበት ‘ድንበር የለሽ የሚስዮናውያን ቤተሰቦች ማህበር’ የትውልድ መንደሩ ንቶዮን ጨምሮ በሰሜን ኪቩ ውስጥ የትምህርት፣ የጤና እና የሰብአዊ ፕሮጄክቶችን እያካሄዱ እንደሚገኝ አብራርቷል።

ባለፈው ሳምንት በደረሰው ጥቃት የቤተሰቡ መኖሪያ መቃጠሉን ለቫቲካን ዜና የተናገረው ጀስቲን፥ በአሁኑ ወቅት ዘመዶቹን ጨምሮ 23 አዲስ ተፈናቃዮችን ማስጠለሉን ገልፆ፥ የአከባቢው ሰዎች በባህላዊ መንገድ ሃዘናቸውን ለመግለጽ እና የተጎዱትን ለመደገፍ በተሰበሰቡበት ምሽት ላይ ጠመንጃ እና የተለያዩ መሳሪያዎችን የታጠቁት ‘አሸባሪዎች’ ደርሰው ነዋሪዎቹን መግደል እንደጀመሩ አብራርቷል።

የኤ.ዲ.ኤፍ ጥቃት ሰሜን ኪቩን እና የሀገሪቱን ምስራቃዊ ክፍል “ለበርካታ ዓመታት” ሲያወድም እንደነበር ያስታወሰው ጀስቲን፥ የቡድኑ ፍላጎት ከኤም 23 ጋር በመተባበር ማዕድናትን በተለይም ወርቅ እና ኮልታን የተሰኘ ማዕድንን መፈለግን እንደሚያጠቃልል በተለያየ መንገድ ይነገራል ብሏል።

ድንገተኛ ጥቃቱ እንዴት ተከሰተ
እሁድ ዕለት ቡቴምቦ ከተማ ውስጥ ከተፈናቀሉት ሰዎች ጋር ተገናኝቶ እንደነበር የተናገረው ጀስቲን፥ ተፈናቃዮቹ የሚመሰክሩት ነገር በጣም አስፈሪ እንደነበር እና አንዳንዶች በእሳት እየጋየ ከነበረ ቤታቸው ውስጥ አምልጠው እንደመጡ እና እስካሁን በህይወት መኖራቸው ራሱ ተአምር እንደሆነ ሲገልጹ እንደነበር፣ የአሸባሪዎቹ ቡድን በጣም ትልቅ እንደሆነ እና የወታደር ልብስ የለበሱ ሴቶች እና ሕፃናትን ጨምሮ በቁጥር ወደ 70 እንደሚጠጉ መመስከራቸውን አስታውሷል።

ከዚህም ባለፈ አንዳንድ የመንደሩ ነዋሪዎችን ስም እንኳን ያውቁ እንደነበር ያስታወሱት ተፈናቃዮቹ፥ ይህም ነዋሪዎቹ ሳያውቁ የአከባቢውን አቀማመጥ ለማጥናት አስቀድመው መንደሩን ይሰልሉ እንደነበር ይጠቁማል ብለዋል።

ጀስቲን በቅርብ ቀናት ውስጥ በአቅራቢያው ባሉ መንደሮች ተመሳሳይ ጥቃቶችን መከሰታቸውን ገልፆ፥ ከእነዚህም መካከል በሐምሌ ወር ላይ በኢቱሪ ክልል፣ ኮማንዳ ወረዳ ውስጥ በሚገኘው የካቶሊክ ቤተክርስትያን በቅዱስ ቁርባን ስግደት ላይ በነበሩ ወጣቶች እና ምዕመናን ላይ የደረሰው ሰፋ ያለ ጥቃት እንደሚገኝበት አስታውሷል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የእነዚያ “ሰማዕታት” ደም “የሰላም፣ የእርቅ፣ የወንድማማችነት እና ለመላው ኮንጎ ሕዝብ የፍቅር ዘር እንዲሆን በመጸለይ ቅርበታቸውን እና የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገለጸው እንደነበር ይታወሳል።

“ሰላም እንፈልጋለን”
“ህዝቡ ሰላም ነው የሚያስፈልገው” ያለው ጀስቲን፥ ምክንያቱም ትምህርት የሚማረው፣ የተለያዩ አገልግሎቶችን ማግኘት እና ስለ ልማት ማሰብ የሚችለው ከሰላም በኋላ መሆኑን ገልፆ፥ ያለ ሰላም ወደ እርሻ ቦታ መሄድ እና በአከባቢው የሚገኙ በርካታ ህፃናትን ደግሞ ወደ ትምህርት ቤት መላክ እንደማይቻል፥ ብሎም በርካታ ሆስፒታሎች እና የጤና ጣቢያዎች በእነዚህ ጥቃቶች መውደማቸውን ከገለጸ በኋላ፥ በመጨረሻም ለመሪዎቹ እና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ባስተላለፈው መልዕክት 'ሰላምን አመጣለሁ፣ እንዲሁም ሰዎች ከእንግዲህ በኋላ አይገደሉም' የሚለን ሰው ብቻ ነው የምንፈልገው በማለት አጠቃሏል።

22 Sep 2025, 14:33