በሊቢያ አቅራቢያ በጀልባ ላይ በተነሳ የእሳት አደጋ በትንሹ 50 ሱዳናውያን ስደተኞች መሞታቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት እንዳስታወቀው የተሻለ ኑሮ እና ሰላም ፍለጋ ብሎም ከጦርነት ለማምለጥ ከአፍሪካ ወደ አውሮጳ ለመሻገር 75 የሱዳን ስደተኞችን ጭኖ በጉዞ ላይ የነበረ የስደተኞች መርከብ እሁድ ዕለት በሊቢያ የባህር ጠረፍ ላይ በእሳት ጋይቶ ቢያንስ 50 ሰዎች መሞታቸውን ያስታወቀ ሲሆን፥ ተቋሙ በህይወት ለተረፉ 24 ሰዎች የህክምና ድጋፍ ማድረጉን ገልጿል።
እ.አ.አ. በ 2011 ዓ.ም. አምባገነኑ ሙአመር ጋዳፊ ከስልጣን ከተወገዱ ወዲህ ሊቢያ ሜዲትራኒያን ባህርን አቋርጠው ወደ አውሮፓ ለሚሰደዱ ስደተኞች መሸጋገሪያ ሆና እያገለገለች ሲሆን፥ በየካቲት 2017 ዓ.ም. በተደረገ ጥናት ከ44 ሀገራት የመጡ ወደ 86,000 የሚጠጉ ስደተኞች ሊቢያ ውስጥ እንደነበሩ ይፋ ተደርጓል።
በመንግስት ሃይሎች የሚፈጸም የሰብአዊ መብት ረገጣ
ይህ በእንዲህ እያለ ‘ሜዲቴራኒያ ሴቪንግ ሂውማንስ’ የተባለ የጣሊያን የሰብአዊ መብት ድርጅት በሲሲሊ ከተማ ለሚገኘው ፍርድ ቤት ባቀረበው አዲስ ማስረጃ በአውሮፓ ህብረት የሚደገፉ የሊቢያ ወታደራዊ ሰራተኞች የሚፈጽሙትን የሰብአዊ መብት ረገጣዎችን በዝርዝር ማቅረቡ የተገለጸ ሲሆን፥ ይህ በሜዲትራኒያን ባህር ላይ የሚንቀሳቀሱ ስደተኞችን የሚታደገው ሰብአዊ ተቋም ለረጅም ጊዜያት በነፍስኄር ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ሲደገፍ እንደነበር ተመላክቷል።
ተቋሙ ባቀረበው መረጃ መሰረት በትሪፖሊ ዓለም አቀፍ እውቅና ካለው መንግስት ጋር ግንኙነት ያላቸው የ111ኛ ብርጌድ ወታደሮች በሊቢያ ባህር ዳርቻ ወደ ባህር ተወርውረዋል ያላቸውን አስር ስደተኞችን ጉዳይ ይፋ ማድረጉ የተገለጸ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ ይህ ሰብአዊ ተቋም በቀጥታ ከሊቢያ መንግስት ሃይሎች ጋር የተገናኙ፣ በጣሊያን መንግስት የሰለጠኑ እና የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግላቸው ግለሰቦችን የሚያመለክቱ ፎቶግራፎችን እና የቪዲዮ ምስሎችን ማሳተሙ ተነግሯል።
ድርጅቱ በማከልም የአውሮፓ መንግስታት የዓለም አቀፍ ህግን በመጣስ እያወቁ በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ከሚሳተፉ ቡድኖች ጋር በመተባበር እንደሚሰሩ ይፋ በማድረግ የከሰሰ ሲሆን፥ በዚህ ህገ ወጥ ድርጊት ላይ ተሳትፈዋል ያላቸውን ሰዎች ማንነት ጨምሮ ማስረጃዎቹን ለዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ማቅረቡ ተገልጿል።