ፈልግ

የቤተልሔም ከንቲባ የሆኑት ማሂር ኒኮላ ካናዋቲ  ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ካቀረቡ በኋላ ሰላምታ ሲለዋወጡ የቤተልሔም ከንቲባ የሆኑት ማሂር ኒኮላ ካናዋቲ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ካቀረቡ በኋላ ሰላምታ ሲለዋወጡ  (@Vatican Media)

የቤተልሔም ከንቲባ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮን አግኝተው ለተስፋ እና ለአብሮነት ጥሪ ማድረጋቸው ተነገረ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ መስከረም 14 ቀን 2018 ዓ.ም. ካቀረቡት ሳምንታዊ ጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በኋላ ከቤተልሔም ከተማ ከንቲባ ጋር ተገናኝተው ሰላምታ የተለዋወጡ ሲሆን፥ ብፁእነታቸው ጦርነቱ እንዲቆም እና በቅድስት ሃገር የክርስቲያኖች ህልውና እንዲጠበቅ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የቤተልሔም ከንቲባ ሆነው በቅርቡ የተሾሙት ማሂር ኒኮላ ካናዋቲ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ረቡዕ ጠዋት ካቀረቡት ሳምንታዊ ጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በኋላ ከብፁእነታቸው ጋር ተገናኝተው ባደረጉት ውይይት ህዝቡ ስላለበት አሳሳቢ ሁኔታ በማንሳት በቅድስት ሀገር ሰላም እና ተስፋ እንዲመጣ ተማጽነዋል።

“በእውነቱ፣ የቤተልሔም ከንቲባ ሆኜ በተሾምኩበት ወቅት የጻፍኩት የመጀመሪያው ደብዳቤ ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የተላከ ደብዳቤ ነው” ያሉት ከንቲባው፥ ምክንያቱም ሲያስረዱ ከዚህ ተነስተው ብዙ ነገር መሥራት እንደሚቻል እና ሕዝባቸውን መደገፍ እንደሚችሉ እምነቱ እንዳላቸው ገልጸው፥ በጣም አስፈላጊው ነገር ለህዝቡ ተስፋ መስጠት እንደሆነ ተናግረዋል።

ከንቲባው እንዳስረዱት ስደት ቤተልሔምን እና ሌሎች የፍልስጤም ከተሞችን እያራቆተ እና በቅድስት ሀገር የክርስቲያን ህልውናዋ ላይ አደጋ እየጣለ እንደሆነ ጠቅሰው፥ በአከባቢው በተፈጠረው ችግር ምክንያት ሰዎች ቤተልሔምን እና ፍልስጤምን ለቀው እየወጡ እንደሚገኝ፣ ብሎም በቤተልሔም ዙሪያ የተደረጉ ሰፈራዎች የከተማው ህዝብ መካከል ፉክክር እንዲኖር እና በተፈጥሮ ሀብቶች ላይ ከፍተኛ ጫና እንዲኖር ማድረጉን አብራርተዋል።

ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጋር የነበራቸው ቆይታ
ግንቦት ወር ላይ የተሾሙት ከንቲባ ካናዋቲ፣ ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ጋር በግል ተገናኝተው ለመወያየት ላቀረቡት ጥያቄ ምላሽ በማግኘታቸው በማመስገን፥ ብፁእነታቸው በፍልስጤም፣ በጋዛ እና በቤተልሔም ውስጥ እየሆነ ስላለው ነገር ድምጽ ማሰማታቸው ጠቃሚ እንደሆነ እና የቅድስት ሀገር መሰረት የሆኑ ህዝቦችን መጠበቅ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ለእርሳቸው ለማስረዳት ጥሩ ጊዜ ማግኘታቸውን አስታውሰው፥ ‘ለሃገሪቱ መሰረት የሆኑ ህዝቦች የሌሉባት ቅድስት ሃገር ሙዚየም ብቻ ናት’ በማለት ገልጸዋል።

“ሁልጊዜ ስለ ቤተልሔም ከመናገሬ በፊት እጸልያለሁ” ያሉት ከንቲባው ከቅዱስ አባታችን ጋር ያደረጉት ስብሰባ ጠቃሚ እንደነበር አስታውሰው፥ በውይይቱ ወቅት በዋናነት የተነጋገሩት ይህን ጦርነቱን ለማስቆም እና በጋዛ የሚገኙ ህዝቦች ላይ እየደረሰ ያለውን ነገር በአስቸኳይ እንዲቆም የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ድምጽ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን እንደነገሯቸው እና እሳቸውም እንደተስማሙ ገልጸዋል።

ቤተልሔም እና በውስጧ የሚገኙ ክርስቲያኖች ጫና ውስጥ ናቸው
ከንቲባው ቤተልሔም 37 ኪ.ሜ. ስክዌር ስፋት እንዳላት እና በአሁኑ ወቅት በከተማዋ ውስጥ ያለውን ህይወት ለብፁእነታቸው ለማስረዳት እንደሞከሩ ገልጸው፥ በአሁኑ ወቅት እየታዩ ከሚገኙት የተስፋፊነት እና የሰፈራ ድርጊቶች በኋላ፥ እንዲሁም በብዙ ነገር ከሚተሳሰሩት እህት ከተማ ከሆነችው ኢየሩሳሌም ጋር የነጣጠላቸው የመለያያ ግንብ ከተገነባ በኋላ፥ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደ ቤተሌማውያን ብዙ ችግሮችን እያስተናገድን እንገኛለን ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በፍልስጤም ግዛቶች ውስጥ የፍልስጤም ክርስቲያኖች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ እንደሚያሳስባቸው አጽንዖት ሰጥተው የገለጹት ከንቲባው፥ በአሁኑ ጊዜ በቅድስት ሀገር የሚገኙ ፍልስጤማዊያን ክርስቲያኖች 168,000 ብቻ እንደሆኑ እና በመላው ዓለም ደግሞ ከ4 ሚሊዮን በላይ ፍልስጤማዊያን ክርስቲያኖች እንደሚገኙ ገልጸው፥ ይህ አሃዝ በራሱ በክርስቲያኖች ላይ ምን ያህል ጫና እንዳለ ያሳያል ብለዋል።

የክርስትና እምነት ተከታይ የሆኑት ካናዋቲ፥ በሕጉ መሠረት የቤተልሔም ከንቲባ ክርስቲያን መሆን እንዳለበት ገልጸው፤ ይህ በፍልስጤም መሪዎች የተደገፈው ድንጋጌ በቤተልሔም፣ በቅድስት ምድር እና በፍልስጤም ውስጥ የሚኖረውን በዓለም ላይ ጥንታዊውን የክርስቲያን ማኅበረሰብ ለመጠበቅ ተፈልጎ የተደነገገ ህግ መሆኑን አስረድተዋል።

አሁንም ድረስ በርካታ ክርስቲያኖች አከባቢውን ለቀው እየወጡ እንደሆነ የጠቆሙት ከንቲባው፥ ማንም ሰው ቤተልሔምን ለቆ ሲወጣ ልባቸው እንደሚሰበር ገልጸው፥ ባለፈው ዓመት ብቻ ከ1000 የሚበልጡ ክርስቲያኖች ወደ ካናዳ፣ ዩናይትድ ስቴትስና ሌሎች አገሮች ለመሰደድ ላቀረቡት ጥያቄ ፈቃድ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

የቱሪዝም እና የኢኮኖሚ ውድቀት
መስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ከተቀሰቀሰው ጦርነት በኋላ በመንፈሳዊ ንግደት እና በቱሪዝም ላይ የተመሰረተው የቤተልሔም ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ ማሽቆልቆሉን ጠቅሰው፥ በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ አጠቃላይ 84 ሆቴሎች በሙሉ መዘጋታቸውን እና የስጦታ ዕቃ መሸጫ ሱቆች፣ ውብ የወይራ እንጨት የሚያመርቱ ቤቶች እና የጌጣጌጥ መሸጫ ሱቆች ሙሉ በሙሉ ዝግ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ባለፉት ጊዜያቶች 14 በመቶ የነበረው የሥራ አጥነት መጠን በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮ ወደ 65 በመቶ ከፍ ማለቱን ገልጸው፥ ግጭቱ በእስራኤል አካባቢዎች ሥራ የማግኘት እድሉን በከፍተኛ ሁኔታ እንዳጠበበው አመላክተዋል።

ከ120,000 የሚበልጡ ቤተሌማውያን ከከተማ ውጭ ይሠሩ እንደነበር ያስታወሱት ከንቲባው፥ ከእነዚህም ውስጥ አንዳንዶቹ የባንክ ብድር እንደነበረባቸው እና በአሁኑ ወቅት የዕለት ጉርሳቸውን ማግኘት እንዳልቻሉ በሃዘኔታ ገልጸዋል።

ውሃ
የውሃ እጥረት እና የህዝቡን እንቅስቃሴው መገደብ ሁኔታውን የበለጠ እንዳባባሰው የገለጹት ከንቲባው፥ በቤተልሔም የሚገኙት ፍልስጤማውያን ጉድጓድ ቆፍረው የራሳቸውን ውሃ እንዳያወጡ ስለሚከለከሉ ችግሩ ከባድ መሆኑን ጠቁመው፥ “ውሃችንን የምንገዛው ከእስራኤላውያን ስለሆነ አንድ ሰው በቀን ከሚያስፈልገው ውስጥ አንድ አምስተኛውን ብቻ ነው የሚሸጡልን” በማለት ችግሩን በምሬት ገልጸዋል።

በቤተልሔም አንዳንድ አካባቢዎች ለ50 እና ለ60 ቀናት ያክል ውሃ እንደማያገኙ ያስታወሱት ከንቲባው፥ ከዚህም ባለፈ በከተማው ውስጥ እንኳን ከ134 በላይ የሚሆኑ ማገጃዎች እና ኬላዎች እንዳሉ ጠቁመው፥ እንቅስቃሴን በማደናቀፍ ሰዎች ነፃነታቸውን ብቻ ሳይሆን ለቤተሰባቸው የሚያስፈልጋቸውን ነገሮች ሟሟላት እንዳይችሉ እና የወደፊት ዕጣ ፈንታቸውን እንዳይገነቡ ያደርጋል ብለዋል።

ለአብሮነት እና ለተስፋ የተደረገ ጥሪ
በቅርቡ በጣሊያን እና በሌሎች ሀገራት ያጋጠማቸው የትብብር መንፈስ ተጨባጭ ለውጥ እንደሚያመጣ የገለጹት ከንቲባ ካናዋቲ፥ ይህ ለሰዎች የበለጠ ተስፋ የሚሰጥ ነገር መሆኑን ጠቅሰው፥ ይህ ስለ እኛ የሚያስብ ሰው እንዳለ እና እኛንም እንዳልረሱን ያሳስበናል ብለዋል።

ከዚህም ባሻገር የላቲን ፓትርያርክ እና የአካባቢው ካህናት እያደረጉላቸው ያለውን ድጋፍ ያነሱት ከንቲባው “አሁን በቤተልሔም ስለምንገኝ ይህ በጣም ጥሩ ተስፋ ነው” በማለት ጠቁመው፥ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማገዝ የሚችልበትን መንገድ በተመለከተ፣ ህዝቡ አከባቢውን ለቆ እንዳይወጣ ለአካባቢው ድርጅቶች ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበው፥ አሁን ለማድረግ እየተሞከረ ያለው ዋናው ነገር ይህ መሆኑን አስረድተዋል።

25 Sep 2025, 13:51