ፈልግ

በጋዛ ከተማ በእስራኤል ጥቃት ከደረሰው ፍንዳታ በኋላ የተከሰተ ጭስ በጋዛ ከተማ በእስራኤል ጥቃት ከደረሰው ፍንዳታ በኋላ የተከሰተ ጭስ 

እስራኤል በጋዛ እያደረሰች ያለውን ጥቃት በማጠናከሯ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መፈናቀላቸው ተነገረ

እስራኤል ማክሰኞ ዕለት የጀመረችውን የምድር ጥቃቷን አጠናክራ በመቀጠል በጋዛ ከተማ ከ150 በላይ ኢላማዎችን መምታቷን ገልፃለች።

   አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

እስራኤል ማክሰኞ ዕለት በጋዛ ከተማ ላይ የጀመረችውን እና በርካታ አካባቢዎች ላይ ያለእረፍት እየፈፀመች የሚገኘውን የምድር ላይ ጥቃት ተከትሎ የጋዛ ሲቪል መከላከያ ባለስልጣን 12 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ገልፆ፥ ከዚህም በተጨማሪ እስራኤል የሃማስ ባለስልጣናት ዋና መገኛ አድርጋ ከምትጠራት የጋዛ ከተማ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ፍልስጤማዊያን አከባቢውን ሸሽተው እየወጡ እንደሆነም ገልጿል።

ይህ በእንዲህ እያለ የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትስ ሃገራቸው “ተልኮዋን እስክታጠናቅ ገላጋይ እንደማትሰማ እና በምንም ሁኔታ ወደኋላ እንደማትመለስ ሁሉም ማወቅ አለበት” ሲሉ መናገራቸው ተሰምቷል።

ላለፉት አስር ቀናት የእስራኤል ወታደሮች ከተማዋን ለመቆጣጠር በሚደረገው ዘመቻ በጋዛ ትልቁ የህዝብ ማዕከል ውስጥ የከተማ መሠረተ ልማቶችን ስልታዊ በሆነ መንገድ እያወደሙ እንደሆነም ጭምር ተገልጿል።

አንድ ሚሊዮን ህዝብ ባላት እና በዓለም ላይ እጅግ በጣም ብዙ ህዝብ ተጨናንቆ በሚኖርባት የሺህ ዓመት እድሜ ባላት የጋዛ ከተማ የመኖሪያ ማማዎች እና ህንጻዎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ መስጊዶች እንዲሁም የመንግስት እና የግል ተቋማት ወደ ፍርስራሽነት እየተቀየሩ እንደሆነ ከስፍራው የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።

የእስራኤል ወታደራዊ ባለስልጣናት 350,000 ሰዎች ከተማዋን ለቀው መውጣታቸውን የገለጸ ቢሆንም፥ ሃማስ አሃዙን ከፍ በማድረግ 190,000 ሰዎች መፈናቀላቸውን ሲገልፅ፥ የተባበሩት መንግስታት በበኩሉ እስከ ባለፈው ሰኞ ድረስ 220,000 ፍልስጤማዊያን መሰደዳቸውን ይፋ አድርጓል።

ለዓለም አቀፍ ጣልቃ ገብነት የተደረገ ጥሪ
ተጠናክሮ በቀጠለው የእስራኤል ጥቃት መካከል በጋዛ የሚገኙ የእርዳታ ድርጅቶች የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መርማሪ ቡድን እስራኤል የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈፀመች ነው የሚል መደምደሚያ ላይ መድረሱን ተከትሎ አስቸኳይ ዓለም አቀፍ ጣልቃ ገብነት መጠየቃቸው የተነገረ ሲሆን፥ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መርማሪዎች ባቀረቡት ዝርዝር ሪፖርት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት እና እልቂት ማግስት በ1948 ዓ.ም. በፀደቀው ዓለም አቀፍ ስምምነት ላይ በተገለጸው መሰረት በጋዛ እየተፈጸመ ያለው ድርጊት የዘር ማጥፋት ነው ብለው መደምደማቸው ተገልጿል።

ስምምነቱ የዘር ማጥፋት ወንጀልን “የአንድን ብሔር፣ ጎሣ፣ ዘር ወይም ሃይማኖታዊ ቡድን በሙሉ ወይም በከፊል ለማጥፋት በማሰብ የሚፈጸም ወንጀል” በማለት የሚገልጽ ሲሆን፥ በኮሚሽኑ የወጣው አዲስ ሪፖርት በዓለም አቀፍ ሕግ ከተገለጹት አምስት የዘር ማጥፋት ድርጊቶች አራቱ እስራኤል ከሐማስ ጋር ጦርነት ውስጥ ከገባችበት መስከረም 2016 ዓ.ም. ወዲህ መፈጸማቸውን አመልክቷል።

ከተባበሩት መንግስታት አካላት ጋር ያላቸው ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሻከረ የመጣው የእስራኤል ባለስልጣናት ክሱን በተደጋጋሚ ውድቅ አድርገዋል።

በዶሃ ላይ የተፈጸመው የእስራኤል ጥቃት ውግዘት ማስከተሉ
በሌላ ዜና የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቮልከር ቱርክ እስራኤል ጳጉሜ 4 ቀን 2017 ዓ.ም. በኳታር ዋና ከተማ ዶሃ ውስጥ በተሰበሰቡት የሃማስ የፖለቲካ መሪዎች ላይ ያነጣጠረውን ጥቃት ያወገዙ ሲሆን፥ ማክሰኞ ዕለት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ወቅት ቱርክ ጥቃቱን “አስደንጋጭ የዓለም አቀፍ ህግ ጥሰት” እንደሆነ ጠቁመው፥ ‘በቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት ላይ የተፈፀመ ጥቃት ብሎም የሽምግልና እና የድርድር ሂደቶችን ታማኝነት የሚጎዳ ነው’ ሲሉ ገልጸውታል።

ከፍተኛ ኮሚሽነሩ ጥቃቱ በህይወት የመኖር መብትን የሚጋፋ እና የኳታርን የሰላም አደራዳሪነት ሚና የሚጎዳ መሆኑን ገልጸው፥ መንግስታት ውግዘቱን እንዲቀላቀሉ በማሳሰብ፥ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በሚደረጉ ዓለም አቀፍ ጥረቶች ላይ የተቃጣ ጥቃት ነው በማለት ገልጸዋል።

19 Sep 2025, 14:36