እስራኤል ሰሞኑን ባደረሰችው ከባድ የአየር ጥቃት በጋዛ የሚገኘው የአል ካውታር ግንብ መፍረሱ ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
እሁድ መስከረም 4 ቀን 2018 ዓ.ም. የእስራኤል የጦር አውሮፕላኖች በምዕራብ ጋዛ ከተማ የሚገኘውን ባለ ብዙ ወለል ህንፃ ማውደማቸውን ከአከባቢው የሚወጡ መረጃዎች የሚያሳዩ ሲሆን፥ ይህም ወታደራዊው ጥቃት በተጨባጭ ህዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መሆኑ ተገልጿል።
በህንፃው እና በአቅራቢያው ባሉ መጠለያዎች ውስጥ በደርዘን የሚቆጠሩ ቤተሰቦች ይኖሩ እንደነበር ነዋሪዎች የተናገሩ ሲሆን፥ የእስራኤል ጦር በበኩሉ የጥቃቱ ኢላማ ወይም አከባቢው የሃማስ መሠረተ ልማት እንደነበር የገለጸ ቢሆንም፥ የአካባቢው ምንጮች ግን በህንፃው ላይ የንግድ ቢሮዎች እንደነበሩ አስረድተዋል።
ባለፈው ሳምንት ሰኞ ዕለት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በቅርብ ቀናት በጋዛ ትላልቅ ሕንፃዎችን ያወደመው የአየር ጥቃት "የዋናው ጥቃት እና ከፍተኛ ዘመቻ መጀመሪያ ነው" ሲሉ መናገራቸው የሚታወስ ሲሆን፥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘመቻው የሐማስ የመጨረሻ ጠንካራ ይዞታን መቆጣጠር እንደሆነም ገልጸዋል።
በጋዛ ከተማ የእስራኤል ወታደሮች የሚሳኤል ጥቃት ከማድረጋቸው በፊት በደቡባዊ ሬማል ሰፈር የሚገኘውን የአል-ካውታር ግንብ ኢላማ በማድረግ ህንፃውን ማውደማቸው የተነገረ ሲሆን፥ የእስራኤል ጦር ነዋሪዎች ከአከባቢው ለቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ ከሰጠ በኋላ የአል-ካውታር ግንብ መፍረሱን የዓይን እማኞች ጠቁመው፥ የነፍስ አድን ሰራተኞች በህይወት የተረፉ ሰዎችን ከፍርስራሹ ሥር ሲፈልጉ እንደነበርም አክለው ገልጸዋል።
የእስራኤል ጦር ወታደሮች ሰሜናዊውን የከተማ መሃል ክፍል ለመያዝ እና ነዋሪዎችን ለማፈናቀል ባደረጉት ሰሞናዊ ጥቃት 53 ፍልስጤማውያን በጋዛ ሰርጥ ሲገደሉ፥ በጋዛ ከተማ የሚገኙ 16 ህንጻዎች ደግሞ መውደማቸው እየተነገረ ይገኛል።
በሃማስ የሚመራው የመንግስት ሚዲያ ጽህፈት ቤት እስራኤል የፈጸመችውን ጥቃት በጋዛ ከተማ የሚገኙ የመኖሪያ አካባቢዎችን ለማፍረስ የተደረገው ሰፊ ዘመቻ ነው ሲል የገለጸ ሲሆን፥ የቦምብ ድብደባው መጠናከር በርካታ ነዋሪዎች ወደ ደቡባዊው የከተማው ክፍል እንዲሰደዱ እንዳደረጋቸው የአከባቢው ባለስልጣናት ተናግረዋል።
ከዚህም ባሻገር የጋዛ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እሁድ ዕለት እንዳሳሰበው ለደም ምርመራዎች እና ለቫይረስ ምርመራዎች የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችን ጨምሮ የሕክምና እና የላቦራቶሪ ግብአቶች እጥረት መኖሩን ያስጠነቀቀ ሲሆን፥ ባለሥልጣናቱ ሰሞናዊው ጥቃት ለታካሚዎች እና ለቁስለኞች በሚደረገው የምርመራ ሂደት ላይ ተጽእኖ እያሳደረ መሆኑን ተናግረዋል።
በጋዛ የሚገኘው የመንግስት ሚዲያ ጽህፈት ቤት እስራኤል በሲቪል ሕንፃዎች ላይ ያደረሰችውን "ስልታዊ የቦምብ ጥቃት" በማውገዝ፥ የጥቃቱ ዓላማ “ማጥፋት እና የግዳጅ መፈናቀልን” ማስከተል ነው ብሏል።
እሁድ ዕለት በተፈጸመው ጥቃት ቢያንስ 35 ሰዎች በጋዛ ከተማ መገደላቸውን የህክምና ባለሙያዎች የገለጹ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ ሁለት ተጨማሪ ፍልስጤማውያን በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ምክንያት መሞታቸውን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር ገልፆ፥ የእስራኤል ጦርነት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በረሃብ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 422 መድረሱን ጠቁሟል።