የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ሃላፊ ‘ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች አደጋ ላይ ናቸው’ ማለታቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ሐሙስ ዕለት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲን በቅድስት መንበር ተቀብለው ያነጋገሩ ሲሆን፥ ኮሚሽነር ግራንዲ ከብፁእነታቸው ጋር ስለነበራቸው ቆይታ ለቫቲካን ዜና እንደተናገሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “ስደተኞችን እና ፍልሰተኞችን ለመደገፍ የቤተክርስቲያኑ ተሳትፎ፣ ጥብቅና እና ተግባር በርዕሰ ሊቃነ ጵጵስና ዘመናቸው ውስጥ እጅግ ጠንካራ እና ማዕከላዊ ተግባራት ሆነው እንደሚቀጥሉ በማረጋገጣቸው እጅግ በጣም መበረታታቸውን ገልጸዋል።
የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ ኮሚሽነሩ ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ባደረጉት ውይይት ‘እጅግ በጣም ውስብስብ ስለሆነው የዓለም ሁኔታ’ እና ለሰዎች መፈናቀል ምክንያት በሆኑት በርካታ ቀውሶች ላይ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸው፥ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ሆነው ሥራቸውን በጀመሩበት ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ60 እስከ 65 ሚሊዮን የሚጠጉ ስደተኞች እና ተፈናቃዮች ብቻ እንደነበሩ ይገመት እንደነበር አስታውሰው፥ ዛሬ ግን ይህ ቁጥር በእጥፍ አድጎ 120 ሚሊዮን ገደማ መድረሱን አሳስበዋል።
ይህ በጣም አስቸጋሪ ከሆነው የዓለማችን ክስተቶች ውስጥ አንዱ መሆኑን የጠቆሙት ግራንዲ፥ ስለዚህም ጉዳይ አንስተው ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጋር መወያየታቸውን አስታውሰዋል።
በጋዛ ውስጥ ያለው ሁኔታ
ከዚህም በተጨማሪ ተቋማቸው የሆነው የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን እንደሚፈለገው ተንቀሳቅሶ የመሥራት ሥልጣን በሌለው ስለጋዛ ጉዳይ አንስተው መወያየታቸውን አስታውሰው፥ ነገር ግን ህዝቡ ያለበት ከፍተኛ ስቃይ እና በደል እንደ ሰብአዊ ተቋም እጅግ በጣም እንደሚያስደነግጣቸው ለብፁእነታቸው መግለፃቸውን ተናግረዋል።
ከፍተኛ ኮሚሽነሩ በማከልም፥ ይህ በጋዛ ብቻ ሳይሆን በዌስት ባንክም ጭምር የፍልስጤም ህዝብ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ አስከፊ ተጽዕኖ ስለሚኖረው ብቻ ሳይሆን፥ የወደፊት የእስራኤል ደህንነት ላይም ጭምር ምን ይዞ እንደሚመጣ መታሰብ አለበት ብለዋል።
ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች አደጋ ላይ ናቸው
ይህ ጉዳይ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ ላይ ስለሚኖረው መዘዝ ያብራሩት ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ፥ በጋዛ ውስጥ እንደ እስራኤል እንዲሁም በዩክሬን ውስጥ ደግሞ እንደ ሩሲያ ያሉ በጣም ኃያላን አገሮች እየፈጠሩት ያሉት ቅድመ ሁኔታዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰብአዊ መብቶች የወደፊት እጣ ፈንታ እና ለሌሎች ሰብአዊ መብቶችም ጭምር እጅግ አደገኛ መሆናቸውን እንደሚያምኑ ገልጸዋል።
የተረሱ ቀውሶች
ዋና ኮሚሽነሩ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እና ቅድስት መንበር በዓለም ላይ ለተከሰቱት በርካታ “የተረሱ ቀውሶች” ላደረጉት ትኩረት ያላቸውን አድናቆት እና ምስጋና ገልጸው፥ በቫቲካን ዕድሉን አግኝተው ለመወያየት በሚመጡበት አጋጣሚ ሁሉ አርዕስት ሆነው የሚቀርቡት ውይይቶች ከዋና ዋናዎቹ የመገናኛ ብዙኃን ትኩረት እና አጀንዳ ስላላገኙት በዓለም ዙሪያ እየተሰቃዩ ለሚገኙት እና ስለተረሱት በርካታ ህዝቦች እንደሆነ አስረድተዋል።
ይህ ቦታ ሙሉ ግንዛቤ፣ ምርጥ መረጃ እና ተሳትፎ ካሉባቸው ጥቂት ቦታዎች አንዱ መሆኑን የጠቆሙት ኮሚሽነሩ፥ ከዚህም አልፎ በሱዳን፣ በኮንጎ እና በማይናማር በመሳሰሉ ስለተከሰቱት እና ማንም ስለማይናገራቸው ቀውሶች የሚነሱበት ሥፍራ እንደሆነም ጭምር አስረድተዋል።
የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን በከፍተኛ ሁኔታ በሚሳተፍባቸው በሁሉም ቦታዎች ቅድስት መንበር እና የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለምታደርግላቸው ድጋፍ ምስጋናቸውን ያቀረቡት አቶ ፊሊፖ በመጨረሻም፥ እንደ ድርጅት ከቅድስት መንበር እና ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በመሠረታዊ ደረጃም ሆነ በተቋም ደረጃ ባገኙት ድጋፍ እና አጋርነት እንዲሁም፥ ይህ በጎ አመለካከት እና አጋርነት ወደፊትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ስላገኙት ማረጋገጫ በእጅጉ እንደተበረታቱ ገልጸዋል።