ፈልግ

የተፈናቀሉ ፍልስጤማውያን በጋዛ ከተማ በድንኳን ካምፕ ውስጥ ተጠልለዋል የተፈናቀሉ ፍልስጤማውያን በጋዛ ከተማ በድንኳን ካምፕ ውስጥ ተጠልለዋል 

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያወጣው ሪፖርት እስራኤልን በጋዛ ውስጥ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽማለች በማለት መክሰሱ ተነገረ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መርማሪዎች እስራኤል በጋዛ ክልል የሚገኙ ፍልስጤማውያን ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽማለች ማለታቸው ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መርማሪ ኮሚሽን እስራኤል በጋዛ በሚገኙ ፍልስጤማውያን ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽማለች ሲል የከሰሰ ሲሆን፥ ማክሰኞ መስከረም 6 ቀን 2018 ዓ.ም. የተለቀቀው ይህ አዲስ ሪፖርት እስራኤል ከሐማስ ጋር ጦርነት ውስጥ ከገባችበት መስከረም 2016 ዓ.ም. ወዲህ የእስራኤል ሃይሎች በዓለም አቀፍ ሕግ ከተገለጹት አምስት የዘር ማጥፋት ድርጊቶች አራቱን ፈጽመዋል በማለት አመልክቷል።

እነዚህም አንድ ቡድን አባላት ላይ ግድያን፣ ከባድ የአካል እና የአእምሮ ጉዳት ማድረስ፣ ቡድኑን ለማጥፋት ሆን ተብሎ የታሰበባቸው ሁኔታዎችን መፍጠር እና እንዳይወልዱ ማድረግን ያካትታሉ በማለት ጠቅሷል።

ኮሚሽኑ እንደገለጸው፤ የአፈጻጸሙ ሁኔታ ሆን ተብሎ ታይቶ በማይታወቅ መጠን ፍልስጤማውያን ላይ ከባድ መሳሪያዎችን በመጠቀም መግደል እና ከፍተኛ ጉዳት ማድረስ፣ በሃይማኖታዊ፣ ባህላዊ እና የትምህርት ቦታዎች ላይ ስልታዊ እና ሰፊ ጥቃቶች መፈጸም እና ጋዛን በመክበብ ነዋሪን ማስራብ ተፈጽሟል ብሏል።

የእስራኤል መንግሥት በበኩሉ እርምጃው የሐማስን አቅም በማውደም ላይ እንጂ በጋዛ ሕዝብ ላይ ያነጣጠረ እንዳልሆነ አጥብቆ በመከራከር፥ ኃይሎቹም በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት እንደሚንቀሳቀሱ እና በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ይናገራል።

ሆኖም ግን የመርማሪ ኮሚሽኑ ሪፖርት በእስራኤል መሪዎች የተደረጉ ንግግሮች እና የእስራኤል ወታደራዊ ሃይሎች የሚወስዷቸው እርምጃዎች አካሄድን የዘር ማጥፋት ድርጊት ዓላማን የሚያሳዩ ማስረጃዎች አድርጎ ያቀረበ ሲሆን፥ የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ጥናቱን ውድቅ በማድረግ ሪፖርቱን “የተዛባ እና ሐሰት” ሲል በመጥራት፥ የኮሚሽኑ ሦስቱን ባለሙያዎች "የሐማስ ተላላኪዎች" ሆነው የሚያገለግሉ እና "በሐማስ ውሸት ላይ ሙሉ በሙሉ መሠረት ያደረጉ ናቸው ሲል ከሷል።

ሦስት አባላት ያሉት ገለልተኛው ዓለም አቀፍ መርማሪ ኮሚሽን የሚመራው በደቡብ አፍሪካዊቷ የቀድሞ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ጉዳዮች ኃላፊ እና የሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ወንጀል ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት በነበሩት ናቪ ፒላይ እንደሆን ተገልጿል።

በርካታ ዓለም አቀፍ እና የእስራኤል የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች፣ ገለልተኛ የተባበሩት መንግሥታት ተቋማት ባለሙያዎች እንዲሁም ምሑራን እስራኤል በጋዛ ፍልስጤማውያን ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽማለች ሲሉ መክሰሳቸው ይታወቃል።

እስራኤል ጥቅምት 26 ቀን 2016 ዓ.ም. በጋዛ ወታደራዊ ዘመቻውን የጀመረችው በሃማስ የሚመራው ታጣቂ ቡድን በደቡብ እስራኤል ላይ ባደረሰው ድንገተኛ ጥቃት ወደ 1,200 የሚጠጉ ሰዎች መሞታቸውን እና 251 ሰዎች ደግሞ መታገታቸውን ተከትሎ መሆኑን የእስራኤል ባለስልጣናት ገልጸዋል።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በጋዛ ቢያንስ 64,905 ሰዎች ተገድለዋል ሲል በሃማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ያስታወቀ ሲሆን፥ የተባበሩት መንግስታት እነዚህን አሃዞች በአጠቃላይ ሊታመን የሚችል መረጃ አድርጎ ይመለከታቸዋል።

ጦርነቱ አብዛኛውን የጋዛ ህዝብ እንዳፈናቀለ እና ከ90 በመቶ በላይ ቤቶች ብሎም መሰረታዊ መሰረተ ልማቶች ደግሞ ወድመዋል ተብሎ የሚገመት ሲሆን፥ ይሄንን ተከትሎ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሚደገፉ ባለሙያዎች በጋዛ ከተማ ረሃብ እንዳለ አውጀዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የእስራኤል ጦር ማክሰኞ ዕለት በጋዛ ከተማ ላይ ከፍተኛ የቦምብ ድብደባ የፈፀመ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ ‘ዘ ጀሩሳሌም ፖስት’ እንደዘገበው ጦሩ ሰኞ መገባደጃ ላይ የምድር ጥቃት መጀመሩን ዘግቧል።

17 Sep 2025, 13:45