ፈልግ

“ሴቶች ለሰላም” ኮንሰርት አቅራቢዎች፥ ፉሩዝ ራዛቪ፥ ፑሜዛ ማትሺኪዛ እና ሴሬና ማልፊ፤ “ሴቶች ለሰላም” ኮንሰርት አቅራቢዎች፥ ፉሩዝ ራዛቪ፥ ፑሜዛ ማትሺኪዛ እና ሴሬና ማልፊ፤ 

“ሴቶች ለሰላም” ኮንሰርት የተስፋ እና የሰብዓዊነት ድምፆችን ያሰባሰበ መሆኑ ተገለጸ

በዓለማችን ዕርቅን፣ ተስፋን፣ አብሮነትን እና ሰላምን ለማስፈን፥ “ሴቶች ለሰላም” በሚል መሪ ሃሳብ ከዓለም ዙሪያ የተውጣጡ ድምጾችን በአንድነት ያሰባሰበ ልዩ ኮንሰርት በሮም ቀርቧል። የኮንሰርቱ ውጥን “ኦፔራ”ን እና ታሪክን በማዋሃድ ሴቶች የሰላም ወኪሎች መሆናቸውን ለማሳየት ሲሆን፥ ሰላም ቅንጦት ሳይሆን ለሰው ልጅ አስፈላጊ በመሆኑ ሙዚቃን እንደ ዓለም አቀፋዊ ቋንቋ በመጠቀም ባሕሎችን በማገናኘት እና በማነቃቃት ግልጽ መልዕክት ለማስተላለፍ ያለመ እንደሆነ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ሴቶች ለሰላም” በሚል መሪ ሃሳብ በሮም ፋርኔዜ አዳራሽ ውስጥ ሰኞ መስከረም 12/2018 ዓ. ም. አመሻሽ ላይ ለታዳሚዎች የቀረበውን ኮንሰርት ያዘጋጀው “ኦፔራ ለሰላም” የተባለው ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ነው። ዝግጅቱ ከተለመደው ኮንሰርት የበለጠ መሳጭ ሆኖ የቀረበ ሲሆን፥ በሙዚቃ፣ በታሪክ እና በመድረክ ዲዛይን ጥምረት የሴቶችን ድምጽ የሚያደምቅ የጽናት፣ የእርቅ እና የተስፋ መልዕክት ያለው መሆኑ ታውቋል።

በዝግጅቱ የቫቲካን ዜና አገልግሎት የተገኘ ሲሆን፥ ድምጻዊያት ሴሬና ማልፊ፣ ፑሜዛ ማትሺኪዛ እና ፎሩዝ ራዛቪ የድርጅቱ መሥራች እና የሙዚቃ ዳይሬክተር በሆኑት በካማል ካን እና በኪነ-ጥበብ እና ፕሮዳክሽን ዳይሬክተር ሚሼል ኤል ጎውል በተጫወቱት ፒያኖ ታጅበዋል።

ሴሬና ማልፊ፣ በልምምድ ወት

የ “ኦፔራ ለሰላም” ዋና ዳይሬክተር እና ተባባሪ መሥራች ጁሊያ ላጋሁዜሬ ለቫቲካን ዜና እንደገለጹት፥ “ይህ ዝግጅት ኮንሰርት ብቻ ሳይሆን ለቀጣዩ ትውልድ አስገራሚ ተግባራትን ያከናወኑ በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ሴቶች ክብርን የምንሰጥበት ነው” ብለው፥ እንደዚህ ዓይነት መልዕክት በእንደዚህ ያለ አስፈላጊ ቦታ ላይ ማስተላለፍ መቻል ልዩ ዕድል ነው” ሲሉ አክለዋል።

“ጽንሰ-ሃሳባዊ ኮንሰርት” ለሰላም

ደቡብ አፍሪካዊቷ ሶፕራኖ ድምጻዊት ፑሜዛ ማትሺኪዛ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት እንደተናገረችው፥ “ሴቶች ለሰላም” ኮንሰርት የተለመደ ዝግጅት እንዳልሆነ ገልጻ፥ ብዙውን ጊዜ በኮንሰርቶች ውስጥ በቀጥታ የሚዜም መሆኑን እና ለአፈጻጸሙ የተዘጋጁ ጽሑፎች እንዳሉ በመግለጽ፥ “የ ‘ሴቶች ለሰላም’ የሰላም ጥረት በዚህ አስከፊ ጊዜ እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ ነው” በማለት ያስረዳች ሲሆን፥ ለማትሺኪዛ “ኦፔራ” ዘወትር የባሕል ብዝሃነት የሚያድግበት ቦታ እንደሆነ ታውቋል።

ጀርመን ውስጥ ልዩ ልዩ ዜግነት ካላቸው 34 ተባባሪዎቿ ጋር የነበራትን ልምድ በማስታወስ እንደተናገረችው፥ የ “ኦፔራ” ዝግጅት እነዚህን የጎሳ ልዩነቶችን ዘወትር ለማቃለል መቻሉን እና “ዓለም እንደዚህ ባለ አስጨናቂ እና አሳሳቢ ጊዜ ውስጥ ሲገኝ የሰላም ጥሪ የሚቀርብበት አስፈላጊ ጊዜ አሁን ነው” ብላለች።

ለምሽቱ ያበረከተችው አስተዋፅዖ ጥልቅ እና ግላዊ እንደ ሆነ የምትናገረው ማትሺኪዛ፥ ከሌሎች ሁለት አጋሮችዋ ጋር የትውልድ አገራቸው ሴቶችን እና የቆሙለትን ዓላማ እንደሚያከብሩ ገልጻ፥ የምትወክለውም ደቡብ አፍሪካዊቷን አክቲቪስት እና ዘፋኝ ሚርያም ማኬባን እንደሆነ በማስረዳት፥ ይህን ማድረግ ልማድ ባልሆነበት በዚህ ጊዜ ለሰላም የሚሟገቱ እና የሚቆሙ በርካታ ሰዎችን እንፈልጋለን” ስትል አስታውቃለች።

“የሙዚቃ ዝግጅቱ ዋና መልዕክት ሰላም፣ ሰላም፣ ሰላም ነው! ጦርነት ይብቃ! የጦር መሣሪያን እናስቀምጥ! የቦምብ ቁልፎችን በመዝጋት ሌሎች መንገዶችን እንፈልግ” ብላለች።

ሶፕራኖ ድምጻዊት ፑሜዛ ማትሺኪዛ በልምምድ ወቅት
ሶፕራኖ ድምጻዊት ፑሜዛ ማትሺኪዛ በልምምድ ወቅት

መልዕክት ያለው አርቲስት መሆን

ሶፕራኖ ድምጻዊት ኢራናዊት ፉሩዝ ራዛቪ፥ የ “ኦፔራ ለሰላም” ቡድን አባል መሆን ሥራዋን ብቻ ሳይሆን ማንነቷን የለወጣት መሆኑን ገልጻለችል።

የ ‘ኦፔራ ለሰላም’ አባል መሆን ትልቅ ነገር መሆኑን ያስታወሰችው ፉሩዝ ራዛቪ፥ “ምናልባት ከዚህ በፊት ድምጻዊ ነበርኩ፤ አሁን ግን መልዕክት ያለው አርቲስት ሆኛለሁ፤ ከሙዚቃ ቤተሰቤ፣ ከአማካሪዎቼ እና ከድምፅ አስተማሪዎቼ ጋር መገናኘት በሕይወቴ ውስጥ ትልቅ ለውጥ እንዳሳይ አድርጎኛል” ብላ፥ “በዚህ አጋጣሚ የሰላም እና የተስፋ መልዕክት ለማስተላለፍ እና ይህም በተለይም በዛሬው ዓለም እጅግ አስፈላጊ ነው ብዬ አስባለሁ” በማለት ተናግራለች።

ከተለያዩ ሀገራት ከተወጣጡ የሥራ ባልደረቦቿ ጋር መሥራት፥ ጉዞዋን እጅግ ከሚያበለጽጉ ሥራዎች መካከል አንዱ እንደሆነ የምትገልጸው ፉሩዝ ራዛቪ፥ በዘፈን ሥራዋ ከ43 በላይ ሀገራትን እንደጎበኘች፥ ይህም ዓይኖቿን እንደከፈተላት እና ስለተለያዩ ባሕሎች እንድትማር ያደረጋት መሆኑን አስረድታለች። “ኦፔራ ለሰላም” ቡድን ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተውጣጡ ብዙ ዘፋኞችን ያካተተ በመሆኑ ምስጋናዋና አቅርባ፥ ቡድኑ “ሚዲያው እንድናምን እንደሚፈልገው ሳይሆን እንደ ዓለም እርስ በርሳችን ያልተራራቅን መሆናችንን እንድንገነዘብ አድርጎናል” በማለት አስረድታለች።

ኢራን ውስጥ ለሚገኙ ሴቶች ባስተላለፈችው በጽናት የተሞላ መልዕክቷ፥ “ተስፋ አለ፤ ከብዙ ነገር ተርፈናል፤ አስቸጋሪ መንገዶችን ሁሌም አልፈናል፤ ኢራናውያን ሴቶች እስካሁን እንደማውቃቸው ጠንካራ ናቸው፤ ኃይላቸውን በማስተባበር መስዋዕትነት በመክፈል ሲታገሉለት የነበረውን ነገር በሙሉ የሚያገኙበት እና ፍላጎታቸው እውን የሚሆንበት ቀን በመጨረሻው ሰዓት ላይ ይመጣል” ስትል ተናግራለች።

“ምናልባት ዘፋኝ ከመሆኔ በፊት መልዕክት ያለኝ አርቲስት ነኝ፤ በተለይ በኢራን ውስጥ ለሚኖሩ ሴቶች ያለኝ መልዕክት፥ ‘ተስፋ አለ!’ የሚል ነው” ብላለች።

ድምጻዊያት ፉሩዝ ራዛቪ፥ እና ሴሬና ማልፊ፣ በልምምድ ወቅት
ድምጻዊያት ፉሩዝ ራዛቪ፥ እና ሴሬና ማልፊ፣ በልምምድ ወቅት

ጥበብ እንደ ዓለም አቀፍ ቋንቋ

ደቡብ አፍሪካዊቷ ሶፕራኖ ድምጻዊት ፑሜዛ ማትሺኪዛም፥ “ሥነ-ጥበብ፣ ሙዚቃ እና ኦፔራ አስፈላጊ ድልድዮች እና ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ናቸው” ስትል ትናግራ፥ “በሙዚቃ ወንድማማቾች እና እህትማማቾች እንሆናለን፣ እርስ በእርሳችን ስለ ባሕሎች እንማራለን፣ በሌላ መንገድ ሄጄ የማላውቀውን በዘፈን ምክንያት ወደ ብዙ አገሮች ሄጃለሁ፣ ሙዚቃ የዓለምን መስኮት ከፍቶልኝ እጅግ ብዙ ሰጥቶኛል” ስትል ተናግራለች።

የባህል ልዩነት መድረክ

ዝግጅቱ እና ሥነ-ጥበባዊ ንድፉ በአደራ የተሰጠው ሚሼል ኤል ጉውል፥ የሊባኖስን ቅርስ ወደ ፕሮጀክቱ በማምጣት የተለያዩ ባሕሎች የተስፋ እና የሰላም መልዕክቶቻቸውን በሙዚቃ እና በኦፔራ አንድ ላይ የሚያሰባስቡ መሆናቸን አስረድቷል።

“ሁሉም ሰው ‘ኦፔራ የጣሊያን ዘውግ ነው’ ብሎ ያስባል” ያለው ሚሼል ኤል ጉውል፥ ይህ ትክክል እንዳልሆነ ገልጾ፥ ኦፔራ በዓለም ዙሪያ ካሉት እያንዳንዱ አርቲስት ጋር አብሮ የሚያስተጋባ መሆኑን በማስረዳት፥ ፕሮጀክቱ ለባሕሎች የመናገር መድረክ እንደሚያመቻች፥ ልዩነቶቻቸውን እና ትግሎቻቸውን መድረክ ላይ በማቅረብ የተስፋ መልዕክት ማስተላለፋቸውን አስረድቷል።

ኤል ጎውል የትውልድ አገሩ ሊባኖስ ኩራት እና ግጭቶች በማጣመር እንደተናገረው፥ እንደ ሊባኖሳውያን ብዙ ችግሮችን ማለፋቸውን አስታውሶ፥ እንደ ስደተኛ ወደ ፓሪስ በመምጣት አዲስ ሕይወት መጀመሩን እና ስደተኛ ቢሆንም ሀገሩን ዘወትር በልቡ መያዙን ገልጿል። በሚያደርጋቸው ሥራዎች አገሩን መወከል በመቻሉ ደስተኛ መሆኑን ተናግሮ፥ “ሁላችንም በሰላም ልንኖር ይገባናል” ሲል አሳስቧል።

መሳቅ፣ በሕይወት መደሰት፣ ሙዚቃን መስማት በሁሉ ቦታ የሚታይ አለመሆኑን ገልጾ፥ አንዳንዶች ይህን ለቅንጦት ቢያደርጉትም ሌሎች ግን እንደማያደርጉት፥ ነገር ግን የበኩሉን በመወጣት ይህን እውን ለማድረግ ተስፋ እንዳለው ተናግሮ፥ ሰላም ለሰው ልጆች ቅንጦት ሳይሆን አስፈላጊ እና መብት መሆኑን በማስረዳት “ሁላችንም መሳቅ፣ በመደሰት እና ሙዚቃን ማዳመጥ ይገባናል” ሲል አጽንዖት ሰጥቷል።

የፕሮዳክሽን ዳይሬክተር ሚሼል ኤል ጎውል ከቡድኑ አባላት ጋር
የፕሮዳክሽን ዳይሬክተር ሚሼል ኤል ጎውል ከቡድኑ አባላት ጋር

የአምባሳደሮች ማህበረሰብ

“‘ኦፔራ ለሰላም’ ሕይወትን በኪነ-ጥበብ ለመለወጥ እና ማኅበረሰቡን ለማነሳሳት ባለው እምነት ላይ የተገነባ ነው” ስትል የገለጸችው ላጋሁዜሬ፥ ቡድኑ በባለሞያዎች ላይ ኢንቨስት እንደሚያደርግ እና ሥራዎቻቸውን እንዲያሳድጉ የሚረዳ ነገር ግን ዕርዳታው ለአገሮቻቸው ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ አምባሳደሮች እንዲሆኑ የሚጠይቅ መሆኑን ተናግራ፥ ይህም ለቀጣዩ ትውልድ አርአያ እንዲሆኑ ለማድረግ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ አስረድታለች።

ላጋሁዜሬ አክላም፥ ሮም ይህን መልዕክት ለማስተላለፍ ተስማሚ ቦታ እንደሆነች፥ በውስጧ ከፍተኛ አቅም ያላቸው የጥበብ ሰዎች መኖራቸውን እና በከተማዋ ውስጥ ድርጅት መመሥረታቸውን ተናግራ፥ “አርቲስቶቻችን ዓለም አቀፍ አምባሳደሮች በማድረግ ለቀጣዩ ትውልድ አርአያ ሆነው ለተሻለ ዓለም ድምጽ በመሆን መልሰው ያበረክታሉ” ስትል አስረድታለች።

የጋራ ጥሪ

“ሰላምን ማምጣት ይቻላል” ስትል አጥብቃ የተናገረችው ማትሺኪዛ፥ እርስ በርስ የተገናኘን በመሆናችን በአንዱ የዓለም ክፍል አንድ ነገር ቢከሰት ሁሉን ሰው ሊነካ እንደሚችል፥ ለጦር መሣሪያ ግዥ በትሪሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ከማውጣት ይልቅ በትምህርት ቤት እና በሆስፒታሎች ግንባታ ላይ ኢንቨስት ቢደረግ፥ ያም በሰው ልጆች ላይ የበላይነትን ለመቀዳጀት ሳይሆን ድህነትን ለመቀነስ የሚያስችል መሆኑን አስረድታለች።  

ራዛቪ በተስፋ በተሞላ ንግግሯ፥ “እንደ አርቲስቶች ሰዎችን አንድ ላይ ለማሰባሰብ፣ የበለጠ እንዲያስቡ እና በሰላም እንዲያምኑ ለማድረግ የሚያስችል አቅም አለን” ስትል ደምድማለች።

ሴሬና ማልፊ በሮም ልምምድ ላይ
ሴሬና ማልፊ በሮም ልምምድ ላይ

 

25 Sep 2025, 14:37