በሱዳን በተከሰተው የእርስ በርስ ግጭት ምክንያት ሰብዓዊ ቀውሱ እና የጦር መሳሪያ ዝውውር እየተባባሰ መሄዱ ተዘገበ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በሱዳን ጦር ሃይሎች (SAF) እና በፈጣን ድጋፍ ሰጪ ሃይሎች (RSF) መካከል እየተካሄደ ያለውን ጦርነት እያቀጣጠለ ያለው ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ንግድ እየተስፋፋ መምጣቱን ‘የተደራጀ ወንጀል መከላከል ዓለም አቀፋዊ ተነሳሽነት’ የተሰኘ ተቋም የጠቆመ ሲሆን፥ ተቋሙ ጥቅምት 10 ቀን 2018 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው ሪፖርት ሕገወጥ የኮንትሮባንድ ነጋዴዎቹ እና ወንጀለኛ ደላሎች በዳርፉር፣ በምስራቅ ቻድ እና በደቡባዊ ሊቢያ የነበሩ ሕገወጥ መንገዶችን እንደገና መጠቀም መጀመራቸውን በዝርዝር አቅርቧል።
ሰብአዊ ቀውሱ እየተባባሰ መሄዱ
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሱዳን ያለው ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱን የገለጸ ሲሆን፥ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት (OCHA) እንዳረጋገጠው 25 ሚሊዮን ሰዎች ወይም ከሱዳን ግማሽ ያህሉ ህዝብ ለከፍተኛ ረሃብ ወይም ድርቅ እየተጋለጠ መሆኑን ጠቁሟል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከዚህን በፊት መስከረም ወር ላይ ባወጣው ሪፖርት ግጭቱ ሚያዝያ 2015 ዓ.ም. ከተጀመረ ወዲህ ላለፉት ሶስት ዓመታት አስከፊ ሁኔታዎች መከሰታቸውን መግለጹ ይታወሳል።
ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው አካባቢዎች የዳርፉር እና ኮርዶፋን ግዛቶች ዋነኞቹ ሲሆኑ፥ በእነዚህ አከባቢዎች የጤና፣ የምግብ እና የንፁህ ውሃ የመሳሰሉ እጅግ አስፈላጊ አገልግሎቶች መቋረጣቸውን ጨምሮ መሰረተ ልማቶች መውደማቸውን እና መፍረሳቸውን የተባበሩት መንግስታት ገልጿል።
በሰሜን ዳርፉር የምትገኘው ኤል ፋሸር ከተማ በፈጣን ድጋፍ ሰጪ ሃይሎች መከበቧን ከስፍራው የሚወጡ መረጃዎች የሚያሳዩ ሲሆን፥ በአከባቢው በሚገኙ ሲቪሎች ላይ ወሲባዊ ጥቃት፣ የግዳጅ ምልመላ እና የዘፈቀደ እስራትን ጨምሮ የተለያዩ በደሎች እንደሚደርስባቸው ይፋ ያደረገው የመንግስታቱ ድርጅት ሪፖርት፥ መስከረም 10 በአል ፋሸር የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ግቢ ላይ ጥቃት እንደተፈጸመበት እና የተለያዩ ተሽከርካሪዎች፣ የእርዳታ አቅርቦቶች እና ቁሳቁሶች መውደማቸውን ገልጿል።
የተከፋፈለ ህዝብ
ካርቱምን እና ዳርፉርን የሚያገናኘው ቁልፍ የትራንስፖርት ማዕከል በሆነችው በአል ኦቤይድ አቅራቢያ በሚገኘው ደቡባዊ ኮርዶፋን ውስጥ እየተካሄደ ያለው ጦርነት ተባብሶ መቀጠሉ የተነገረ ሲሆን፥ በዚህም ምክንያት ለበርካታ ዓመታት ለአከባቢው የሰብዓዊ እርዳታ ማቅረብ እንዳልተቻለ ተገልጿል።
ከዚህም በተጨማሪ የዲሊንግ እና ካዱግሊ ከተሞች ከአንድ ዓመት በላይ በጦር ሃይሎች መከበባቸው እና በእርዳታ ሰራተኞች ላይ አፈና፣ እስራት እና ማስፈራራት እንደሚደርስ ተነግሯል።
በአከባቢው የተከሰተው የጎርፍ አደጋ ወሳኝ የሆኑ የአቅርቦት መስመሮችን በተለይም በዳርፉር የሚገኘውን ምስራቃዊ ኒያላን እና በርካታ የአካባቢው መንገዶችን ማውደሙ የተነገረ ሲሆን፥ ይህም የአከባቢውን ህዝብ ለኮሌራ እና ለወባ ወረርሽኝ መዳረጉ ተገልጿል።
እነዚህ በሽታዎች ካርቱምን ጨምሮ በሕይወት ለመቆየት የሚታገሉትን የአከባቢው ማህበረሰቦችን በእጅጉ እንደጎዳ፣ ብሎም ነዋሪዎች መብራት እና የውሃ አቅርቦትን ከመሳሰሉ መሠረታዊ አገልግሎቶች ለቀናት እንደሚቋረጡ የተገለጸ ሲሆን፥ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሪፖርት በመጨረሻም ምንም እንኳን በርካታ ተግዳሮቶች ቢኖሩም ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ወሳኝ የሆኑ የሰብአዊ እርዳታዎችን በአስተማማኝ ሁኔታ ሊደረስባቸው በሚችሉ አካባቢዎች ለሚገኙ ተፈናቃዮች እያቀረቡ እንደሆነ ገልጿል።