ፈልግ

የተጎጂዎች አስከሬን በሪዮ ዲ ጄኔሮ ጎዳና ላይ የተጎጂዎች አስከሬን በሪዮ ዲ ጄኔሮ ጎዳና ላይ   (ANSA)

በብራዚሏ ሪዮ ዲ ጄኔሮ ከተማ በተካሄደ ድንገተኛ ዘመቻ የሟቾች ቁጥር ቢያንስ 130 መድረሱ ተነገረ

የሪዮ ዲ ጄኔሮ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ኦራኒ ቴምፔስታ የከተማው አስተዳደር በአደገኛ ዕፅ ወንጀለኞች ላይ ባደረገው መጠነ ሰፊ የፖሊስ ዘመቻን ተከትሎ ሰላም፣ አንድነት እና የሰው ሕይወት እንዲጠበቅ ጥሪ አቅርበዋል።

አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ጥቅምት 18 ቀን 2018 ዓ.ም. ማክሰኞ ዕለት የብራዚሏ ከተማ ሪዮ ዲ ጄኔሮ ውስጥ ድሆች የሚኖሩባቸው ሁለት አካባቢዎች ፖሊስ “ኮንቴይመንት” ብሎ በሰየመው መጠነ ሰፊ ዘመቻ የተነሳ ጎዳናዎቿ በእሳት እና በሞቱ ሰዎች አስከሬን ተሞልቶ የነበረ ሲሆን፥ እስከ አሁን ድረስ ባለው መረጃ 130 ሰዎች መሞታቸው ይፋ ተደርጓል።

በሰሜን ሪዮ ዲ ጄኔሮ የድሆች መኖሪያ በሆኑት አሉማኦ እና ፔናህ አከባቢዎች የከተማው ፖሊስ እና የወንበዴ ቡድን አባላት ባካሄዱት ጦርነት ሊባል በሚችል ፍልሚያ ከሁለቱም ወገን ሰዎች መሞታቸው ተነግሯል።

በከተማይቱ ታሪክ ውስጥ እጅግ ደም አፋሳሽ ነው በተባለው በዚህ ዘመቻ ላይ በግዛቱ ውስጥ ያሉ 2500 የልዩ ሃይል መኮንኖች የተሳተፉ ሲሆን፥ ፖሊስ ዘመቻ የከፈተበት 'ኮማንዶ ቬርሜልሆ' የተባለው የወንበዴዎች ቡድን በብራዚል ለረዥም ዓመታት የቆየ አደገኛ የወንጀል ቡድን እንደሆነ ይነገራል።

የወንጀለኛ ቡድኑ ሥም በፖርቹጋልኛ "ቀዩ ዕዝ" በመባል የሚታወቅ ሲሆን፣ ብራዚልን እስከ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 1985 ድረስ ካስተዳደራት አምባገነኑ ወታደራዊ መንግሥት ዘመን ከተመሠረተው ከግራ ዘመም የእስረኞች ድርጅት ጋር እንደሚያያዝ ተገልጿል።

በዚህ ዋና ግቡን በአደንዛዥ ዕፅ እና የጦር መሳሪያ ዝውውር ላይ የተሳተፈውን የቡድኑን የግዛት መስፋፋት ለማስቆም በተደረገ ዘመቻ ከ100 በላይ ሰዎች መታሰራቸው ከአከባቢው የወጣ መረጃ ያመላክታል።

የብፁዕ ካርዲናል ቴምፔስታ ጥሪ
ይሄንን ተከትሎ በከተማዋ ሀዘኑ እና ውጥረቱ እየጨመረ በመምጣቱ የሪዮ ዴጄኔሮ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ኦራኒ ጆአዎ ቴምፔስታ ማክሰኞ ዕለት በሰጡት መግለጫ ‘ለተከሰተው ከፍተኛ ስቃይ ማዘናቸውን’ ገልጸው፥ “ሁከት እና ፍርሃት የከተማችንን ልብ አቁስሏል፣ ከበርካታ ቤትም ሰላምን ነጥቋል” ሲሉ በአጽንዖት ተናግረዋል።

እንዲህ ዓይነት አሳዛኝ ሁኔታ ሲያጋጥም ጥላቻን መንዛት እንደማይገባ እና በግዴለሽነት ምላሽ መስጠት እንደማይቻል ጠቅሰው፥ ሕይወት እና ሰብአዊ ክብር ፍጹም የሆኑ እሴቶች እንደሆኑ እና የሰው ልጅ ሕይወት የእግዚአብሔር ቅዱስ ስጦታ ስለሆነ ሁል ጊዜም ሊጠበቅ እና ሊከበር እንደሚገባ አሳስበዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ቴምፔስታ ለሪዮ ዲ ጄኔሮ ሕዝብ ባስተላለፉት የተስፋ መልዕክት “የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንደመሆናችን መጠን ሰላም ፈጣሪ እንድንሆን ተጠርተናል” ያሉ ሲሆን፥ ጥላቻን፣ ቂም በቀልን እና የህብረተሰቡን መዋቅር የሚበክል ግዴለሽነትን እንድናሸንፍ ተጠርተናል ብለዋል።

እርቅን ለማስፈን፣ እርስ በርስ ለመከባበር እና ከሁሉም በላይ ለህይወት ጥበቃ ለማድረግ፣ ፍትህን ለማስፈን እና ሰላማዊ ማህበረሰብን ለመገንባት የእያንዳንዱን ሰው ልጅ ክብር የሚያጎለብት በተለይም ድሃ እና በጣም ተጋላጭ የሆነውን የህብረተሰቡን ክፍል ለመጠበቅ በአስቸኳይ ኃይላችንን በጋራ ማሰባሰብ አለብን በማለት መክረዋል።

“ሁከትና ብጥብጥ እያለም ቢሆን ፍቅር እና መልካምነት ከየትኛውም ጥቃት የበለጠ ጠንካራ እንደሆኑ አምናለሁ” ያሉት ብፁዕ ካርዲናሉ፥ በመጨረሻም “የሕይወታችን ጌታ ልባችንን ይመልስልን፣ የዓመፅን ቁስሎች ፈውሶ የሰላሙ መሣሪያ ያድርገን” በማለት ደምድመዋል።

የተ. መ. ድ. ሰላም እና ተሀድሶ እንዲሰፍን ጥሪ ማቅረቡ
የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቮልከር ቱርክ ብራዚል በሃገሪቷ ውስጥ አጠቃላይ እና ውጤታማ የሆነ የፖሊስ አሰራር ማሻሻያ ተግባራዊ እንድታደርግ አሳስበው፥ እንደ ኮማንዶ ቬርሜልሆ ያሉ “አመጸኛ እና በደንብ የተደራጁ የወንጀል ቡድኖችን” ለመጋፈጥ የሚያጋጥሙትን ተግዳሮቶችን በማስታወስ፥ ‘ለበርካታ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው ረጅሙ የዘመቻ ዝርዝር እንዴት እንደሚካሄዱ ጥያቄዎችን ያስነሳል’ ብለዋል።

ኮሚሽነሩ ብራዚል “አስከፊ የጭካኔ መረቦችን እንድታመክን እና የሕግ አስከባሪ ተግባራት የኃይል አጠቃቀምን በተመለከተ ዓለም አቀፍ መመዘኛዎችን እንዲያከብሩ” የጠየቁ ሲሆን፥ በዘመቻዎቹ ላይ “ገለልተኛ እና ውጤታማ ምርመራዎች” እንዲደረግ እንዲሁም የተጎዱ ቤተሰቦች እና ማህበረሰቦች “ፍትህ እና ካሳ እንዲያገኙ” የሚያስችል ዘዴ እንዲፈጠር ጥሪ አቅርበው፥ “ዘረኝነትን፣ አድልዎ እና ኢፍትሃዊነትን የሚያራምድ ሥርዓት የሚያበቃበት ጊዜ አሁን ነው” ብለዋል።

የጠቅላይ ፍርድ ቤት ጣልቃ ገብነት
ይህ በእንዲህ እያለ የብራዚል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ስለዘመቻው፣ የኃይል አጠቃቀም እና የተጎጂ ቤተሰቦችን መርዳትን በተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያ እንዲሰጡ የከተማውን ገዢ ክላውዲዮ ካስትሮን የጠየቀ ሲሆን፥ የሃገሪቷ ፕሬዚዳንት ሉዊዝ ኢናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ በበኩላቸው የተደራጁ ወንጀሎች ቤተሰቦችን ማፍረስ፣ ነዋሪዎችን መጨቆን እና አደገኛ ዕፆችንና ዓመፅን በከተሞች የማስፋፋት ተግባራቸውን መቀጠላቸውን እንደማይቀበሉ ገልጸው፥ አክለዋውም “የፖሊስ መኮንኖችን፣ ሕፃናትን እና ንጹሐን ቤተሰቦችን ለአደጋ ሳይጋለጡ የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውሩን ዋና ክፍል ለመምታት ከጸጥታ ኃይሎች ጋር የተቀናጀ ጥረት” እንዲደረግ ጠይቀዋል።

31 Oct 2025, 13:37