ፈልግ

ተቃዋሚዎች የሞት ቅጣት እንዲቆም በአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፊት ለፊት ድምፃቸውን ሲያሰሙ ተቃዋሚዎች የሞት ቅጣት እንዲቆም በአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፊት ለፊት ድምፃቸውን ሲያሰሙ   (2021 Getty Images)

የሞት ቅጣትን የመቃወም ቀን 'እንቅፋቶች ቢኖሩም ጥረቶችን በእጥፍ የማሳደግ እድል' አለው ተባለ

ዘንድሮ በተከበረው ዓለም አቀፍ የሞት ቅጣትን የመቃወም ቀን ላይ መቀመጫውን በዩናይትድ ስቴትስ ያደረገው የካቶሊክ ንቅናቄ ትስስር ዋና ዳይሬክተር ክሪሳኔ ቫላንኮርት መርፊ በያዝነው ዓመት ምንም እንኳን የሞት ቅጣት ቁጥር ቢጨምርም፥ የሞት ቅጣትን ለማስቀረት የተደረጉ በርካታ አዎንታዊ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን ገልጸዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

እ.አ.አ. በ 2024 ዓ.ም. ከሁለት ሦስተኛ በላይ የሚሆኑት ሃገራት የሞት ቅጣትን ያስቀሩ ሲሆን፥ 145 ሃገራት ደግሞ በሕግም ሆነ በተግባር ማስወገዳቸው ተገልጿል።

እነዚህ ተግባራት ትልቅ መሻሻሎች ቢሆንም በዓለም ዙሪያ የተመዘገቡት የሞት ቅጣቶች በመጨመር በ 2024 ዓ.ም. 1,518 የደረሰ ሲሆን፥ ይህም ከ 2015 ዓ.ም. ወዲህ ከፍተኛው ቁጥር መሆኑ እና ከእነዚህም የሞት ቅጣቶች ውስጥ አብዛኞቹ የተፈጸሙት እንደ ቻይና፣ ኢራን፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ኢራቅ እና ዩናይትድ ስቴትስ ያሉ ሃገራት ውስጥ እንደሆነ ተነግሯል።

በየዓመቱ እንደ ጎረጎሳዊያኑ ጥቅምት 10 ላይ የሚከበረው ዓለም አቀፍ የሞት ቅጣትን የመቃወም ቀን ላይ ሞትን ለማስቆም በተደረገው ዓለም አቀፍ ጥረት የተገኘውን እድገት ለመገምገም እድል እንደሚሰጥ የተነገረ ሲሆን፥ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሞት ቅጣትን በተመለከተ ግንዛቤ ለመፍጠር በርካታ ሥራዎችን እየሰራ የሚገኘው ‘ካቶሊክ ሞቢላይዚንግ ኔትዎርክ’ (CMN) ወይም የካቶሊክ ንቅናቄ ትስስር ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ክሪሳን ቫላንኮርት መርፊ ጉዳዩን አስመልክተው እንደተናገሩት በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሞት ቅጣትን ለማስቆም በሚደረገው ጥረት በርካታ ሥራዎችን መስራታቸውን ገልጸው፥ በሃገሪቷ ውስጥ ከሚገኙት ግዛቶች ውስጥ ግማሽ ያህሉ የሞት ቅጣትን እንደሚተገብሩ እና ግማሾቹ ደግሞ የሞት ቅጣቱን ከሥርዓቶቻቸው ውስጥ ማስወገዳቸውን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በአሳዛኝ ሁኔታ በርካታ የሞት ቅጣቶች እየተፈጸሙ እንደሚገኝ የጠቆሙት ሃላፊዋ፥ አሁን ላይ እየታዩ ያሉት የፖለቲካ ትርክቶች ከባድ መሆናቸውን ገልጸው፥ ለእያንዳንዱ የሰው ልጅ ክብር ዋጋ መስጠት እንደሚገባ እና ይህም የሞት ቅጣታቸውን እየተጠባበቁ የሚገኙ ሰዎችን እንደሚያካትት አንስተው፥ ይህም በመሆኑ በሚደረገው ትግል ተስፋ መቁረጥ እንደማይገባ እና በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሞት ቅጣትን ለማስቆም የሚያደርጉትን ጥረት ወደ ፊት እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል።

መስከረም 30 ቀን 2018 ዓ.ም. አርብ ዕለት እንኳን በዩናይትድ ስቴትስ፣ ኢንዲያና ግዛት ውስጥ የሞት ቅጣት ሊፈጸም ዕቅድ ተይዞ የነበረ መሆኑን ያስታወሱት ሃላፊዋ፥ ይህ ወር በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ “ሕይወትን የማክበር ወር” ተብሎ እንደሚታሰብ ገልጸው፥ ይህም በመሆኑ ካቶሊኮች አምላክ የሰጠንን የሰው ልጆችን ሕይወት ከፅንስ ጀምሮ እስከ ተፈጥሯዊ ሞት ድረስ ለማክበር በድጋሚ ቃል እንዲገቡ ጥሪ አቅርበዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ወይዘሮ ክሪሳን በዚህ ወር ውስጥ ብቻ የሞት ቅጣት እንዲፈጸምባቸው ቀጠሮ የተያዘላቸው ስምንት ሰዎች መኖራቸውን አስታውሰው፥ በሰው ልጅ ክብር ላይ እንዲህ ያለ ግፍ ሲፈጸም ስናይ ሁሉንም የሰው ልጅ ህይወት ከማክበር ጋር ፍጹም የሚቃረን ተግባር መሆኑን እንረዳለን ብለዋል።

ቤተክርስቲያኗ በአሁኑ ጊዜ ልታደርጋቸው የሚገቡ ብዙ ፈታኝ ጉዳዮች እንዳሉባት የጠቆሙት ሃላፊዋ፥ ነገር ግን እነዚህ ጉዳዮች የሞት ቅጣትን የሚያስቆመውን የሰው ልጅ ሕይወት ጉዳይ እንደማያጠፋው ወይም እንደማያሳንስ ገልጸዋል።

በዚህ ዓመት ከፍተኛውን የሞት ቅጣት ካስመዘገበው የፍሎሪዳ ግዛት ብፁዓን ጳጳሳት ጀምሮ ቤተክርስቲያን ተቃውሞዋን ከረዥም ጊዜ ጀምሮ ግልፅ ማድረጓን ያነሱት ወይዘሮ ክሪሳን፥ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ያሉ ብፁዓን ጳጳሳትን ስናይ ለምሳሌ በዚህ ዓመት አብዛኛው የሞት ቅጣት በተፈጸመበት በፍሎሪዳ ግዛት ውስጥ ግድያዎችን ለመቃወም አንድ ግንባር መፍጠራቸውን አይተናል ያሉ ሲሆን፥ ህዝቡ ቅጣቱ እንዲቀንስ ወይም ምህረት እንዲደረግ ለግዛቱ ገዢ ጥሪ ማድረጉን አስታውሰው፥ ቤተክርስቲያን ለዚህ ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት መስጠቷን ያሳየናል ብለዋል።

ሃላፊዋ ባለፉት 15 እና 20 ዓመታት ውስጥ በየዓመቱ የሚፈጸሙ ግድያዎች በግማሽ በመቀነሳቸው የተገኘውን እድገት ጠቁመው፥ ይህ በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ ሳይሆን በሌሎች አገሮችም የተገኘ ስኬት መሆኑን ገልጸዋል።

የአሜሪካ ማህበረሰብ ለሞት ቅጣት ትዕግስት እያጣ መምጣቱን እና በዚህም እንደሚበረታቱ የገለጹት ወይዘሮ ክሪሳን፥ ምንም እንኳን የሞት ቅጣቶች እየበዙ ቢመጡም ከቁጥጥር ውጭ ናቸው ማለት አይቻልም ብለዋል።

በቅርቡ የተደረገው ጥናት የእሳቸውን ሃሳብ እንደሚያጠናክር የገለጹት ሃላፊዋ፥ ይህም በአሜሪካ ውስጥ የሞት ቅጣት ያለው ህዝባዊ ድጋፍ ከ1970ዎቹ ወዲህ ዝቅተኛው ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ያሳያል ብለዋል።

“አሁን የምናየው ወቅታዊ መጠነኛ እድገት አሳሳቢ ጉዳይ በመሆኑ ትግላችንን አጠናክረን እንቀጥላለን” ያሉት ወይዘሮ ክሪሳን፥ ወደ ፊት ሁኔታው እየተስተካከለ እንደሚሄድ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ የሞት ቅጣትን ወደ መጨረሻው ምዕራፍ ስናሸጋግረው ውዥንብር እና ፍሰቶች መኖራቸው አይቀርም ብለዋል።

የካቶሊክ ሞቢላይዚንግ ኔትዎርክ ዳይሬክተሯ አሁን ባለው የትራምፕ አስተዳደር “ሃይለኛ እና ድፍረት የተሞላበት ንግግርን” በማንሳት፥ አስተዳደሩ በፌዴራል ደረጃ የሞት ፍርዶችን እና ግድያዎችን ለመከታተል ያለውን ፍላጎት ለመጨረሻው ጊዜ በግልፅ አሳይቷል ብለዋል።

የቅጣት መቀነስን እና በነፃ መሰናበትን ጨምሮ የሞት ቅጣት እንዲቀር የሚሟገቱ ሰዎችን የሚደግፍ አጸፋዊ አዝማሚያ እንዳለ ያነሱት ሃላፊዋ ይህም ለእንቅስቃሴው ትልቅ ማበረታቻ እንደሆነ ጠቅሰው፥ ያም ሆኖ ግን ይህ ወቅት ለዩናይትድ ስቴትስ በጣም ፈታኝ ጊዜ እንደሆነ ገልጸዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ ህዝብ የሞት ቅጣትን በግልፅ ለማስቆም ድምፃቸውን አጠናክረው ማሰማታቸውን የሚቀጥሉበት ጊዜ እንደሆነ እና በሃገሪቷ ውስጥ ፍላጎቱ እንደሚታይ ገልጸው፥ የሞት ቅጣት የአንድ ወገን ጉዳይ ብቻ አለመሆኑን፥ ብሎም ሁለቱም ወገኖች ይህ የሕይወት ጉዳይ እንደሆነ እና ልንከታተለው የሚገባን ጉዳይ መሆኑን መረዳት ጀምረዋል ብለዋል።

ስለዚህ ጉዳዩ ከአሁን በኋላ የአንድ ፓርቲ ባለቤትነት ወይም ተራ ተራማጅ ወይም ሊበራል ሃሳብ ተደርጎ እንደማይቆጠር አመላክተው፥ ይህ በእውነቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የበለጠ ተቀባይነት ያለው ነገር እንደሆነ አብራርተዋል።

ወይዘሮ ክሪሳን መርፊ የሞት ቅጣት መጠነኛ ጭማሪ ማሳየቱን ተከትሎ የጸሎት ጥሪ ያደረጉትን የፍሎሪዳ ብፁዓን ጳጳሳትን ተነሳሽነት ሁሉም ሰው እንዲከተል በመጋበዝ፥ ይሄ ጉዳይ እንደ ቴክሳስ ባሉ በርካታ የሞት ቅጣቶች ባሉበት ግዛቶችም እንደሚስተዋል ጠቅሰው፥ የሞት ቅጣትን በመቃወም የዚያ ግዛት ብፁዓን ጳጳሳት አንድ ወጥ ጥሪ ማቅረባቸውን ካስታወሱ በኋላ በመጨረሻም፥ ቅዱስ አባታችን በቅርቡ ስለ ሞት ቅጣት መናገራቸውን እና የሕይወት ጉዳይ አድርገው ማንሳታቸውን በማስታወስ አበረታች እርምጃዎች እየታዩ እንደሆነ በመግለጽ አጠቃለዋል።

13 Oct 2025, 14:25