ፈልግ

የቦርጎ ላውዳቶ ሲ ከፍተኛ ትምህርት ማዕከል የቦርጎ ላውዳቶ ሲ ከፍተኛ ትምህርት ማዕከል  

ቫቲካን የአየር ንብረትን አስመልክቶ ያላት አስደናቂ የትምህርት ቁርጠኝነት ለሌሎች አርአያ እንደሆነ ተነገረ

የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ከፍተኛ ሥራ እየሰራ የሚገኘው ‘ኤርዝ ዴይ. ኦርግ’ (EARTHDAY.ORG) የተባለው ተቋም እና ዓለም አቀፋዊ የወጣቶች ንቅናቄ ቅድስት መንበር የአየር ንብረት ትምህርትን የኦፊሴላዊው የአየር ንብረት ፖሊሲዋ ማዕከል ለማድረግ የወሰነችውን ውሳኔ እንደሚያከብሩ ገልጸው፥ ይህ ቁርጠኝነት በፓሪስ ስምምነት ሥር ቫቲካን ግዛቷን እ.አ.አ. በ2035 የበካይ ጋዝ ልቀትን በ28 በመቶ ለመቀነስ ቃል የገባችበት ስምምነት ውስጥ መካተቱ ተገልጿል።

   አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ከዓለም አቀፍ የወጣቶች ንቅናቄዎች ጋር በመሆን ‘ኤርዝ ዴይ ዶት ኦርግ’ የተሰኘው የአየር ንብረት ብክለትን ለመከላከል እና ለምድራችን ጥበቃ እንዲደረግ እ.አ.አ. በ 1972 ዓ.ም. በሲቪል ማህበረሰብ የተቋቋመው መንግስታዊ ያልሆነ ተቋም ቅድስት መንበር የአየር ንብረት ትምህርትን ሃገር አቀፋዊ የአየር ንብረት ፖሊሲዋ ማእከል ለማድረግ ያሳየችውን ውሳኔ በደስታ እንደሚቀበሉ ገልጸው፥ መስከረም 6 ቀን 2018 ዓ.ም. ቫቲካን በፓሪሱ ስምምነት መሰረት በሀገር አቀፍ ደረጃ የተወሰነ አስተዋፅዖን (NDC) ካቀረበች በኋላ ተቋሙ ባወጣው መግለጫ መሰረት፥ ቅድስት መንበር ለተዋሃደ የስነ-ምህዳር ትምህርት ያላትን ፈር ቀዳጅ ቁርጠኝነት እንደ “ጠንካራ የሥነ ምግባር አመራር እና ለመላው የካቶሊክ ዓለም የተላለፈ ግልጽ መልዕክት አድርጎ እንደሚመለከተው ገልጿል።

ኤርዝ ዴይ ዶት ኦርግ (EARTHDAY.ORG) የምድራችንን ሥነ ምህዳር ለመጠበቅ አወንታዊ እርምጃ የሚመስዱ በ 192 ሃገራት ውስጥ በሚንቀሳቀሱ ከ150,000 በላይ ከሆኑ አጋሮች ጋር በመተባበር የአካባቢ ጥበቃ እንቅስቃሴ የሚያደርግ በዓለም ትልቁ ተቋም ሲሆን፥ ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ መሰረት ‘ይህ እርምጃ የአየር ንብረት ትምህርት ጥምረትን እና የዓለም ወጣቶች ስኬትን ይወክላል” በማለት ገልጿል።

በካቶሊክ ትምህርት ቤቶች ላይ ያለው ተጽእኖ
የአየር ንብረት ትምህርትን በማስቀደም “ከቫቲካን ድንበሮች ባሻገር የተዘረጋው” የዚህን እርምጃ አስፈላጊነት በማጉላት፥ የቅድስት መንበር ቁርጠኝነት “በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚገኙት ትምህርት ቤቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎች እና ደብሮች ላይ ትልቅ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር በመግለጽ፥ ይህም መሠረታዊ ሥነ-ምህዳር ከሥርዓተ ትምህርት እና በሚሊዮን ከሚቆጠሩ የማኅበረሰብ ሕይወት ጋር እንዲዋሃድ ያበረታታል ብሏል።

ይህ አዲሱ ቁርጠኝነት ለዓመታት የተደረጉ ንቅናቄዎች ላይ የተገነባ ሲሆን፥ የጥምረቱ ጥረቶች እ.አ.አ. በ 2019 ዓ.ም. ማድሪድ ውስጥ በተካሄደው 25ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በሆነው የኮፕ 25 ጉባኤ ላይ ኤርዝዴይ ዶት ኦርግ ከቅድስት መንበር፣ ከጣሊያን፣ ከሜክሲኮ እና ከተባበሩት መንግስታት ጽህፈት ቤት ጋር በጋራ ባዘጋጁት ይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ዓለም አቀፍ እውቅናን ማግኘቱ ተገልጿል።

ጋዜጣዊ መግለጫው በወቅቱ የተፈጠረው ጥምረት በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጠንካራ የምድር ቀን መልዕክቶች መጠናከሩን በማስታወስ፥ ከእሳቸው ሃዋሪያዊ መልዕክት ከሆነው ታሪካዊው ላውዳቶ ሲ እስከ ዛሬ ያለውን ቀጣይነት አጉልቶ ያሳያል ተብሏል።

የቦርጎ ላውዳቶ ሲ
መግለጫው በመቀጠል በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ መሪነት ተነሳሽነቱ ወደፊት ‘የቦርጎ ላውዳቶ ሲ’ ሲጀመር ተጨባጭ የሆነ ቅርፅ እንደሚኖረው ጠቅሶ፥ “የላውዳቶ ሲ ራዕይ ጠንካራ ማዕከል” እንደሚሆን እና ለተለያዩ የትምህርት ተቋማት ማዕከል እንዲሁም በተዋሃደ ስነ-ምህዳር ውስጥ ተግባራዊ የልምምድ ሥፍራ ይሆናል በማለት ገልጿል።

የኤርዝ ዴይ ዶት ኦርግ ፕሬዝዳንት የሆኑት ካትሊን ሮጀርስ በበኩላቸው ‘ይህ የፖሊሲ ማሻሻያ ብቻ ሳይሆን፤ የጋራ ራዕይን ተቋማዊ ማድረግ እንደሆነ’ ገልጸው፥ ከ ‘ኮፕ25’ ጀምሮ እስከ ቦርጎ ላውዳቶ ሲ' ድረስ ያለው እያንዳንዱ እርምጃ አብረዋቸው ከሚሰሩ በሚሊዮን በሚቆጠሩ ወጣቶች ትጋት እና ጥረት እዚህ መድረሱን የገለጹ ሲሆን፥ ቀላል የአየር ንብረት ትምህርት ጥያቄን ወደ ማይካድ ዓለም አቀፋዊ ተልዕኮ በመቀየራቸው ይህ ድል የወጣቶቹም ጭምር እንደሆነ ጠቁመዋል።

ለቅድስት መንበር ሙሉ ድጋፍ
ተቋማቸው የአየር ንብረት ትምህርትን በማሳደግ ረገድ መንግስታትን ለመርዳት ባለው ተልዕኮ መሰረት ወደፊት ለዚህ ታላቅ ንቅናቄ ተግባራዊነት ለቅድስት መንበር ሙሉ ድጋፉን እንደሚሰጥ ያረጋገጡት ፕረዚዳንቱ፥ ድርጅቱ ከቫቲካን በተጨማሪ በአርጀንቲና፣ ካምቦዲያ፣ ኮሎምቢያ፣ ኮስታ ሪካ፣ ዶሚኒካን ሪፐብሊክ፣ ጆርጂያ፣ ኬንያ እና ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ በተወሰኑ ሃገራት ተመሳሳይ ቁርጠኝነቶች መኖራቸውን አስታውቀዋል።

09 Oct 2025, 14:03