ፈልግ

በግብፅ፣ ሻርም አል-ሼይክ ከተማ ጥቅምት 3 ቀን 2018 ዓ.ም. በአሜሪካ አደራዳሪነት ለሚካሄደው የጋዛ የሰላም ጉባኤ ዝግጅት ሲደረግ በግብፅ፣ ሻርም አል-ሼይክ ከተማ ጥቅምት 3 ቀን 2018 ዓ.ም. በአሜሪካ አደራዳሪነት ለሚካሄደው የጋዛ የሰላም ጉባኤ ዝግጅት ሲደረግ   (AFP or licensors)

የጋዛ ጉባኤ ሰኞ ዕለት በግብፅ እንደሚካሄድ ተነገረ

በጋዛ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ለማስቆም ተብሎ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ከግብ ለማድረስ ያለመ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ሰኞ ዕለት በግብፅ የቀይ ባህር ሪዞርት ከተማ በሆነችው ሻርም አል-ሼይክ ውስጥ ሊካሄድ እንደሆነ ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በጋዛ እየተካሄደ ያለውን የእስራኤል - ሃማስ ጦርነት ለማስቆም በአሜሪካ ሃሳብ አመንጪነት ባለፈው ሳምንት ውስጥ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ለማጠናቀቅ ያለመ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ጥቅምት 3 ቀን 2018 ዓ.ም. በግብጽ እንደሚካሄድ የተነገረ ሲሆን፥ የግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አል ሲሲ እና የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ይሄንን የውይይት መድረክ በጋራ እንደሚመሩት እና ከ20 በላይ የሀገራት መሪዎች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል።

በዚህ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ እንደሚሳተፉበት በታቀደው የመሪዎች ጉባኤ በጋዛ ሰርጥ ያለውን ጦርነት ለማስቆም፣ ክልላዊ የሰላም ጥረቶችን ማበረታታት እና በመካከለኛው ምስራቅ አዲስ የጸጥታ እና የመረጋጋት ምዕራፍ ላይ ያተኩራል ተብሏል።

አርብ ዕለት ተግባራዊ መሆን የጀመረው በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ከሶስት ቀናት ከባድ ድርድር በኋላ የተደረሰ ስምምነት መሆኑ የሚታወስ ሲሆን፥ ድርድሩ በግብፅ፣ በኳታር፣ በቱርክ እና በዩናይትድ ስቴትስ ሸምጋይነት እንደተካሄደም ጭምር ይታወቃል።

የስምምነቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ የእስራኤል ወታደሮች ከጋዛ ከተማ፣ ራፋህ፣ ካን ዮኒስ እና ሰሜናዊ ጋዛ ለቆ መውጣትን ጨምሮ፣ አምስት የእርዳታ ማስተላለፊያ መንገዶችን መክፈት እንዲሁም ታጋቾችን እና እስረኞችን መፍታትን ያጠቃልላል ተብሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የእስራኤል ጦር ሲቪሎች በራሺድ እና በሳላህ አልዲን መንገዶች ሊጓዙ እንደሚችሉ ካወጀ በኋላ የተፈናቀሉ ፍልስጤማውያን ከደቡባዊው የግዛቱ ክፍል ወደ ሰሜን መመለስ በመጀመራቸው ግብፅ አስቸኳይ የምግብ እና የህክምና ቁሳቁሶችን ወደ ጋዛ መላክ እንደጀመረች ተገልጿል።

የተኩስ አቁም ስምምነት ቢደረግም፥ ቡድኑ ትጥቅ እስኪፈታ ድረስ እና ግዛቱ ከወታደራዊ ኃይል ነፃ እስከሚሆን ድረስ የእስራኤል ወታደሮች በሐማስ ላይ ያለውን ጫና ለማስቀጠል በጋዛ ውስጥ እንደሚቆዩ ታውቋል።

በሳምንቱ መጨረሻ ላይ የጋዛ ሲቪል መከላከያ ግጭቱ መስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ 9,500 ደብዛቸው የጠፉ ሰዎች ሪፖርቶች እንደደረሰው የገለጸ ሲሆን፥ የጋዛ ሲቪል መከላከያ ቃል አቀባይ የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ከእስራኤል ባለስልጣናት ጋር በመተባበር ስለጠፉት ሰዎች ሁኔታ ለመወሰን እንዲረዳቸው ጠይቀዋል።

የጋዛ የጤና ባለስልጣናት እንደገለፁት ከሁለት ዓመት በላይ በዘለቀው የእስራኤል ወታደራዊ ዘመቻ ከ67,000 በላይ ሰዎች መሞታቸው እና በግዛቱ ላይ ከባድ ረሃብ መድረሱን ይፋ አድርገዋል።

13 Oct 2025, 15:35