ከዌስት ባንክ ሰፋሪዎች ጥቃት በኋላ ክርስቲያኖች የተስፋን አስፈላጊነት መግለፃቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በፍልስጤም የእስራኤል ሰፋሪዎች በሌሎች ላይ የሚያደርሱት ጥቃት እና ሁከት ለአፍታ ሳይቋረጥ ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፥ ሰፋሪዎቹ በሚያደርሱት ተከታታይ ጥቃት ህንጻዎች እና መኪኖች በእሳት ወድመዋል፣ እንዲሁም የደረሱ ሰብሎች ጉዳት ደርሶባቸዋል። ይህም በመሆኑ ከኢየሩሳሌም በስተሰሜን እና ከራማላ በስተምስራቅ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ በምትገኘው፣ አሁንም ድረስ ሙሉ በሙሉ ክርስቲያኖች የሚኖሩባት እና የመጨረሻው የፍልስጤም መንደር በመባል በምትታወቀው በዚህች አነስተኛ መንደር ታይቤ ሰላም መጥፋቱ እየተነገረ ይገኛል።
በራማላ አቅራቢያ የምትገኘው አነስተኛ መንደር አቦድ ተወላጅ የሆኑት አባ ባሻር ፋዋድል “በቅርብ ቀናት ውስጥ እንኳን በሰፋሪዎች አዲስ ጥቃት ደርሶብናል” በማለት ለቫቲካን ዜና የተናገሩ ሲሆን፥ ካህኑ እ.አ.አ. ከ 2021 ዓ.ም. ጀምሮ የላቲን ሥርዓተ አምልኮን የምትከተል የታይቤ ቤተክርስቲያን ቁምስና ካህን ሆነው አገልግለዋል።
ከአንድ ሺህ በላይ ነዋሪዎች ያሏት ከተማዋ የሶስት አብያተ ክርስቲያናት ማለትም የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን፣ የመልካይቲክ ቤተክርስቲያን እና የላቲን-ሥርዓት አምልኮን የምትከተል የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መገኛ እንደሆነችም ጭምር ተነግሯል።
እየተባባሰ የመጣው ጥቃት
ሰሞኑን ሰፋሪዎቹ ባደረሱት ጥቃት የቁምስናው እና የምዕመናን ንብረት የሆነ አንድ ህንፃ እና ከፊት ለፊቱ ቆመው የነበሩ ሁለት መኪኖችን ማውደማቸውን የገለጹት አባ ፋዋድል፥ ጥቃት አድራሾቹ የመኪኖቹን ጎማዎች ቀድመው ማስተንፈሳቸውን፣ መስታወቱን፣ መስኮቶቹን ብሎም ሁሉንም ነገር እንደሰባበሩ ተናግረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በሁለት ቀናት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ የነዳጅ ማደያውን ማውደማቸውን እና በርካታ ነገር መዝረፋቸውን የጠቆሙት ካህኑ፥ እነዚህ የጥፋት እና የጥቃት ድርጊቶች ተቀባይነት የሌላቸው መሆኑን ገልጸው፥ እስራኤላውያን ይሄንን ጥቃት አጥብቀው ሊያወግዙት እንደሚገባ አሳስበዋል።
ከጥቂት ቀናት በፊት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በዌስት ባንክ መንደር ሰኞ ዕለት በአንዳንድ ሰፋሪዎች የተፈፀመውን ጥቃት “እፍኝ የማይሞሉ አክራሪ” ሃይሎች ያደረሱት ጥቃት በማለት የተቹ ሲሆን፥ አባ ፋዋድል ይሄንን አስመልክተው እንደተናገሩት “ቃላቶች ብዙ ትርጉም እንዳላቸው” ጠቁመው፥ ምክንያቱም "በዌስት ባንክ ውስጥ እየሆነ ያለው ነገር በእውነት ወንጀል ስለመሆኑ ተጨማሪ ማስረጃዎች ናቸው” በማለት አስረድተዋል።
ካህኑ በማከልም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡት ምላሽ “ተቀባይነት የሌለውን ይሄንን ጥቃት ለማስቆም ዓለም አቀፍ ግፊት እየተደረገ መሆኑን የሚያሳይ ይመስላል” በማለትም ሃሳባቸውን ገልጸዋል።
በቂ ያልሆነው የመኸር ወቅት
ምንም እንኳን ከመስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ተጠናክሮ የቀጠለ ቢሆንም፥ ለእነዚህ ተለዋዋጭ የሆኑ ጥቃቶች አዲስ ያልሆነችው የታይቤ መንደር በእስራኤላዊያን ሰፋሪዎች ለረጅም ጊዜያት ጥቃት ሲደርስባት እንደነበር መረጃዎች የሚያሳዩ ሲሆን፥ በተለይም በመኸር ወቅት ጥቃቱ እንደሚባባስ እና በዚያ አካባቢ በርካታ ፍልስጤማውያን ሰብል የሚሰበስቡበት ጊዜ ሲደርስ ወደ እርሻ መሬታቸው መጓዝ የሚኖርባቸው ቢሆንም፥ ነገር ግን ሰፋሪዎቹ መንገድ በመዝጋት እና ጥቃት በመፈጸም እንቅፋት እንደሚሆኑባቸው ገልጸዋል።
‘በፍልስጤማዊያን ዘንድ ታሪካዊ ጠቀሜታ ያለው የወይራ ዘይት ምርት በዚህ ዓመት በድርቅ እና በሰፋሪዎች ጥቃት ምክንያት በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል ተብሎ ይጠበቃል’ በማለት የገለጸው የፍልስጤም መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ‘አሪጅ’ (ARIJ) ሲሆን፥ ካህኑ በበኩላቸው “ወደ ወይራ ዛፍ እርሻዎቻችን ከሄድን ይህ ሦስተኛ ዓመታችን ነው” ሲሉ ችግሩን አመላክተዋል።
የፍርሃት ድባብ
ተደጋጋሚ ጥቃቶች በነዋሪዎች ላይ የፍርሃት ድባብ እንደፈጠሩ እና በአሁኑ ወቅት ነዋሪዎቹ በከፍተኛ ብስጭት ውስጥ እንደሚገኙ የጠቆሙት አባ ፋዋድል፥ በታይቤ ብቻ ሳይሆን በራማላ ምሥራቃዊ አካባቢዎች ከደረሱ በርካታ የእስራኤላዊያን ሰፋሪዎች ጥቃት በኋላ በርካታ ሰዎች በደህንነት እጦት ምክንያት ሀገሪቱን ለመልቀቅ እያሰቡ እንደሆነ ገልጸው፥ በታይቤ የዕለት ተዕለት ኑሮ በብዙ መዘጋት እና ወታደራዊ ገደቦች ምክንያት ለእገዳ መዳረጉን አስረድተዋል።
ይህ በስቃይ የሚታወቀው የአኗኗር ዘይቤ ባለፈው ሐምሌ ወር ላይ የሃይማኖት እና የሲቪል ተቋማትን ትኩረት መሳቡ የተነገረ ሲሆን፥ በዚህም ወቅት የቅድስት ሀገር የክርስቲያን አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች ከበርካታ የዲፕሎማቲክ ልዑካን ጋር በመሆን ድጋፋቸውን ለመግለጽ እና ሰላም እንዲሰፍን ለመጠየቅ መንደሩን መጎብኘታቸው ይታወሳል።
አባ ፋዋድል እንደገለጹት ልዑካኑ በወቅቱ ያስተላለፉት መልዕክት ሦስት ገጽታዎች የነበሩት ሲሆን፥ “በክርስቲያኖች መካከል የአንድነት እና የመቀራረብ ምልክት እንዲኖር፣ የዲፕሎማሲያዊ ትብብር እንዲደረግ እና በቅርቡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ላይ እሳት እስከማስነሳት የደረሰውን የሰፋሪዎች ጥቃት እንዲያስቆሙ ባለስልጣናት ላይ ጫና ለማሳደር የተደረገ ሙከራ መሆኑን ገልጸዋል።
የታይቤ ተስፋ
በዚህ የመከራ ጊዜ ጸሎት ማድረግን አጠናክሮ መቀጠል አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት የደብሩ ካህን፥ ጸሎት ተአምራትን እንደሚያደርግ፣ ሰዎችን እንደሚለውጥ እና እነዚህን ሁኔታዎች ወደ መልካም ነገር እንደሚለውጥ ጠቁመው፥ ከሁሉም በላይ ጸሎት ወደ ሰላም ይመራል ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በኢየሩሳሌም የላቲን ሥርዓተ አምልኮ የምትከተል ሃገረ ስብከት ድጋፍ የሚደረግላት አነስተኛ ደብር ስር ያሉትን የታይቤን ማህበረሰብን መደገፍ እንደሚገባ ያሳሰቡት ካህኑ፥ የእነዚህ ድጋፎች ግብ ለበርካታ ቤተሰቦች መረጋጋትን እና ገቢን ለማግኘት የሚረዱ አዳዲስ ሥራዎችን ለመፍጠር፣ ብሎም ለመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ገንዘብ ለማሰባሰብ እንደሆነም ጠቁመዋል።
ከምንም በላይ ተስፋን ፈጽሞ ማጣት እንደማይገባ ያሳሰቡት አባ ፋዋድል፥ በመጨረሻም የሰፋሪዎችን ጥቃት ከመፍራት ይልቅ ቤተክርስቲያን በሰዎች ልብ ውስጥ በሰላም እና በደህንነት መኖር እንደሚቻል የሚያሳይ "ተስፋን ለመስጠት" እንደተጠራች ገልጸው፥ “ተስፋዬ የትንሳኤው ተስፋ ነው” በማለት አጠቃለዋል።