ፈልግ

 ብራዚል፣ ኮሎምቢያን እና ፔሩን የሚያቋርጠው በዓለም ላይ በጣም ኃይለኛ የሆነው የአማዞን ወንዝ -የአየር ላይ እይታ ብራዚል፣ ኮሎምቢያን እና ፔሩን የሚያቋርጠው በዓለም ላይ በጣም ኃይለኛ የሆነው የአማዞን ወንዝ -የአየር ላይ እይታ  

በአማዞን ደን ላይ እየደረሰ ያለው ውድመት “ወደመጨረሻው ነጥብ” ተቃርቧል ተባለ

የዓለማችን ትልቁ ዝናባማው እና ጥቅጥቁ የአማዞን ደን በሚገኝበት የብራዚሏ ቤሌም ከተማ ከኅዳር 1 እስከ 12 ቀን 2018 ዓ.ም. 30ኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ30) የሚካሄድ ሲሆን፥ ይህ ተምሳሌታዊ ምርጫ አማዞን ዓለም አቀፍ ብዝሃ ሕይወትን እና የፕላኔቷን የአየር ንብረት ለመጠበቅ ያለውን ወሳኝ ሚና እንደሚያሳይ የተነገረ ሲሆን፥ የፈረንሣይ የልማት ምርምር ተቋም (IRD) ተመራማሪ እና የአማዞን የሳይንስ መድረክ አባል የሆኑት ጃን-ካርሎ ኢስፒኖዛ ስለዝግጅቱ ገለፃ አድርገዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የዓለም ሙቀት መጨመርን ወደ 1.5 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ለመገደብ በሚደረገው ጥረት ላይ ያተኩራል በተባለው በዚህ ጉባዔ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ ከግሉ ዘርፍ፣ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና ከመገናኛ ብዙኀን በሺዎች የሚቆጠሩ ተወካዮች የሚሳተፉበት እንደሆነ ተነግሯል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓመታዊ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ፣ የአየር ንብረት ለውጥን እንዴት መቋቋም እንደሚቻል ለመወያየት የሀገራት መሪዎችን፣ ሚኒስትሮችን እንዲሁም ተደራዳሪዎችን እና የተለያዩ ተዋንያንን በማሰባሰብ እንደሚያወያይ ይታወቃል።

አማዞን ከብራዚል ጥቅጥቅ ደን እስከ አንዲያን ደጋማ አካባቢዎች ከሆኑት ፔሩ እና ቦሊቪያ፣ ኢኳዶር፣ ኮሎምቢያ፣ ቬንዙዌላ፣ ጉያና፣ ሱሪናሜ እና ፍሬንች ጊያናን ጨምሮ ዘጠኝ ሃገራትን የሚያካትት ሲሆን፥ የብዝሀ ሕይወት ሀብት ባለቤት የሆነው አማዞን 6.9 ሚሊዮን ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሲሆን በተፈጥሮ ሀብቱ ላይ ጥገኛ የሆኑ ከ34 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መኖሪያ እና በዓለማችን እጅግ ሀይለኛ በሆነው ወንዝ ላይ ኑሮአቸውን የመሰረቱ ሰዎች እንደሚኖሩበት ይገለፃል።

የአየር ንብረት ለውጥን አስመልክቶ ከህዳር 1 እስከ 12 ቀን 2018 ዓ.ም. ድረስ የሚካሄደው 30ኛው የኮፕ 30 ጉባኤ የአማዞን ወንዝ ከአትላንቲክ ውቅያኖስ ጋር በሚገናኝበት እና በሰሜናዊ ምስራቅ ብራዚል በምትገኘው ቤሌም ከተማ እምብርት ላይ እንደሆነ ተገልጿል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በአማዞን ከተካሄደው የሲኖዶስ ውይይት በኋላ ባቀረቡት ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ “ስለሚያጓጓው የተፈጥሮ ውበቱ፣ ወንዞቹን እና ደኖቹን የሞላውን ብዝሃ ሕይወትን በትጋት ስለሚጠብቀው የአማዞን ክልል” በአድናቆት ማንሳታቸው ይታወሳል።

ሆኖም ከአምስት ዓመታት በኋላ የአማዞን ደን “መመለስ ወደማይቻልበት ነጥብ” እየደረሰ መምጣቱ የተነገረ ሲሆን፥ ከዚህ ባለፈም የደን መጨፍጨፍ እና የዓለም ሙቀት መጨመር ውጤቶች የማይቀለበሱ እየሆነ መምጣታቸው ተነግሯል።

የፍራንኮ-ፔሩ ተወላጅ የሆኑት የምርምር እና ልማት ኢንስቲትዩት (IRD) ተመራማሪው ዣን ካርሎ ኢስፒኖዛ “ይህ ቀደም ሲል በደቡባዊ አማዞን ተፋሰስ ላይ የተከሰተ ጉዳይ መሆኑን” እና እንደ ቦሊቪያ አማዞን ያሉ በደቡብ ክልሎች ያሉ ደኖች ከጊዜ ወደ ጊዜ ከባድ እና ረዥም ድርቅ እያጋጠማቸው እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፥ ከፍተኛ የሆነ የድርቅ ሪከርድ በ 2016 እና 2017 ዓ.ም. መመዝገቡን አስታውሰው ‘የብራዚል ሴራዶ ሳቫናን መምሰል ጀምረዋል’ ሲሉ በምሬት ተናግረዋል።

ምንም እንኳን የዚህ “የማይቀለበስ ነጥብ” ትክክለኛ ቀን በትክክል ለመለየት አስቸጋሪ ቢሆንም ሳይንቲስቶች ማለፍ የማይገባቸው ወሳኝ ደረጃዎችን ለይተው ማወቃቸውን እና ለደን መጨፍጨፍ የመጨረሻው ነጥብ 40 በመቶ እንደሚገመት አብራርተዋል።

ነገር ግን ከፈረንሳይ እና ከጀርመን የመሬት ስፋት ጋር የሚስተካከለው ከ17 እስከ 20 በመቶ የሚሆነው የአማዞን ደን መጨፍጨፉን የጠቆሙት ተመራማሪው፥ ከዚህም በተጨማሪ ሌላ 17 በመቶ የሚሆነው ክልል በሰዎች እንቅስቃሴ መሸፈናቸውን ጠቁመው፥ የዓለም ሙቀት መጨመርን በተመለከተ ካለፈው ምዕተ ዓመት ወዲህ ከፍተኛ ሙቀት የተመዘገበው ያለፉት ሁለት አስርት ዓመታት እንደነበር አስታውሰዋል።

የውሃ ዑደት ዋና ዋና ውጤቶች
ይህ ከፍተኛ የደን ጭፍጨፋ ብዙውን ጊዜ “የአረንጓዴ ምድር ሳንባ” ተብሎ የሚጠራውን ካርበን የመምጠጥ አቅምን በእጅጉ የቀነሰ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ በክልሉ የውሃ ዑደት ላይ አስከፊ ተጽእኖዎችን ማስከተሉ ተነግሯል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፊ ጥናት ያካሄዱት ኤስፒኖዛ በአማዞን ላይ ከሚጥለው ዝናብ ግማሽ ያህሉ በዛፎች አማካኝነት ወደ ከባቢ አየር የሚመለሰው በትነት እንደሆነ ጠቅሰው፥ የአማዞን ደን እርጥበትን በእራሱ ስነ-ምህዳር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ‘አንዴስ’ ተብሎ የሚጠራውን የሞቃታማ የበረዶ ግግር መገኛ ስፍራ፣ የአህጉሪቱን ደቡባዊ ክፍሎች እና ራቅ ያሉ አካባቢዎችን ጨምሮ በጣም ርቀው በሚገኙ ክልሎች ላይም ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ገልጸዋል።

ስለዚህ በብራዚል ተጠናክሮ የቀጠለው የደን መጨፍጨፍ አጎራባች ሃገራት በሆኑት ቦሊቪያ እና ፔሩ ያለውን ወቅታዊውን ብሎም የወደፊት የውሃ አቅርቦትን ለመወሰን ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት እና በመጨረሻም የምግብ ዋስትናቸውን አደጋ ላይ እንደሚጥል ተነግሯል።

ከኮፕ 30 የሚጠበቁ ነገሮች
ተመራማሪው ኤስፒኖዛ እ.አ.አ. በ 2019 ዓ.ም. የተጀመረው ሳይንሳዊ ተነሳሽነት የሆነው ‘የአማዞን ሳይንስ መድረክ’ አባል ሲሆኑ፥ ይህ ቡድን ወደ 300 የሚጠጉ ተመራማሪዎች ስለ አማዞን እውቀትን ለማቀናጀት እና ይሄንንም ለመጠበቅ መፍትሄዎችን የሚያዘጋጁት አባላት እንዳሉት ተነግሯል።

“የማይቀለበስ ነጥብ” ላይ እንዳይደርስ ከቀረቡት የመጀመሪያ ቁልፍ ተግባራት መካከል የደን ጭፍጨፋን ዜሮ ለማድረስ የታቀዱ ብሔራዊ ፖሊሲዎች ይገኙባቸዋል ተብሏል።

ሆኖም ተመራማሪው የአማዞን የደን ጭፍጨፋ በዓለም አቀፍ የገበያ ሃይሎች በሆኑት፥ በተለይም በአኩሪ አተር እና በወርቅ ኢንዱስትሪዎች የሚመራ በመሆኑ በአማዞን ሀገራት ሃላፊነት ብቻ ሊወሰን እንደማይችል አስታውሰዋል።

ሳይንቲስቶች በአማዞን ደኖች፣ በወንዞች እና በአንዲስ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያበላሹ የግድብ ግንባታ እና ሌሎች የመሠረተ ልማት ግንባታዎች እንዲቆሙ የጠየቁ ሲሆን፥ “አማዞን ከባህር ጠለል በላይ በ5,000 ሜትር ላይ ባለው እና አብዛኞቹ የአማዞንን ብዝሀ ህይወት የሚደግፈው ደለል የሚመነጩበት ከአንዲስ እንደሚጀምር የገለጹት ተመራማሪው፥ ከዚህም በተጨማሪ “በደን እና በከባቢ አየር መካከል ያለውን የአየር ንብረት ሚዛን ለመጠበቅ” የመጋቢነት ሥራቸው ወሳኝ የሆነውን የአገሬው ተወላጅ ግዛቶችን እና ነዋሪዎቻቸውን የመጠበቅን አስፈላጊነት አጉልተው አንስተዋል።

ባለፈው ሰኔ ብራዚሊያ ውስጥ የተካሄደውን ዓለም አቀፍ ስብሰባ ተከትሎ፥ ይህ የመጨረሻው ሃሳብ ከአምስት ወራት በፊት በአማዞን ተፋሰስ ሃገራት የሚገኙ የአከባቢው ድርጅቶች ያቀረቡትን ጥያቄ በማስተጋባት፥ በመጪው የኮፕ 30 ጉባኤ በተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ማዕቀፍ ውስጥ የበለጠ ውክልና እና የውሳኔ አሰጣጥ ላይ ተሳትፎን ከመጠየቅ ባሻገር፥ ከዘጠኙ የአማዞን ሀገራት የተውጣጡ መሪዎች ከአየር ንብረት ፋይናንስ ቀጥተኛ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጥያቄ እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል ተብሏል።

07 Nov 2025, 13:41