ፈልግ

ሰኞ ዕለት በኒው ዴልሂ በተከሰተው ከባድ ፍንዳታ አከባቢ ሰዎች ተሰብስበው  ሰኞ ዕለት በኒው ዴልሂ በተከሰተው ከባድ ፍንዳታ አከባቢ ሰዎች ተሰብስበው  

የህንድ ብፁዓን ጳጳሳት የኒው ዴልሂ ጥቃት ተከትሎ ለሰላም የጸሎት ጥሪ ማድረጋቸው ተነገረ

የህንድ ብፁዓን ጳጳሳት ሰኞ ዕለት ለስምንት ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነውን በኒው ዴልሂ የደረሰውን የአሸባሪዎች ጥቃት ተከትሎ ስለ ሰላም ጸሎት እንዲደረግ እና ለህዝቡ ጥበቃ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የህንድ ፖሊስ ስምንት ሰዎች በሞቱበት እና በርካቶች ደግሞ በቆሰሉበት ሰኞ ዕለት በኒው ዴልሂ በመኪና ላይ ከደረሰው የቦምብ ጥቃት ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ቢያንስ አምስት ሰዎችን በደቡባዊ ካሽሚር ግዛት በቁጥጥር ስር ማዋሉ የተዘገበ ሲሆን፥ የቦምብ ጥቃቱ የሽብር ተግባር እንደሆነ በመገለጽ በምርመራ ላይ የሚገኝ እንደሆነ እና ጥቃቱ ምናልባትም በህንድ እና በፓኪስታን መካከል ለረጅም ጊዜያት የዘለቀውን የካሽሚር ግዛት የይገባኛል ጥያቄ ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል እየተባለ ይገኛል።

ከዚህም በተጨማሪ የህንድ ጸጥታ ሃይሎች ከኒው ዴሊሂ ውጭ የሚንቀሳቀሰውን የአንድ “ተጠርጣሪ የሽብር ቡድን” ጥቃት እንዳከሸፉ፣ ሰባት ታጣቂዎችን በቁጥጥር ስር እንዳዋሉ እና በርካታ መሳሪያዎችን እንዲሁም ለቦምብ መስሪያ የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችን በቁጥጥር ስር እንዳዋሉ ገልጸዋል።

በሌላ ዜና ማክሰኞ ዕለት በፓኪስታን ዋና ከተማ ኢስላማባድ አጥፍቶ ጠፊዎች ባደረሱት ፍንዳታ በትንሹ 12 ሰዎች ሲሞቱ በደርዘን የሚቆጠሩት ደግሞ መቁሰላቸው የተገለጸ ሲሆን፥ በሁለቱ ሃገራት በደረሱት ጥቃቶች መካከል ቀጥተኛ ግንኙነት ባይኖርም በተከታታይ ቀናት የተፈጸመው የቦምብ ጥቃት በህንድ እና በፓኪስታን መካከል ያለውን ውጥረት ከፍ እንዳደረገው እየተገለጸ ይገኛል።

ረቡዕ ዕለት የቫቲካን ዜና ወኪል የሆነው ፊደስ የህንድ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ (CBCI) ጉዳዩን አስመልክተው መግለጫ ማውጣታቸውን የዘገበ ሲሆን፥ ብፁዓን ጳጳሳቱ በመግለጫቸው በኒው ዴልሂ በደረሰው ጥቃት ለሞቱት እና ለቆሰሉት ንጹሃን ሰዎች የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልጸው፥ ምዕመናን “ነቅተው እንዲጸልዩ” ጥሪ አቅርበዋል።

“ሀሳባችን እና ጸሎታችን በዚህ ጊዜ ከፍተኛ ስቃይ ከደረሰባቸው ሁሉ ጋር ነው” ያለው መግለጫው፥ ብፁዓን ጳጳሳቱ የተጎዱት በፍጥነት እንዲያገግሙ ጸሎታቸው እንደማይቋረጥ በመግለጽ፥ ከዚህም ባለፈ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ዜጎች “ነቅተው እንዲጠብቁ እና ማንኛውንም አጠራጣሪ ድርጊት ካስተዋሉ ለፖሊስ በፍጥነት እንዲያሳውቁ” አሳስበዋል።

ብፁዓን ጳጳሳቱ በመጨረሻም “በቤተክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ ውስጥ ወይም አቅራቢያ ስለሚደረጉ አጠራጣሪ ድርጊቶች ወይም የተጣሉ ዕቃዎችን ለሚመለከታቸው ባለ ሥልጣናት እንዲያሳውቁ” ለሰበካ ካህናት መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፥ “እንደ አንድ ማህበረሰብ አንድነታችንን እና ሰላማችንን በመጠበቅ፥ የዜጎችን ደህንነት እና ጸጥታ ለማስጠበቅ በጋራ በመስራት፤ ለምንወዳት ሀገራችን ሰላምና ደህንነት እንጸልይ” በማለት መግለጫቸውን አጠቃለዋል።

13 Nov 2025, 13:22