በናይጄሪያ በሶስት ቀናት ውስጥ ለሶስተኛ ጊዜ ጥቃት መድረሱ ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በናይጄሪያ ሰሜን ምዕራብ ግዛት ውስጥ በምትገኘው ኬቢ ከተማ ከ20 በላይ ልጃገረዶች ታፍነው ከተወሰዱ ከጥቂት ቀናት በኋላ በሃገሪቷ ሌላ የሃይል ጥቃት እና አፈና መፈጸሙ የተነገረ ሲሆን፥ ህዳር 9 ቀን 2018 ዓ.ም. ምሽት ላይ አንድ ታጣቂ ቡድን በኤኪቲ ግዛት ሥር በምትገኘው ኡርኩ ከተማ ውስጥ ወዳለው የጴንጤቆስጤ ቤተክርስቲያን በመግባት ሁለት ሰዎችን መግደላቸው ተገልጿል።
ተከታታይ ጥቃቶች
ከዚህኛው ጥቃት አንድ ቀን ቀደም ብሎ ህዳር 8 አንድ የወሮበሎች ቡድን በመንግስት በሚተዳደረው የልጃገረዶች አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ላይ ጥቃት መፈጸሙ የሚታወቅ ሲሆን፥ ከተማሪዎቹ ውስጥ ሁለቱ ለማምለጥ እንደቻሉ እና አንደኛዋ ደግሞ ቆስላ ወደ ቤቷ መግባት እንደቻለች ተገልጿል። ይህ በእንዲህ እያለ ከ24 ሰዓታት በኋላ በኩሼ ጉግዱ ማህበረሰብ ላይ ከባድ ጥቃት ተፈጽሞ አንድ የካዱና ሃገረ ስብከት ካህን መታገታቸው ተገልጿል።
ከእነዚህ ሁለት ጥቃቶች በኋላ የታጣቂዎች ቡድን ህዳር 9 በክዋራ ግዛት፣ ኦኬ ኢሴጉን ከተማ በሚገኘው የክርስቶስ ሐዋርያዊ ቤተክርስቲያን ላይ ጥቃት የፈጸሙ ሲሆን፥ ይህ አከባቢ የሃገሪቷን ሰሜናዊ እና ደቡባዊ ክፍል የሚያገናኝ እንደ መተላለፊያ ሆኖ የሚያገለግል ክልል እንደሆነ እና ጥቅጥቅ ያሉ ደኖች የሚገኙበት፣ መንገዶቹ ጨለማ የሆኑበት እንዲሁም አነስተኛ የፖሊስ አባላት ያሉበት አካባቢ በመሆኑ የሚሊሻዎች እና ወንጀለኞች ትኩረት ሆኖ ቆይቷል።
በቤተክርስቲያኑ ውስጥ በነበሩ የደህንነት ካሜራዎች የተነሱ ምስሎች ጥቃቱ እንዴት እንደተፈጠረ ለመረዳት የአከባቢውን ባለስልጣናት ማገዙ የተነገረ ሲሆን፥ የግዛቱ ፖሊስ አጥቂዎቹን “ሽፍቶች” ብሎ በመጥራት አጥር ላይ ወጥተው ወዲያው ተኩስ መክፈታቸውን ገልጿል።
በጥቃቱ ወቅት የቤተክርስቲያኑ መጋቢ ምዕመናን በአንዲት ትንሽ ክፍል ውስጥ እንዲደበቁ በማድረግ ክፍሉን እንደቆለፈ እና ሌሎች ሰዎች ደግሞ ከመሠዊያው ጀርባ እንዲሁም የተወሰኑት በመጋረጃው ስር መደበቃቸውን የደህንነት ካሜራው አሳይቷል።
አንዳንዶቹ ጭንብል ለብሰው የነበሩት ሽፍቶቹ ወደ ቤተክርስቲያኑ እንደገቡ ሴቶቹ ሲሸሹ የተዋቸውን ቦርሳዎች ሲሰበስቡ እንደነበር እና በኋላ ላይ ታጋቾችን “ማደን” እንደጀመሩ ታይቷል።
በዚህ ጥቃት ወጣት ወንድ እና ሴቶች፣ እንዲሁም አዛውንቶች በአጠቃላይ 35 ሰዎች ወደ ጫካ የተወሰዱ ሲሆን፥ ጥቃት አድራሾቹ አስለቃሽ ጭስ በመጠቀማቸው የጸጥታ ኃይሎች በፍጥነት ወደ ቤተክርስቲያኑ መግባት እንዳልቻሉም ተገልጿል።
በጥቃቱ መጨረሻ ሽፍቶቹ ለማምለጥ ሲሞክሩ ከጸጥታ አካላቱ ጋር በተፈጠረ የተኩስ ልውውጥ ከሽፍቶቹ ውስጥ አንድ ሰው መሞቱ እና ፖሊስ ምርመራ ከጀመረ በኋላ ደግሞ ሁለተኛ ሰው ጫካ ውስጥ ሞቶ መገኘቱ የተገለጸ ሲሆን፥ በሕይወት የተረፉ ሰዎች በቤተክርስቲያኑ ወለል ዙሪያ 100 የሚያህሉ የጥይት ሳጥኖችን ማየታቸውን አስታውሰዋል።
ወደ ፊት መጓዝ
የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ቦላ ቲኑቡ በኬቢ እና ኩዋራ ግዛቶች ውስጥ የተከሰቱትን ጥቃቶች ለመከታተል እና ጉዳዩን በቅርበት ለማየት ወደ ደቡብ አፍሪካ እና አንጎላ ሊያደርጉት የነበረውን ጉዞ ያራዘሙ ሲሆን፥ ፕረዚዳንቱ አፈና ከባድ ንግድ እየሆነባት በምትገኘው እና በአፍሪካ በሕዝብ ብዛት ቀዳሚ ስፍራ ላይ በምትገኘው ናይጄሪያ የጸጥታ እርምጃዎችን ለማጠናከር እየሰሩ እንደሆነ ገልጸዋል።