ሶሪያ የጦር ወንጀለኞችን ለመጀመሪያ ጊዜ ለፍርድ ማቅረብ መጀመሯ ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
እ.አ.አ. በ 2011 ዓ.ም. የፀደይ አብዮት በአረብ ሀገራት ሲፈነዳ ሶሪያም የአብዮቱ ሰለባ መሆኗ የሚታወስ ሲሆን፥ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የእርስ በርስ ጦርነት አመሳት፣ የግጭት አዙሪት ተጠናወታት፣ ኃያላን መንግስታትም የእጅ አዙር ጦርነታቸውን አፋፋሙ። የብዝሃንነቷ ማሳያዋ እና ተስፈኛዋ ሀገር ተስፋዋ ደበዘዘ። ጥንተ ምድር ሶሪያ የቀውስ፣ የብጥብጥ፣ የውድመት አብነት ሆነች። ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ናጣት። ዜጎቿ ለሞት፣ ለስደትና ለከፋ ሰብዓዊ ቀውስ ተዳረጉ።
ይሄን ተከትሎ በተጀመረው ወንጀልን የማጣራት ሂደት መጋቢት ወር ላይ የመንግስት ወታደሮች እና ከስልጣን የተወገዱት የሶሪያ ፕሬዚደንት በሽር አል አሳድ ደጋፊዎች በተሳተፉበት ግጭት ዙሪያ በመንግስት መሪነት ለወራት ሲካሄድ የነበረውን ምርመራ ተከትሎ የሶሪያ መንግስት ሚዲያ እንደዘገበው ማክሰኞ ዕለት 14 ተከሳሾች አሌፖ በሚገኘው የፍትህ ቤተ መንግስት መገኘታቸውን ገልጿል።
ፍርድ ቤቱ ከቀረቡት ተጠርጣሪዎች መካከል ሰባቱ የአል አሳድ ታማኝ ደጋፊዎች ሲሆኑ የተቀሩት ሰባቱ ደግሞ የአዲሱ መንግስት የጸጥታ ሃይሎች አባላት መሆናቸው ታውቋል።
ይህ ደም መፋሰስ የተከሰተው በሻራአ የሚመራው የሱኒ እስላማዊ አማጽያን ባለፈው ዓመት ታህሳስ ወር ላይ በሃገሪቱ አናሳ ቁጥር ያላቸው አላውያን ብሔረሰብ አባል የሆነውን አሳድን ከስልጣን ካስወገዱ በኋላ፣ ላለፉት 54 ዓመታት የዘለቀው የአሳድ ቤተሰብ የግዛት ዘመን ካበቃበት ጊዜ ጀምሮ ከነበሩት ግጭቶች አንዱ እንደሆነም ይታወቃል።
ተከሳሾቹ የእርስ በርስ ጦርነት በመቀሰቀስ፣ ሃገርን የመገንጠል ተግባር፣ የታቀደበት ግድያ መፈጸም እና ዘረፋ የሚሉ ክሶች የቀረበባቸው ሲሆን፥ ሁሉም ተከሳሾች ሲቪሎችን በመግደል እና በወታደራዊ ኬላዎች እና በመንግስት መስሪያ ቤቶች ላይ ጥቃት ያደረሱ ሚሊሻዎችን በማቋቋም ተከሰው ተጠይቀዋል።
የሮይተርስ ምርመራ እና የመንግስት ሪፖርት እንደሚያመለክተው የሶሪያ ወታደሮች ከየካቲት 28 እስከ 30 ቀን 2017 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ 1,500 የሚጠጉ የሶሪያ አላውያንን መግደላቸውን የገለጹ ሲሆን፥ ጥቃቱ የደረሰው የአሳድ ታማኝ የሆኑ የቀድሞ መኮንኖች ለቀናት በፈጸሙት ጥቃት 200 የጸጥታ ሃይል አባላትን መግደላቸውን ተከትሎ እንደሆነ ተገልጿል።
ባለሥልጣናቱ በሶሪያ ታሪክ የጸጥታ ሃይሎች በወንጀል ተከሰው ለፍርድ መቅረብ ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ ነገር እንደነበር ጠቁመው፥ የድብቁ አምባገነናዊ አገዛዝ የጨለማው ምዕራፍ በሚያበቃበት አዲስ ዘመን ተጠያቂነትን ለማስፈን ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ፕሬዚደንት ሻራ የአመጽ ተግባርን ሶሪያን አንድ የማድረግ ተልዕኮአቸውን አደጋ ላይ የሚጥል እንደሆነ በመግለጽ ያወገዙ ሲሆን፥ ተጠያቂዎችንም ለፍርድ ለማቅረብ ቃል ገብተዋል።