ፈልግ

ከዋናው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ30) ቀደም ብሎ የዓለም መሪዎች ቅድመ ስብሰባ ከጥቅምት 27-28 ድረስ በብራዚሏ ከተማ ቤሌም ተካሂዷል ከዋናው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ30) ቀደም ብሎ የዓለም መሪዎች ቅድመ ስብሰባ ከጥቅምት 27-28 ድረስ በብራዚሏ ከተማ ቤሌም ተካሂዷል   (AFP or licensors)

ከፓሪሱ ስምምነት ከአስር ዓመታት በኋላ በአማዞን የሚካሄድ የኮፕ 30 ጉባዔ

30ኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ30) በይፋ ሊከፈት ጥቂት ሰዓታት ብቻ በቀሩበት በአሁኑ ወቅት ከሁለት ቀናት ቀደም ብሎ ቅድመ ጉባኤ የሚኒስትሮች ስብሰባ በብራዚሏ ከተማ ቤሌም የተካሄደ ሲሆን፥ በዚህም በታሪክ ከተመዘገቡት ያሳለፍነው የአውሮፓዊያኑ 2024 ዓመት ምህረት በጣም ሞቃታማ ሆኖ መመዝገቡ እና ጉባዔው በቀዳሚነት የዓለም የሙቀት መጠንን ከኢንዱስትሪው አብዮት በፊት ወደ ነበረበት ወደ 1.5 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ለመመለስ በሚደረገው ጥረት ላይ እንደሚያተኩር ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ከኅዳር 1 እስከ 12 ቀን 2018 ዓ.ም. ድረስ በብራዚል፣ የአማዞን መግቢያ በሆነችው ቤሌም ከተማ የሚካሄደው 30ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓመታዊ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ30) የአየር ንብረት ለውጥን እንዴት መቋቋም እንደሚቻል ለመወያየት የሀገራት መሪዎችን፣ ሚኒስትሮችን እንዲሁም ተደራዳሪዎችን እና የተለያዩ ተዋንያንን እንደሚያሳትፍ የተገለጸ ሲሆን፥ ለዚህም ቅድመ ዝግጅት ከጥቅምት 27 – 28 ቀን 2018 ዓ.ም. ድረስ የዓለም መሪዎች እና ሚንስትሮች ቅድመ ስብሰባ ማድረጋቸው ተነግሯል።

ከህዳር 1 ጀምሮ ለሁለት ተከታታይ ሳምንታት ያህል በሚካሄደው በዚህ ጉባዔ በሺዎች የሚቆጠሩ የሲቪል ማህበረሰብ ተወካዮች፣ ሳይንቲስቶች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሰራተኞች፣ ወጣት አክቲቪስቶች እና ነጋዴዎች ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት እርምጃን ለማስተባበር በቤለም ከተማ ይሰባሰባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል።

ወደ 30 የሚጠጉ የሀገራት እና የመንግስታት መሪዎችን ጨምሮ 140 ያህል ልዑካን ወደስፍራው እንደሚያቀኑ የኮፕ30 አዘጋጆች ያረጋገጡ ሲሆን፥ ይህ አሃዝ ካለፉት ዓመታት የኮፕ ዝግጅቶች በእጅጉ ያነሰ እንደሆነም ጠቁመዋል።

ቻይና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሯን ዲንግ ዙዢያንግን እንደምትልክ ብታስታውቅም፥ በዓለም ላይ በዋናነት በካይ ጋዝን ከሚያመነጩት ሃገራት ውስጥ የአሜሪካ እና ቻይና ሀገራት መሪዎች በጉባዔው ላይ እንደማይገኙ የተገለጸ ሲሆን፥ ከአፍሪካ መሪዎች ውስጥ የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ፌሊክስ ሺሴ-ኬዲ፣ የኮንጎ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ዴኒስ ሳሱ፣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ እንዲሁም የአፍሪካ ልማት ባንክ ቡድን ፕሬዝዳንት እንደሚገኙበት ተገልጿል።

በሌላ በኩል ብሪታንያ በንጉስ ቻርለስ ሳልሳዊ እና በእንግሊዝ ጠቅላይ ሚንስትር ኬይር ስታርመር በተላኩት በልዑል ዊሊያም እንደምትወከል የተገለጸ ሲሆን፥ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ፣የጀርመኑ መራሂተ መንግስት ፍሬድሪክ ሜርዝ እና የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ፎን ደርም የአትላንቲክ ውቅያኖስን በማቋረጥ በስፍራው እንደሚገኙ ተመላክቷል።

ቅድስት መንበር በበኩሏ የቅድስት መንበር ዋና ጸሃፊ በሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በሚመራ እና በብራዚል የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ ተወካይ በሆኑት ሊቀ ጳጳስ ጂያም-ባቲስታ ዲኳትሮ በሚደገፍ አሥር የሚጠጉ የልዑካን ቡድን የተወከለች መሆኑ ተነግሯል።

ከፓሪስ ስምምነት በኋላ ያሉ አሥር ዓመታት
እ.አ.አ. በ 2015 በፓሪስ በተካሄደው የኮፕ 21 ጉባዔ ወቅት የተደረሰውን ስምምነት ለመገምገም የዘንድሮው ጉባኤ አጀንዳ ያደረገ ሲሆን፥ በወቅቱ 196 የሚሆኑ አካላት የዓለም የሙቀት መጠንን ከኢንዱስትሪው አብዮት በፊት ወደ ነበረበት ወደ 1.5 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ለመመለስ የተለያዩ እርምጃዎችን ለመተግበር መስማማታቸው ይታወሳል።

በእቅዱ መሠረት በኢንዱስትሪ የበለፀጉ ሀገራት ለደሀ አገሮች ከ 2020 እስከ 2025 ድረስ በየዓመቱ 100 ቢሊዮን ዶላር መስጠት የሚኖርባቸው ሲሆን፥ ሃገራት የበካይ ጋዝ ልቀት መጠናቸውን ለመቀነስ የማቀድ፣ የመተግበር እና ውጤቱንም ይፋ የማድረግ ኃላፊነት የተጣለባቸው ሲሆን ከጎርጎሮሳዊያኑ 2023 ዓ.ም. ጀምሮ በየአምስት ዓመቱ የሚመዘን እንደሆነ እና በፓሪስ ስምምነት መሠረት ከ2050 ጀምሮ ባሉት ሃምሳ ዓመታት ከካርቦን ዳይ ኦክሳይድ ነጻ የሆነ ዓለምን ለማየት ተስፋ ተደርጓል።

ይህ የብሔራዊ የአየር ንብረት ቁርጠኝነት ማሻሻያ የመጣው የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የአየር ንብረት ብክለትን ለማስተካከል ያለው ፍላጎት እያሽቆለቆለ ባለበት ወቅት መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ ሄክ የተሰኘው የፓሪስ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር እና የአካባቢ ጂኦፖለቲካል ስፔሻሊስት የሆኑት ፍራንሷ ገመኔ ጉዳዩን አስመልክተው እንደተናገሩት ‘በአሁኑ ወቅት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በጂኦፖለቲካ የተበታተነ ዓለም ውስጥ እንደምንገኝ’ ጠቁመው፥ በተለይም ከዩናይትድ ስቴትስ ጀምሮ ከአየር ንብረት እርምጃዎች የሚሸሹ ሕዝባዊ መንግሥታት እየበዙ መምጣታቸውን እያየን ነው ብለዋል።

ፕሮፌሰሯ በማከልም በአስር ዓመታት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ዶናልድ ትራምፕ ዩናይትድ ስቴትስን ከፓሪስ ስምምነት ማስወጣታቸውን አስታውሰው፥ ይህም ውሳኔ በሚቀጥለው ጥር ወር ላይ ከሚካሄደው ጉባዔ በኋላ ተግባራዊ እንደሚሆን አመላክተዋል።

በዩክሬን ውስጥ ያለው ጦርነት እና በመካከለኛው ምስራቅ ውስጥ ያለው ግጭት በአየር ንብረት ውይይቶች ውስጥ ታሪካዊ ሚና የሚጫወቱ የአውሮፓ ህብረት ሃገራትን ጨምሮ በአየር ንብረት ጉዳዮች ላይ በተወሰነ ደረጃ መበታተንን ያስከተለ ሲሆን፥ ከዚህም ባለፈ በአካባቢው የተከሰቱት ጦርነቶች በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ያስከተለው አስከፊ ውጤቶችም መኖራቸው ተነግሯል።

በዓለም ላይ በሁሉም ቦታ ማለት ይቻላል የአየር ንብረት ብክለትን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጫና መኖሩን የገለጹት ፕሮፌሰር ገመኔ፥ የኮፕ30 ጉባዔ ዋና ፈተና አሁን ባለው ጂኦፖለቲካዊ አውድ ውስጥ ለዓለም አቀፍ ትብብር አዲስ መነሳሳትን መፍጠር እንደሆነ አስረድተዋል።

ቤልጂየማዊቷ ተመራማሪ በዓለም አቀፍ ትብብር አማካይነት ባለፉት አስር ዓመታት የዓለም ሙቀት መጨመር ትንበያዎችን ከ 3.9 ድግሪ ሴንቲ ግሬድ ወደ 2.6 ድግሪ ሴንቲግሬድ በመቀነስ ከፓሪሱ ስምምነት የተገኙ ስኬቶችንም ያስታወሱ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ እ.አ.አ. ስምምነቱ በተፈረመበት በ 2015 ዓ.ም. ከዝቅተኛ የካርቦን ኢነርጂ ይልቅ በነዳጅ ላይ የተመረኮዙ በርካታ ኢንቬስትመንቶች እንደነበሩ እና ነገር ግን ይህ ጥምርታ ከ 2016 ዓ.ም. ጀምሮ መቀልበሱን አስታውሰው፥ ዝቅተኛ የካርቦን ኢነርጂ ኢንቬስትመንቶች ባለፉት አስርት ዓመታት ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ ማደጋቸውን አመላክተዋል።

የአየር ንብረት ፋይናንስ ለደቡቡ ዓለም
ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት የፋይናንስ ግብን ማጠናከር ሌላኛው አጀንዳ ሲሆን፥ የበለጸጉ ሀገራት በማደግ ላይ ለሚገኙ ሀገራት ቃል የገቧቸውን የገንዘብ ድጋፎች እንዲሰጡ ጠንካራ ጥሪ እንደሚያቀርቡ እና በዚህም ያደጉ ሀገራት በ2035 ለታዳጊ ሀገራት የሃይል ሽግግር እና ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ለመላመድ በዓመት 300 ቢሊዮን ዶላር የሚያሰባስቡ ይሆናል ተብሏል።

ፕሮፌሰር ፍራንሷ ገመኔ ዩናይትድ ስቴትስ ከማንኛውም ዓለም አቀፍ ዕርዳታ ሙሉ በሙሉ ራሷን ማግለሏን፣ የአውሮፓ መንግስታት ባዶ ካዝና ማቅረባቸውን እና ቻይናም ተጨማሪ መዋጮ ማድረግ ፍላጎቱ እንደሌላት አስታውሰው፥ የጂ 20 ሀገራት በተለይም ቻይና፣ አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት ሃገራት ከፍተኛ የካርቦን ልቀትን የሚያበረክቱ ሃገራት እንደሆኑ፥ ነገር ግን በማደግ ላይ ያሉ ሃገራት 4 በመቶ ብቻ እንደሚያበረክቱ አስታውሰው፥ በእውነቱ በደቡቡ ዓለም አቀፍ ክልል ውስጥ ላሉ ሃገራት እነዚህ ጉዳዮች በጣም ተስፋ አስቆራጭ መሆናቸውን በቁጭት ተናግረዋል።

በአማዞን ጠረፍ ላይ የሚካሄደው የኮፕ ጉባዔ
እ.አ.አ. በ 1992 ዓ.ም. በብራዚሏ ሪዮ ዴጄኔሮ በተካሄደው ‘ኤርዝ ሰሚት’ በተሰኘው ጉባዔ ላይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓመታዊ የአየር ንብረት ለውጥ የስምምነት ማዕቀፍ እና የኮፕ ጉባኤዎች መፈጠራቸው ይታወሳል።

ከሰላሳ ሶስት ዓመታት በኋላ የደቡብ አሜሪካ ትልቋ ሀገር ከዓለም ዙሪያ የተውጣጡ ዲፕሎማቶችን እና ሳይንቲስቶችን በጥቅጥቅ ደኖቿ ጫፍ ላይ ወደምትገኝ ከተማ በመቀበል የአየር ንብረት ታሪክን ለመስራት ጥረት የምታደርግ ሲሆን፥ በዚህ ጉባኤ ‘ትሮፒካል ፎረስት ፎሬቨር ፈንድ’ (TFFF) የተሰኘ በዓለም ዙሪያ ያሉ ሞቃታማ ደኖችን ለመጠበቅ የሚያግዝ የ100 ቢሊየን ፓውንድ የኢንቨስትመንት ፈንድ የሚያስጀምር በመሆኑ የቦታ ምርጫው ከተምሳሌትነቱ በላይ እንደሆነ ተነግሯል።

‘ፍትሃዊ ሽግግርን’ ማረጋገጥ
የኮፕ 30 ጉባዔ ‘ፍትሃዊ ሽግግር’ በሚለው ጽንሰ ሃሳብ ላይ ለማተኮር ማቀዱ የተነገረ ሲሆን፥ መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት በአየር ንብረት ለውጥ ሥራዎች ላይ ያላቸውን ሚና ማሳደግና የባለድርሻ አካላትን ትብብር ማጠናከር ትኩረት የተሰጠሰው ጉዳይ መሆኑም ተመላክቷል።

ለአፍሪካ ኮፕ 30 ለአየር ንብረት ለውጥ ፈተናዋ መፍትሄ የሚያመጡ ውሳኔዎችን የምትጠብቅበት መድረክም እንደሆነ የተነገረ ሲሆን፥ የአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ ተደራሽነት ማሳደግና ፍትሃዊነትን ማስፈን፣ ፍትሃዊ የኢነርጂ እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማረጋገጥ፣ ተፈጥሯዊ መፍትሄዎች፣ የብዝሃ ህይወት ጥበቃ፣ ኢኖቬሽን፣ የማይበገር አቅምን መገንባትና የዜጎች መብት ጥበቃ ከአፍሪካ አጀንዳዎች መካከል ይጠቀሳሉ።

አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ ዝቅተኛ ድርሻ ቢኖራትም ዋነኛ የችግሩ ገፈት ቀማሽ ስትሆን፥ ተከታታይ ድርቆች፣ ጎርፎችና በረሃማነት አበይት ፈተናዎቿ ናቸው። በዚህ ረገድ ኮፕ 30 ለአፍሪካ በማይበገር አቅም ግንባታ፣ መሰረተ ልማት አቅርቦትና የኢነርጂ ተደራሽነት ላይ የሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች እንደሚኖሩ ይጠበቃሉ ተብሏል።

10 Nov 2025, 13:56