ፈልግ

የአማዞን ወንዝ የአማዞን ወንዝ  

በአማዞን የሚገኙ የሆስፒታል ጀልባዎች የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስን ጥረት ማስቀጠላቸው ተነገረ

በብራዚል፣ ቤሌም ከተማ እየተካሄደ ከሚገኘው የኮፕ 30 ጉባዔ ጎን ለጎን የሆስፒታል ጀልባዎች በአማዞን ወንዝ ዳርቻ ተደርድረው በመቆም በጣም ለተቸገሩ ሰዎች የህክምና እርዳታ እየሰጡ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን፥ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ አነሳሽነት ሥራቸውን የጀመሩት እነዚህ ጀልባዎች በሁሉም የአማዞን ወንዝ አከባቢዎች በመንቀሳቀስ ከከተሞች ርቀው ለሚገኙ የአከባቢው ተወላጅ ማህበረሰቦች እና በወንዙ ዳር የሚኖሩ ሰዎችን ፍላጎት የሟሟላት ሥራ እንደሚሰሩ ዶክተር ፌሊፔ የሚባል አንድ በጎ ፈቃደኛ የህክምና ባለሙያ ምስክርነቱን ሰጥቷል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በጓጃራ ወንዝ ዳርቻ በርካታ ሰዎች ወደ ሳኦ ጆአ 23ኛ ባርኮ ሆስፒታል ለመጓዝ ሰልፍ የሚሰለፉ ሲሆን፥ እነዚህን ተሳፋሪዎች በአቅራቢያው ወደሚገኝ ደሴቶች የሚያጓጉዘው መደበኛ ጀልባ ሳይሆን፥ በምትኩ፣ የቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ ሆስፒታል ጀልባ እንደሆነ እና ይህ ጀልባ በአማዞን ወንዝ ላይ በመጓዝ በውሃ ላይ ጉዞ ብቻ የሚደረስባቸው በዓለም ትልቁ ጥቅጥቅ ጫካ ድረስ የሚዘልቅ ጀልባ እንደሆነ ተነግሯል።

ከብራዚል፣ ሚናስ ጌሬይስ ከተማ የመጣው የ28 ዓመቱ የዓይን ሐኪም ፌሊፔ ለህክምና ወደሚጎበኟቸው አንዳንድ ቦታዎች የሚወስዱ መንገዶች እንደሌሉ በመጥቀስ፥ አንዳንድ ጊዜ ጀልባዎቹ ማንንም ከመድረሳቸው በፊት ለሁለት ወይም ለሦስት ቀናት ያክል እንደሚጓዙ ገልጿል።

ፌሊፔ በቅዱስ ዮሃንስ 23ኛ ሆስፒታል ጀልባ ላይ ከተሳፈሩት በርካታ የበጎ ፈቃደኛ ዶክተሮች ውስጥ አንዱ ሲሆን፥ ይህ ተንሳፋፊ የህክምና ጀልባ በሁሉም የአማዞን ወንዞች ዳርቻ ለሚገኙ ህዝቦች እና ለተወላጅ ማህበረሰቦች ነፃ የህክምና አገልግሎት ከሚሰጡ ሶስት ተንሳፋፊ ሆስፒታሎች አንዱ ነው።

ሌላኛው ‘ባርኮ ፓፓ ፍራንሲስኮ’ የተሰኘው የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጀልባ በቤሌም፣ ፓራ ወንዝ ዳርቻ ላይ ከጎኑ የቆመ ሲሆን፥ እነዚህ ጀልባዎች የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ጀልባ ከተሰኘችው ሦስተኛዋ ጀልባ ጋር በመሆን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እ.አ.አ. በ 2013 ዓ.ም. በብራዚል በተካሄደው የዓለም ወጣቶች ቀን የአማዞን ህዝብ በሃይማኖታዊ ማህበረሰቦች ችላ እንዳይባል ምኞታቸውን በገለጹበት ወቅት የተበረከቱ እንደሆኑ ተገልጿል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በወቅቱ ወንድም ፍራንቺስኮ ቤሎቲን “በአማዞን ውስጥ ነህ?” ብለው እንደጠየቁ እና እሱም “አይደለሁም” ብሎ እንደመለሰ እና ብፁዕነታቸው “እዛ መሄድ አለብህ” ብለው እንደነገሩት፥ ይህም እሳቸው እስከ ዳርቻዎች ድረስ እንዲደርሱ የተደረገ ጥሪ እንደነበር እና ጥሪውም በ 2019 ዓ.ም. ምላሽ ማግኘቱ ይገለፃል።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እነዚህ ጀልባዎች የተገለሉ ሰዎችን የሚረዱ ዶክተሮችን፣ ነርሶችን እና በጎ ፈቃደኞችን በማቋቋም እስካሁን አንድ ሚሊዮን ሰዎች ተጠቃሚ አድርገዋል።

ፌሊፔ እንደተናገረው “እንደተለመደው ከሆነ አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች ወደ ሆስፒታል ይሄዳሉ፥ እዚህ ግን እኛ ወደ ሰዎቹ እንሄዳለን” በማለት ገልጿል።

የሳኦ ጆአ 23ኛ ጀልባ በአሁኑ ወቅት በኮፕ 30 ጉባዔ የመክፈቻ ቀናት በቤሌም አቅራቢያ የሚገኙ ማህበረሰቦችን በማገልገል ላይ የሚገኝ ሲሆን፥ የፓፓ ፍራንሲስኮ ጀልባም እንደዚሁ ወደ ጥቅጥቅ ጫካው ዘልቆ ለመግባት የሚቀጥለው ተልዕኮውን እየተጠባበቀ ይገኛል።

በአሁኑ ጊዜ በጀልባው ለሚሰጠው አገልግሎት ተጠቃሚ የሆነው የቤሌም ህዝብ ሲሆን፥ በኩሽና ውስጥ የሚገኙ ምግብ ሰሪዎች ጉዞውን ለሚጠባበቁ ሰዎች ምግብ በማብሰል ይጠመዳሉ። ከኩሽናው በተጨማሪ የምክር አገልግሎት የሚሰጡበት ክፍሎች የሚገኙ ሲሆን፥ ከእነዚህም ውስጥ የቀዶ ጥገና ክፍሎች፣ ላቦራቶሪዎች እና የመድሃኒት ክፍሎች ይገኙበታል።

“እዚህ ሁሉም ነገር አለን” ያለው ፌሊፔ፥ የምክር አገልግሎትን ጨምሮ፣ ከዓይን ሞራ ግርዶሽ ህክምና እስከ ጥቃቅን አጠቃላይ ህክምናዎች የሚሰጡባቸው የቀዶ ጥገና ህክምና እና የተለያዩ ምርመራዎችን እናደርጋለን ብሏል።

በጣም የተለመዱት በሽታዎች በከተሞች አካባቢ በቀላሉ ሊታከሙ የሚችሉ ነገር ግን ተደራሽ ባለመሆናቸው ተባብሰው የቀሩ ኢንፌክሽኖች፣ የአንጀት መውረድ፣ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ሲሆኑ፥ አንዳንድ ሰዎች ለመጀመሪያ ደረጃ ህክምና ዓመታትን እንደሚጠብቁ እና ሌሎች ደግሞ እነሱን ለማግኘት ሲሉ ለሰዓታት በትናንሽ ታንኳ እንደሚጓዙ የገለጸው ፌሊፔ፥ የበጎ ፈቃደኞቹ እና ሰራተኞቹ ልክ እንደ ቤታቸው ስለሚንከባከቡት ቦታው ንፁህ መሆኑንም ጭምር ገልጿል።

ፌሊፔ የሚያገለግላቸው ሰዎችን እንደሚወድ በመግለጽ፥ “እዚህ ያሉት ሰዎች በህይወቴ ካየኋቸው ደጋግ ሰዎች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው” ያለ ሲሆን፥ ሙሉ በሙሉ እንደሚያምኗቸው እና ካላቸው ጥቂት ነገር ብዙ እንደሚሰጧቸው ተናግሯል።

ትላንት አንድ ታካሚ ከዚህ በፊት አይቶት የማያውቀውን ፍሬ እንደሰጠው ያስታወሰው ፌሊፔ፥ ሌላኛው ደግሞ ከዚህ በፊት በጭራሽ አይቼው እንደማላውቅ መናገሬን በመስማቱ ብቻ ጃምቡ የሚባል የማደንዘዣ ስሜት ያለው በአፍ ውስጥ የሚደረግ ቅጠል እንዳመጣለት ገልፆ፥ “ወደ ኋላ እንድትመለስ የማያደርግህ እንደዚህ አይነት ፍቅር ነው” ብሏል።

በቀን እስከ አሥር የሚደርሱ የዓይን ቀዶ ሕክምናዎችን የሚያደርገውና በደርዘን የሚቆጠሩ ታካሚዎችን የሚከታተለው ፌሊፔ፥ ተሞክሮው እንክብካቤ የሚያገኙትን ብቻ ሳይሆን ሕክምናውን የሚሰጡ ሰዎችንም ጭምር እንደሚለውጥ ገልፆ፥ “ጉዳዩ ስለ በጎ አድራጎት ብቻ ሳይሆን፥ ለእነሱም ሆነ ለእኛ ስለ ለውጥ ነው” በማለት አብራርቷል።

የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ህልም
ፌሊፔ አጠገባቸው ወደቆመችው ወደ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጀልባ በማመላከት “ይህ የእሳቸው ሕልም ነበር” ያለ ሲሆን፥ ይህ ህልም በጂኦግራፊያዊ ብቻ ሳይሆን በማህበራዊ ደረጃም በሩቅ ያሉትን የመድረስ ህልም እንደሆነ በመግለጽ፥ እዚህ እየሆነ ያለው ነገር በህይወት ቢኖሩ ኖሮ በእውነት እንደሚያኮራቸው አልጠራጠርም ብሏል።

በቤሌም የኮፕ 30 ጉባኤ እየተካሄደ ባለበት በአሁኑ ወቅት፥ በአማዞን ወንዝ ላይ ያሉት ጀልባዎች በሰዎች እንክብካቤ እና በጋራ ቤታችን እንክብካቤ መካከል ትልቅ ግንኙነት እንዳለ ለተሰብሳቢዎቹ ያስታውሳሉ ያለው ፌሊፔ፥ ኮፕ ስለ ለውጥ የሚያወሳ ጉባዔ እንደሆነ ጠቅሶ፥ ሁላችንም የተለያየን መሆናችንን ብናውቅም፥ ነገር ግን ደግነት፣ አንዳችን ለሌላችን እንዲሁም ለፍጥረት የምናደርገው እንክብካቤ አንድ ላይ የሚያገናኘን ነገር እንደሆነ በማስታወስ፥ “ይህ ጀልባም የዚያ ግንኙነት ማረጋገጫ ነው” በማለት በአጽንዖት ገልጿል።

ፌሊፔ የአስር ቀናት ጉዞው በቅርቡ ቢያበቃም፥ ነገር ግን ቀጣዩ ተልዕኮ መቼ እንደሚሆን እንደሚያጓጓው በመግለጽ፥ በዚህም ምክንያት ቤት እንደደረሰ የሚቀጥለውን ተልዕኮ መፈለግ እንደሚጀምር በፈገግታ አስታውሶ፥ ይህ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ አስደናቂ ቅርስ ስለሆነ መቼም ቢሆን
እንዲያበቃ እንደማይፈልግ ገልፆ፥ “ብፁዕነታቸው አሁንም ድረስ እዚህ፥ በአማዞን እምብርት ላይ አሉ” በማለት አጠቃሏል።

17 Nov 2025, 16:46