ፈልግ

ጋዛ ጋዛ   (AFP or licensors)

የጎረጎሳዊያኑ 2025 ለጋዜጠኞች አስቸጋሪ ዓመት እንደነበረ ተገለጸ

ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን የጎረጎሳዊያኑ 2025 ዓመት ለጋዜጠኞች አስቸጋሪ ዓመት እንደነበረ እንዲሁም ጥላቻ እና ወንጀለኞችን አለመቅጣት በስፋት የታየበት ዓመት መሆኑን በመግለጽ፥ በዚህ ዓመት የተገደሉትን የጋዜጠኞች ቁጥር የሚዘረዝር ሪፖርት ማውጣቱ ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በግጭት፣ በተደራጁ ወንጀሎች እና በጋዜጠኞች ላይ ያለው ጥላቻ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣበት ይህ ዓመት አሳዛኝ ጉዳቶችን ማስከተሉ በሪፖርቱ የተገለጸ ሲሆን፥ በዚሁ ዓመት ብቻ 67 ጋዜጠኞች መገደላቸውን፣ 503ቱ መታሰራቸውን፣ 135ቱ የደረሱበት አለመታወቁን እና 20 ጋዜጠኞች ደግሞ መታገታቸውን ይፋ አድርጓል።

ሰሞኑን በድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን በወጣው በዚህ ዓመታዊ ሪፖርት ላይ የቀረቡት እነዚህ አኃዞች በጦርነት የተጎዱ ሰዎችን ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፥ ሆን ተብሎ እውነትን ለመናገር የተነሱ ድምፆችን ዝም ለማሰኘት የተደረጉ አሳዛኝ ክስተቶችንም ያመላክታሉ ተብሏል።

“ጋዜጠኞቹ ሞተው ሳይሆን ተገድለው ነው” የሚለው ይህ ሪፖርት፥ ይህ አገላለጽ በሚዲያ ባለሙያዎች ላይ የሚፈጸመው ግፍ በአጋጣሚ ሳይሆን ሆን ተብሎ የሚፈጸምበትን እውነታ እንደሚያሳይ የተገለጸ ሲሆን፥ ይህም ስልታዊ ድርጊት የሚፈጸመው ነፃ እና ትክክለኛ መረጃ ብዙ ነገር ሊገልጥ ይችላል ብለው በሚፈሩ ሰዎች እንደሆነም ተመላክቷል።

በዚህ ዓመት ከተገደሉት ጋዜጠኞች መካከል ግማሽ ያህሉ ወይም 43 በመቶው እንደ ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን ገለጻ የእስራኤል ወታደሮች የሚዲያ ባለሙያዎችን በተደጋጋሚ ዒላማ ባደረጉበት የጋዛ ጦርነት ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን፥ ይህም የሚያሳየው እውነታውን መዘገብ ከግጭቱም በላይ አደገኛ የሆነበት ክልል መሆኑን ነው ተብሏል።

ሆኖም ግን ይህ የተከሰተው በጋዛ ብቻ ሳይሆን፥ ከዩክሬን እስከ ሱዳን፣ ከየመን እስከ ሶሪያ ተመሳሳይ ድርጊት መፈጸሙን የጠቆመው ሪፖርቱ፥ በእነዚህ አከባቢዎች በርካታ ጋዜጠኞች እንደጠፉ፣ እንደታሰሩ ወይም የወታደራዊ እና አነስተኛ ቡድኖች ቀጥተኛ ዒላማ መሆናቸውን ገልጿል።

እነዚህ ጉዳቶች በጦር ግንባር ዘገባ ወቅት በአጋጣሚ የሚከሰቱ ጉዳቶች አለመሆናቸውን አጽንዖት የሰጠው የድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን ሪፖርት፥ ነገር ግን ምስክሮችን ለማጥፋት በታቀደ ሁኔታ የተፈጸሙ ድርጊቶች መሆናቸውን አመልክቷል።

ይህ ጉዳይ በእነዚህ አከባቢዎች ብቻ የሚያበቃ ሳይሆን ከውቅያኖስ ማዶ በመሻገር ሌላ በላቲን አሜሪካ፣ በተለይም በሜክሲኮ ቢያንስ ዘጠኝ ጋዜጠኞች መገደላቸውን የገለጸ ሲሆን፥ በጋዜጠኞች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት የራሱ አስከፊ አመክንዮ እንዳለው አብራርቷል።

ሪፖርቱ ከዚህም በተጨማሪ የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎች፣ በሙስና የተዘፈቁ የአካባቢ ባለስልጣናት እና ሥር የሰደዱ የወንጀል ቡድኖች እውነትን መመርመር ብዙውን ጊዜ የሞት ፍርድ የሚያስቀጣበትን ሁኔታ እንዲፈጠር ማድረጋቸውን አመላክቷል።

የድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን ይህንን ነፃ ጋዜጠኝነትን ለማፈን ማስፈራራት፣ ማጥፋት እና መግደልን በዘዴ ጥቅም ላይ የማዋልን ተግባር
የ “ሜክሲ-ካኒዜሽን” ጥቃት በማለት የሚገልጸው ሲሆን፥ በዚህ አካሄድ በአብዛኛው ሁኔታ ወንጀለኞች ሳይነኩ እንደሚቆዩ እና ወንጀለኞችን አለመቅጣት ለተጨማሪ ደም መፋሰስ እንደሚዳርግ አመላክቷል።

እነዚህ ከመካከለኛው ምስራቅ እስከ ላቲን አሜሪካ የሚገኙ የተለያዩ ክልሎችን አንድ የሚያደርጋቸው ነገር መረጃ የማግኘት መብት የሆነውን መሠረታዊ የሰብአዊ መብት በየጊዜው መሸርሸር እንደሆነ የገለጸው ሪፖርቱ፥ በጋዜጠኞች ላይ ጥቃት ሲሰነዘር ማህበረሰቦች ዓይናቸውን እና ጆሮዎቻቸውን እንደሚያጡ ገልጿል።

የድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን ሪፖርት በመጨረሻም በሀሰት መረጃ እና በጽንፈኝነት እየተቀረጸ ባለ ዓለም ውስጥ ነፃ የሆነ ዘገባ አለመስጠት ማህበረሰቦችን ለመጠቀሚያ እና ለፍርሀት ተጋላጭ እንደሚዳርግ የገለጸ ሲሆን፥ ይህ ሪፖርት ለእውነት ጥብቅና መቆም ሕይወትን ከመጠበቅ ጋር የማይነጣጠል መሆኑን ያስታውሰናል ተብሏል።

10 Dec 2025, 13:20