ፈልግ

ፓሱ የሚሰኘው በፓኪስታን የሚገኘው የበረዶ ግግር ፓሱ የሚሰኘው በፓኪስታን የሚገኘው የበረዶ ግግር  (AFP or licensors)

በዓለም አቀፍ የተራራ ቀን ረጅሙ የህይወት መስመሮቻችን የሆኑትን ተራሮች መጠበቅ እንደሚገባ ተነገረ

ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ የተራራ ጫፎች አንስቶ እስከ ተራራማ ቦታዎች ላይ የተሰሩ የኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት ድረስ የተራራማ አካባቢዎች ጥልቅ መንፈሳዊ እና ሥነ-ምህዳራዊ ጠቀሜታ ያላቸው ሲሆን፥ በአሁኑ ወቅት በፍጥነት የበረዶ ግግር መጥፋት እና የሙቀት መጨመር ፕላኔቷን ስጋት ላይ ጥሏል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ዓለም አቀፉ የተራራ ቀን ለፕላኔታችን አስፈላጊ የሆኑትን ነገር ግን በዓለም አቀፍ ውይይቶች ብዙ ጊዜ ችላ የተባሉ ክልሎችን በቅርበት እንድንመለከት የሚጋብዘን ሲሆን ይጋብዘናል። ተራሮች የአየር ንብረትን ይቆጣጠራሉ፣ ብዝሃ ህይወትን ይጠብቃሉ እንዲሁም ባህላዊ እና መንፈሳዊ ባህላቸው ከመሬታቸው ጋር በጥብቅ የተሳሰሩ ማህበረሰቦችን ይደግፋሉ። ተራሮች ወደ ሁለት ቢሊዮን ለሚጠጉ ሰዎች ንጹህ ውሃ በማቅረብ የዓለም የውሃ ማማዎች ናቸው።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥም ተራሮች ጠንካራ ምሳሌያዊ ትርጉም ያላቸው ሲሆን፥ ተራሮች በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ የተገለጹት እንደ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ብቻ ሳይሆን ሰማይና ምድር የሚገናኙባቸው ቅዱሳን ቦታዎች ናቸው።

በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ተራሮች የመገናኛ ቦታዎች ናቸው። በድነት ታሪክ ውስጥ ቁልፍ ጊዜዎችን ያመለክታሉ፤ እግዚአብሔር ለሙሴ በሲና ተራራ ላይ ትዕዛዛትን ሰጥቶታል፥ ኤልያስ እግዚያብሄርን “ጸጥ ባለ እና አነስተኛ ድምፅ” ሰምቶታል፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራ ላይ ክብሩን ገልጧል። እነዚህ ትዕይንቶች ፍጥረት ዳራ ሳይሆን እግዚአብሔር በሁሉም ቦታ የሚገኝበት ቦታ መሆኑን ያስታውሰናል።

ተራሮች እና ውሃዎቻቸው
ሆኖም ዛሬ፥ የዓለም ተራሮች እየጨመረ በሚሄድ ጫና ውስጥ ናቸው፥ 70 በመቶው የምድር ንጹህ ውሃ በረዶ ወይም ጉም ሆነው የሚገኙ ሲሆን፥ የበረዶ ግግር ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት እየቀለጠ ይገኛል። ካለፉት ስድስት ዓመታት ውስጥ በአምስቱ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የበረዶ ግግር እያፈገፈገ ይገኛል።

እ.አ.አ. ከ 2000 እስክ 2023 ባሉ ዓመታት ውስጥ ብቻ ዓለም 6,542 ቢሊዮን ቶን የበረዶ ግግር አጥታለች፣ የሙቀት መጠኑ እየጨመረ በመሄዱ ከዚህም በላይ ሊሆን እንደሚችል ይነገራል።

በተራራማ አከባቢዎች የሚኖሩ ማህበረሰቦች ላይ የሚያስከትለው መዘዝ ከባድ ነው። በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት በዚህ አከባቢ የሚኖሩ ህዝቦች አብዛኛውን ጊዜ ድሆች ሲሆኑ፥ ከእነዚህም ውስጥ ወደ ግማሽ የሚጠጉት ቀድሞውኑ የምግብ ዋስትና እጦት አጋጥሟቸዋል። በዚህ አከባቢ የሰብሎች የውሃ ዋስትና ከበረዶ እና ከበረዶ ግግር በሚመጣው የተረጋጋ የውሃ ፍሰት ላይ የተመሰረተ ነው። ግግር በረዶው የመቅለጥ ሁኔታው እየጨመረ ሲሄድ የጎርፍ አደጋ፣ የመሬት መንሸራተት እና የውሃ እጥረት ይጨምራል። ዛሬ በዓለም ዙሪያ ከ15 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከበረዶ ሐይቆች ከሚመጣው የጎርፍ አደጋ በጣም የተጋለጡ ናቸው።

የተራራ ባህላዊ እና መንፈሳዊ ቅርስ
የበረዶ ግግር መጥፋት የባህል እና የመንፈሳዊ ቅርስ መጥፋት ነው። በርካታ የአገሬው ተወላጆች እና የተራራማ ማህበረሰቦች የበረዶ ግግርን እንደ ቅዱስ ቦታዎች ያከብራሉ። የማንነት ምንጮች እና የባህላዊ ልማዶች መሰረት ናቸው። ዩኔስኮ እንደዘገበው 50 በሚሆኑ የዓለም ቅርስ ቦታዎች የሚገኙ 18,000 የበረዶ ግግሮች በየዓመቱ 58 ቢሊዮን ቶን እንደሚያጡ እና በጎረጎሳዊያኑ በ2050 ከእነዚህ የበረዶ ግግሮች አንድ ሶስተኛው ሊጠፋ እንደሚችል ግምቱን አስቀምጧል።

እነዚህ የበረዶ ግግሮች ሲጠፉ ለዘመናት በዙሪያቸው የኖሩ ባህሎች፣ እምነቶች እና ወጎችም አብረው ይጠፋሉ።

በእምነት፣ በባህል እና በተራሮች መካከል ያለውን ትስስር ለማሳየት እንደ ምሳሌ የሚጠቀሰው በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኘው ጥንታዊው የአቡነ የማታ ጉህ ቤተ ክርስቲያን ነው። ብዙ ጊዜ በዓለም ላይ ካሉት እጅግ በጣም የጥንት እና አንጋፋ አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዱ ተብሎ የሚገለፀው ይህ የአቡነ የማታ ጉህ ቤተ ክርስቲያን ከከባብያዊ ወለል 200 ሜትር በላይ ከተራራ ላይ የተፈለፈለ ቤተክርስቲያን ነው። ወደ ቤተክርስቲያኑ መውጫው መንገድ የእጅ እና የእግር ማስቀመጫዎችን በመወጣጣት ብቻ ነው። በውስጡ ከ15ኛው ክፍለ ዘመን የሚመነጩ ጉልህ ምስሎች ይገኛሉ።

ስጋት እየጨመረ ቢመጣም የተስፋ ምልክቶች እየታዩ ነው። በአለም ዙሪያ፣ ተራራ አከባቢ የሚኖሩ ማህበረሰቦች የግብርና ስነ-ምህዳሮችን እየተለማመዱ፣ የተራቆተ መሬትን ወደ ነበሩበት በመመለስ እና የበረዶ ግግርን ለመጠበቅ እና የተፈጥሮ አደጋዎችን የሚጠቁሙ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓቶችን ለማሻሻል በወጣቶች የሚመራ ተነሳሽነት እየፈጠሩ ነው። የተባበሩት መንግስታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት የሀገር በቀል ዕውቀትን ከሳይንስ ጋር ማጣመር ዘላቂ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲዎችን ለማዘጋጀት እና የውሃ ሀብቶችን ለመጠበቅ ወሳኝ መሆኑን አፅንዖት ሰጥቶ ገልጿል።

ዓለም አቀፍ ጥረቶች
የዓለምን የበረዶ ግግሮች ለመጠበቅ እና በእነሱ ላይ ጥገኛ የሆኑትን ማህበረሰቦች ለመደገፍ ዓለም አቀፍ እርምጃ ያስፈልጋል። የግሪንሀውስ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ፣ የውሃ ለውጥን ለመላመድ እና የመቋቋም አቅምን ለማጠናከር ፈጣን እና ጠንካራ ጥረቶችን ማድረግ አስፈላጊ ነው። የተራራማ ክልሎች ደህንነት ማጣት በግብርና፣ በብዝሃ ህይወት፣ በውሃ ሃይል፣ በባህላዊ ቅርስ እና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የዕለት ተዕለት ህይወት ላይ ተጽእኖ ያሳድራል። ለእነዚህ አከባቢዎች ጥበቃ ማድረግ የአካባቢ ጉዳይ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ ኃላፊነት ነው።

ይህ ዓለም አቀፍ የተራራ ቀን ተራሮች ከምናያቸው በላይ የበለጠ ነገር እንደሚጠቅሙ ያስታውሰናል። እኛን ይደግፉናል፥ ተራሮችን እና እነሱን የሚንከባከቡ ሰዎችን መጠበቅ የጋራ ቤታችንን የመጠበቅ የተልዕኳችን አስቸኳይ አካል ነው።

12 Dec 2025, 17:04