አሜሪካ የኢሚግሬሽን ማመልከቻዎችን መቀበል ማቆሟ ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የኢሚግሬሽን ማመልከቻዎቹ መታየት ከቆመባቸው መካከል ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ከፊል የጉዞ እገዳ ከተጣለባቸው ከ19 ሀገራት የሚመጡ ሰዎችን የሚመለከት ሲሆን፥ ይህም በኢሚግሬሽን ላይ ተጨማሪ ገደቦችን በማስቀመጥ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የፖለቲካ መድረክ ዋና ገፅታ መሆኑ ተነግሯል።
የዩናይትድ ስቴትስ የዜግነት እና የኢሚግሬሽን አገልግሎት ኃላፊ ጆሴፍ ኤድሎው እንዳሉት ፕሬዝዳንት ትራምፕ "አሳሳቢ ከሆኑ አገራት የመጡ ስደተኞች በሙሉ የእያንዳንዳቸው የመኖሪያ እና የሥራ ፈቃድ በጥብቅ እንደገና እንዲመረምር" መመሪያ መስጠታቸውን ገልጸዋል።
የትራምፕ አስተዳደር አገራቱን የዘረዘረበትን ምከንያትም ሲገልጽ የፀጥታ ችግሮች እንዲሁም የቢዝነስ፣ የተማሪ እና የቱሪስት ቪዛ ያላቸው ግለሰቦች ከተፈቀደላቸው ጊዜ በላይ በመቆየታቸው ምክንያት መሆኑን አስፍሯል።
የሃገራቱ ዝርዝር አፍጋኒስታን እና ሶማሊያን የሚያጠቃልል ሲሆን፥ አዲሱን ፖሊሲ የሚገልጸው ይፋዊ ማስታወሻ ላይ የብሔራዊ ደህንነት እና የሕዝብ ደህንነት ጉዳዮች ለውሳኔው ምክንያት ሆነው የተጠቀሱ ሲሆኑ በተለይም በቅርቡ በአፍጋናዊ ዜጋ የተገደለው የብሔራዊ ዘብ አባል ጉዳይ ውሳኔውን ማፋጠኑ ተገልጿል።
የትራምፕ አስተዳደር ባለፈው ሳምንት በዋሽንግተን ዲሲ ሁለት የብሔራዊ ዘብ አባላት ላይ ጥቃት ከተፈከፈተ በኋላ በስደተኞች ላይ የሚያደርገውን ዘመቻ ያጠናከረው ሲሆን፥ በአፍጋኒስታናዊ ጥቃት የተፈጸማባቸው የብሔራዊ ዘብ አባላት የ20 ዓመቷ ሳራ ቤክስትሮም እና የ24 ዓመቱ አንድሪው ዎልፍን ሲሆኑ፥ ሳራ ህይወቷ ሲያልፍ አንድሪው ደግሞ ከባድ ጉዳት ደርሶበት በህክምና ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።
“ይህ ጥቃት በአገራችን ላይ የተጋረጠውን ትልቁን የብሔራዊ ደኅንነት ስጋት አጉልቶ ያሳያል” ያሉት ፕሬዝዳንቱ፥ የባለፈው አስተዳደር 20 ሚሊዮን ያልታወቁ እና በሚገባ ምርመራ ያልተደረገባቸው የውጭ አገር ዜጎች ከመላው ዓለም እንዲገቡ ማድረጉን ገልጸው፥ “ማንኛውም አገር ለኅልውናው አደጋ የሆነውን ይህንን ዓይነት ስጋት አይታገስም” ብለዋል።
የአሜሪካው ፕረዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከቅርብ ቀናት በፊት ሶማሌያዊያን ስደተኞችን “ቆሻሻ” ብለው በመጥራት “በአገራችን ውስጥ አንፈልጋቸውም” በማለት ንግግር ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን፥ ትራምፕ ማክሰኞ ዕለት በተካሄደው የካቢኔ ስብሰባ ላይ “እውነቱን ለመናገር በአገራችን እንዲኖሩ አልፈልግም” ካሉ በኋላ "ወደ አገራችን ቆሻሻ ማስገባት ብንቀጥል አሜሪካ በተሳሳተ መንገድ ትሄዳለች" ብለዋል።
ባለፈው ወር የዩናይትድ ስቴትስ ብፁዓን ጳጳሳት “በአሜሪካ ውስጥ ባሉ ስደተኞች ላይ እየደረሰ ስላለው ነገር” ያላቸውን ስጋት በመግለጽ “ልዩ መልዕክት” ማስተላለፋቸው የሚታወቅ ሲሆን፥ ብፁዓን ጳጳሳቱ በመልዕክታቸው ሃገራት “ስደተኞችን ጨምሮ የሁሉንም ሰዎች መሠረታዊ ክብር እንዲገነዘቡ” እና በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በኢሚግሬሽን ሕጎች እና ሂደቶች ላይ “የትርጉም ማሻሻያ” እንዲደረጉ መጠየቃቸው ይታወቃል።
አሜሪካ ከዚህ በኋላ ወደ ሀገሯ አላስገባም ካለቻቸው ሀገራት መካከል መንግስት ረቡዕ ዕለት ባወጣው የሃገራት ዝርዝር ውስጥ አፍጋኒስታን፣ በርማ፣ ቻድ፣ ኮንጎ ሪፐብሊክ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ኤርትራ፣ ሄይቲ፣ ኢራን፣ ሊቢያ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን እና የመን የሚገኙበት ሲሆን፥ እነዚህ ሃገራት ሰኔ ወር ላይ በጣም ከባድ የኢሚግሬሽን እገዳዎች እንደተደረገባቸውም ይታወቃል።
በሰኔ ወር የወጣው አዋጅ አሜሪካን "ከውጭ አሸባሪዎች እና ከሌሎች የብሔራዊ እና የሕዝብ ደኅንነት ስጋቶች" ለመጠበቅ የውጭ አገር ዜጎች ወደ አገሪቱ እንዳይገቡ የሚከለክል ሲሆን፥ በዚሁ ወር ላይ ከፊል እገዳ ከተጣለባቸው 19 ሀገራት ዝርዝር ውስጥ የተካተቱት ብሩንዲ፣ ኩባ፣ ላኦስ፣ ሴራሊዮን፣ ቶጎ፣ ቱርክሜኒስታን እና ቬንዙዌላ ይገኙበታል።
በአዲሱ ፖሊሲ መሰረት በሂደት ላይ የሚገኙ ማመልከቻዎችም ጭምር መታየት እንዲያቆሙ እና በዝርዝሩ ውስጥ ከሚገኙ ሃገራት የመጡ ስደተኞች ጉዳይ በድጋሚ መታየት እንደሚጀምር የሚያዝ ሲሆን፥ ይህም የሚሆንበት ምክንያት ሁሉንም የብሄራዊ ደህንነት እና የህዝብ ደህንነት ስጋቶች ሙሉ በሙሉ ለመገምገም እንደሆነ ተገልጿል።