የዛይድ ሽልማት ዳኞች ሰብዓዊ ወንድማማችነት የሁሉም ሰው ተልዕኮ መሆኑን ገለጹ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ቀጣይነት ባለው ግጭት እና መከፋፈል በሰፈነበት ዓለማችን ውስጥ ሰብዓዊ ወንድማማችነት በጣም ሩቅ እና የማይቻል ቢመስልም፥ ሆኖም ግን በየዓመቱ የተወሰኑ የወንዶች እና የሴቶች ቡድን በተለያዩ ባህሎች፣ ሃይማኖቶች እና የአኗኗር ዘይቤዎች ውስጥ ተጨባጭ በሆነ ተግባር ሰላማዊ አብሮ መኖርን ለመፍጠር እየሰሩ ለሚገኙ ለአንድ ወይም ለብዙ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች የዛይድ ሽልማት ለሰብአዊ ወንድማማችነት ላይ የመሸለም ሃላፊነት እንደሚሰጣቸው ተገልጿል።
በዚህ ዓመት ለ 2026 የዛይድ ሽልማት ዙር ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በእጩነት የቀረቡ ሲሆን፥ ከ75 ሀገራት የተውጣጡ ከ350 በላይ አመልካቾች መቅረባቸው ተነግሯል።
ወንድማማችነት እና እውነታ ይስማማሉ?
ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ግጭቶች በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የበርካታ ሰዎችን የዕለት ተዕለት ኑሮ አስከፊ እያደረጉ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት፥ የዛይድ ሽልማት ተምሳሌታዊ ኃይል የመሆን እድልን ለማስታወስ ያገለግላል ተብሏል።
ከዳኞች ኮሚቴ አባላት አንዱ የሆኑት ቻርለስ ሚሼል ለቫቲካን ዜና እንደተናገሩት እነዚህ ዓለም አቀፋዊ ተግዳሮቶች ይህ ትውልድ ለሰብዓዊ ወንድማማችነት ሀላፊነት እንዳለበት የሚያሳዩበትን መንገድ አጉልቶ እንደሚያሳይ ገልጸው፥ የወደፊቱ ዓለም የተሻለ እና ፍትሃዊ እንዲሆን፣ በዓለም ዙሪያ ለሁሉም ሰው የሚሆን ተጨማሪ እድሎች እንዲኖሩ ውሳኔዎችን መወሰን እንደሚገባ የቀድሞው የቤልጂየም ጠቅላይ ሚኒስትር እና የቀድሞ የአውሮፓ ምክር ቤት ፕሬዚዳንቱ አፅንዖት ሰጥተው ገልጸዋል።
ይህንንም ለማሳካት ሁሉም ሰው በአንዳንድ የጋራ አስተሳሰብ መርሆዎች ማለትም ለወንድማማችነት፣ ለመቻቻል፣ ሰላማዊ ለሆነ አብሮ የመኖር ዘይቤ፣ ለመከባበር እና ለመስማማት የበለጠ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ማመን ያስፈልጋል ብለዋል።
ለሁሉም ሰው የሚሆን ተልዕኮ
ሌላኛዋ የኮሚሽኑ ዳኛ የሆኑት የዩኒሴፍ ዋና ዳይሬክተር ካትሪን ራስል በበኩላቸው የሰብዓዊ ወንድማማችነት በዛይድ ሽልማት ላይ ለተሳተፉት ብቻ እንዳልሆነ ገልጸው፥ ሁሉም ሰው በማህበረሰቡ ውስጥ ለውጥ ለማምጣት አንድ ነገር ማድረግ ይችላል ብለዋል።
ራስል የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ኤጀንሲ ሃላፊ እንደመሆናቸው መጠን የተሻለ ዓለምን ለመገንባት ለህፃናት ቅድሚያ መስጠት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ አሳስበው፥ ህፃናት ልጆች ብዙውን ጊዜ ሊቆጣጠሩት በማይችሉት ሁኔታዎች እንደሚጠመዱ እና መቼም ቢሆን መጥፎ ሁኔታን ፈጽሞ እንደማይፈጥሩ፥ ነገር ግን በቀጥታ የችግሮች ሰለባ እንደሚሆኑ አስረድተዋል።
አቶ ሚሼል በዩኒሴፍ ዋና ዳይሬክተር ንግግር ላይ አክለው እንደተናገሩት የእነዚህን ህፃናት የወደፊት ህይወት ለመጠበቅ እና ለመንከባከብ የሚረዳው ብቸኛው መንገድ እርስ በርስ የተሻለ ሰብዓዊ ትስስርን መፍጠር እንደሆነ ጠቁመው፥ ‘በወንድማማችነት፣ በመቻቻል እና በመከባበር መንፈስ የተቃኙትን እነዚህን ሁሉ በዓለም ዙሪያ ያሉ ውጥኖችን ስንመለከት ሁላችንም ተጠያቂዎች መሆናችንን ያሳያል’ ብለዋል።
ሁለቱ ዳኞች የዛይድ ሽልማት የአድልዎ፣ የመከፋፈል እና የአመጽ እንቅፋቶችን በማፍረስ በምትኩ ነፃ የሆነ፣ የፍቅር እና የወንድማማችነት መንገዶችን ለማሳየት በተዘጋጀው ዓለም አቀፍ ቡድን ውስጥ እንዲካፈሉ የሚጋብዝ መሆኑን ደጋግመው ተናግረዋል።
አንዳንድ ሰዎች ግዙፍ ድርጅቶችን እንደሚመሩ፣ አስደናቂ ሥራዎችን እንደሚሠሩ፣ አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች እና በጦርነት ቀጣናዎችም ጭምር እንደሚሰሩ የገለጹት ወይዘሮ ራስል፥ ሆኖም ግን ማንኛውም ሰው የሆነ ነገር ማድረግ እንደሚችል አመላክተዋል።
የተስፋ እና የወንድማማችነት ምሳሌዎች
የለውጥ ፍላጎት ግን ከቃላት በላይ እንደሚጠይቅ የጠቆሙት አቶ ሚሼል በበኩላቸው፥ የዛይድ ሽልማት ተጨባጭ ፕሮጀክቶችን እና ድርጊቶችን ለመደገፍ ቁርጠኝነቱ እንዳለው በማመልከት፥ ተቋሙ ከዚህ የበለጠ እንደሚሰራ ተስፋ እናደርጋለን ብለዋል።
በተመሳሳይ ጊዜ ወይዘሮ ራስል ሽልማቱ ተጨባጭ እርምጃዎችን ለሚወስዱ ተነሳሽነቶች “የተለያዩ ሃይማኖት እና እምነት ያላቸውን ሰዎች በሚያሳትፍ መንገድ” እንደሚሸልም ጠቁመዋል።
አቶ ሚሼል የዚህ ሽልማት ውበት ይህ መሆኑን ገልጸው፥ ምክንያቱም በብዙ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ አመለካከቶች ቢኖሩንም፥ በመሠረታዊ ተግዳሮቶች ላይ ግን እንስማማለን ካሉ በኋላ፥ በዓለም አቀፍ ደረጃ የጋራ እሴቶች እና መርሆዎች ቢኖሩን ኖሮ የበለጠ ሰላም፣ መረጋጋት እና መጪው ጊዜ የበለጠ አወንታዊ እድሎች እንዲኖሩት ማድረግ ይቻል ነበር ብለዋል።
ወይዘሮ ራስል እና አቶ ሚሼል ሐሙስ ጥዋት ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፣ እንዲሁም ከቀናት በፊት ደግሞ ከአል-አዝሃር ታላቁ ኢማም ጋር ከተገናኙ በኋላ፣ ከሌሎች ዳኞች ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን በእጩነት የቀረቡትን የመጨረሻ እጩዎችን የመለየት እና የክብር ተሸላሚዎችን የመምረጥ ሥራዎችን የጀመሩ ሲሆን፥ በዚህም መጪው ጥር ወር ላይ የሚገለጸውን እና አሁን ባለንበት ዓለም የሰብዓዊ ወንድማማችነት ተምሳሌት የሆኑትን የክብር ተሸላሚዎች ይመርጣሉ ተብሏል።