ፈልግ

በስፔን ውስጥ የተመረተ ወታደራዊ መኪና በስፔን ውስጥ የተመረተ ወታደራዊ መኪና   (ANSA)

ጂኦፖለቲካዊ ውጥረቶች ተጠናክረው በቀጠሉበት በአሁኑ ወቅ በዓለም አቀፍ ደረጃ የመከላከያ በጀት እየጨመረ መምጣቱ ተነገረ

የዓለም አቀፍ የስትራቴጂ ጥናት ኢንስቲትዩት እንደገለጸው ተጠናክሮ በቀጠለው ጂኦፖለቲካዊ ውጥረቶች ውስጥ ዓለም አቀፋዊ ወታደራዊ ወጪዎች እየጨመሩ መምጣታቸው ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የዓለም አቀፍ የስትራቴጂ ጥናት ኢንስቲትዩት (IISS) ይፋ ባደረገው የአውሮፓዊያኑ የ 2026 ዓመታዊ የወታደራዊ ወጪዎች ልኬት ሪፖርት እንደሚያሳየው ሃገራት ለመከላከያ የሚያወጡት ወጪ እየጨመረ ያለበት ፍጥነት ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን የገለጸ ሲሆን፥ አውሮፓ እና አንዳንድ የኢስያ ክፍሎች ቀጣይነት ያለው የደህንነት ስጋቶችን በመጥቀስ እና ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ነገሮችን በመተው ከፍተኛ ወታደራዊ ጭማሪ ማስመዝገባቸው በሪፖርቱ ተገልጿል።

እ.አ.አ. ከ2025 ዓ.ም. ወዲህ የዓለም ወታደራዊ ወጪ ወደ ላይ እያሻቀበ መምጣቱን ያመላከተው የተቋሙ ሪፖርት፥ በተጠቀሰው ዓመት ወታደራዊ ወጪው በግምት 2.63 ትሪሊዮን ዶላር መድረሱን አመልክቷል። ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ2.5 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን እና ምንም እንኳን የእድገቱ ፍጥነት ሩሲያ በዩክሬን ላይ ከፈጸመችው ወረራ በኋላ ከታየው ከፍተኛ እድገት ጋር ሲነፃፀር ዘገምተኛ መሆኑ ተገልጿል።

ሪፖርቱ በክልሎች መካከል ያለውን ልዩነት አጉልቶ የሚያሳይ ሲሆን፥ መንግስታት ለጸጥታ ስጋቶች ምላሽ እየሰጡ በሚገኙበት እና የኔቶ አጋሮች ወታደሮቻቸውን ለማጠናከር ቃል እየገቡ በሚገኙበት በአሁኑ ወቅት የአውሮፓ የመከላከያ ወጪ ከዓለም አቀፉ አማካይ ወታደራዊ ወጪዎች በእጅጉ በመብለጥ በ 12.6 በመቶ ገደማ የጨመረ ሲሆን፥ እ.አ.አ. በ 2025 ለዓለም አቀፍ የመከላከያ ወጪ ከ 21 በመቶ በላይ ለሆነው ለአውሮፓ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ በዚህ ጭማሪ ውስጥ ጀርመን ግንባር ቀደም ሚና ተጫውታለች ተብሏል።

በአንጻሩ የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ በጀት እድገት ለጊዜው በ 2025 ዓ.ም. ከነበረበት መጠነኛ ቅናሽ የታየበት ሲሆን፥ ምንም እንኳን አሁን ባለው አስተዳደር ስር ያሉ ውጥኖች ‘ጎልደን ዶም’ የተሰኘውን የሚሳየል መከላከያ ፕሮግራሞችን የመሳሰሉ ተነሳሽነቶችን በመጥቀስ የአሜሪካ ወታደራዊ ወጪን በ2026 ከ1 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ከፍ ለማድረግ እቅድ ያለው ቢሆንም እድገቱ ጉልህ እንዳልሆነ ተገልጿል።

የሩስያ የመከላከያ ወጪ በበኩሉ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሄዱን የጠቀሰው ሪፖርቱ፥ ነገር ግን ከቀደሙት ዓመታት ጋር ሲነፃጸር በጣም ቀርፋፋ በሆነ ፍጥነት ከዩክሬን ጋር በተፈጠረ ግጭት ምክንያት ቀደም ብሎ ከፍተኛ ጭማሪ ካሳየ በኋላ ጉልህ የሆነ ለውጥ መታየቱን ጠቅሷል።

ቻይና እ.አ.አ. በ 2025 ከክልሉ ወታደራዊ ወጪ ወደ 44 በመቶ የሚጠጋ ከፍተኛውን ድርሻ በመያዝ በመላው ኢስያም የመከላከያ በጀቶች በአንፃሩ ጭማሪ ማሳየታቸው የተገለጸ ሲሆን፥ ሌሎች በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ሃገራት በደህንነት ፉክክር ውስጥ የራሳቸውን የመከላከያ ወጪ ከፍ ማድረጋቸው ተጠቁሟል።
በመካከለኛው ምስራቅ እና በሰሜን አፍሪካ አካባቢ የሚደረጉ ወታደራዊ ወጪዎችም መጨመራቸውን እና ይህም በአከባቢው የሚታዩ ቀጣይነት ያላቸው ክልላዊ ውጥረቶችን እና ወታደራዊ ዝግጁነትን ለማጠናከር የመንግስት ውሳኔዎችን የሚያመለክቱ ናቸው ተብሏል።

ር.ሊ. ጳጳሳት ሊዮ ወታደራዊ ወጪዎች ገደብ እንዲኖራቸው ያደረጉት ጥሪ
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የጤና ስርዓቶችን ለማጠናከር ጥቅም ላይ መዋል የነበረባቸው በጀቶች ወደ ወታደራዊ በጀቶች መዞራቸውን በመጥቀስ በወታደራዊ ግጭቶች ውስጥ የሚደረጉ ከፍተኛ በጀቶችን በመቃወም ጥሪ ማድረጋቸው ይታወሳል።

የካቲት ወር መጀመሪያ ላይ ለጳጳሳዊ የሕይወት ጉዳዮች ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ንግግር ያደረጉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ኢኮኖሚን የሚያደቁ፣ ብሎም የቴክኖሎጂ እና የሎጂስቲክ አቅሞችን የሚያዳክሙ ጦርነቶች ላይ ከማተኮር ይልቅ ሕይወትን ለመጠበቅ እና የሕክምና እንክብካቤን ለማረጋገጥ በሚደረጉ ጥረቶች ላይ ማተኮር አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው፥ ግጭቶች ሆስፒታሎችን ጨምሮ በሲቪል መዋቅሮች ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ እና በሕዝብ ጤና ላይ ቀጥተኛ ጉዳት እንደሚያደርሱ ገልጸዋል።

ሽምግልናን የሚያበረታቱ እና ውጥረቶችን መከላከል የሚችሉ የባለብዙ ወገን ስልቶች እንደገና እንዲጀመሩ ጥሪ ያቀረቡት ብፁዕነታቸው፥ የጤና አገልግሎት ተደራሽነቱ ሊገደብ የማይችል ሁለንተናዊ መብት እንደሆነ አሳስበዋል።

27 Feb 2026, 13:28