ማዳጋስካር ‘ጊዛኒ’ በተሰኘ አውሎ ንፋስ መመታቷ ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በአምስቱ የማዳጋስካር ክልሎች በደረሰው አደጋ ከደርዘን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ከመሞታቸውም በተጨማሪ በርካታ ሰዎች ቆስለው ከከተማዋ እንዲወጡ የተደረጉ ሲሆን፣ 400 ሺህ ያህል ሕዝብ ከሚኖርባት ቶማሲና ከተማ 90 በመቶ የሚሆኑ ቤቶች ጣሪያቸው በነፋሱ መወሰዱ ተነግሯል።
ጊዛኒ የሚል ስያሜ የተሰጠው ከባድ አውሎ ነፋስ ያደረሰውን አደጋ ተከትሎ የቤተክርስቲያን መሪዎች እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ለሃገሪቷ አስቸኳይ እርዳታ እንዲደረግ ተማጽነዋል።
ይህ አውሎ ንፋስ በማዳጋስካር አምስት ክልሎች ውስጥ የሚገኙ 25 ወረዳዎችን ካወደመ በኋላ በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸው፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ መፈናቀላቸው እንዲሁም መሰረተ ልማቶች ክፉኛ መጎዳታቸው ተገልጿል።
ግምገማዎች እና የአደጋ ጊዜ ምላሾች ተጠናክረው በቀጠሉበት በአሁኑ ወቅት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የተለያዩ ድጋፎች እንዲደረጉ ጥሪያቸውን ማሰማት ቀጥለዋል።
የቫቲካን የዜና ወኪል የሆነው ፊደስ ኒውስ የካቲት 9 ባወጣው ጊዜያዊ ዘገባ ብሔራዊ የአደጋ እና የአደጋ ስጋት አስተዳደር ቢሮ (BNGRC) እንደገለጸው የአደጋ ጊዜ ቡድኖች በህንድ ውቅያኖስ ደሴት ላይ በምትገኘው ማዳጋስካር ውስጥ በሚገኙ አምስት ክልሎች ጊዛኒ የሚል ስያሜ የተሰጠው ከባድ አውሎ ነፋስ ያደረሰውን ጉዳት እየገመገሙ እንደሆነ ገልጿል።
ጉዳቶች እና ጥሪዎች
ሁለት የግል ሆስፒታሎች እና ሰባት የመንግስት ሆስፒታሎችን ጨምሮ ወደ 49,000 የሚጠጉ ሕንፃዎች መጎዳታቸው የተነገረ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ እስካሁን ድረስ 59 ሰዎች መሞታቸው፥ 15 ሰዎች እንደጠፉ እና 804 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸው ተነግሯል።
የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል እና ቀይ ጨረቃ ማህበራት ፌዴሬሽን በበኩሉ 16,428 ሰዎች ወይም 4,045 ቤተሰቦች መፈናቀላቸውን ይፋ አድርጓል።
የቤተክርስቲያን እና የዓለም አቀፍ ህብረት ጥረት
የማዳጋስካር ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ የካቲት 4 ባወጣው መግለጫ በደረሰው ውድመት ምላሽ በመስጠት በአውሎ ንፋስ አደጋው ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፥ በብፁዕ አቡነ ዣን ክላውድ ራኮቶአሪሶአ የተፈረመበት ይህ ደብዳቤ የካቶሊክ ምእመናን በተለይም በምስራቅ ማዳጋስካር የቶማሲና ሀገረ ስብከት ውስጥ የሚገኙ በአደጋው የተጎዱ ማኅበረሰቦችን እንዲረዱ ጥሪ አቅርቧል።
የሀገረ ስብከቱ መሪዎች የእርዳታ ሥራን የማስተባበር ኃላፊነት በብፁዓን ጳጳሳቱ የተሰጣቸው ሲሆን፥ ምእመናን ለዕርዳታ የሚሰጠውን መመሪያ እንዲከተሉ አሳስበዋል።
እሑድ የካቲት 8 ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ባደረሱት የመልአከ እግዚያብሔር ጸሎት ወቅት ለተጎዱት ሰዎች ያላቸውን ቅርበት ገልጸው ለተጎጂዎች ጸሎት ማቅረባቸው ይታወሳል።
አደጋዎች
ማዳጋስካር ቀድሞውንም በየካቲት ወር መጀመሪያ ላይ በሌላ ሞቃታማ አውሎ ንፋስ ክፉኛ መመታቷ የሚታወስ ሲሆን፥ ይህ አውሎ ንፋስ የሞት አደጋ እና ለበርካታ ሰዎች መፈናቀል ምክንያት መሆኑ ይታወቃል።
በሌላ ዜና የሞዛምቢክ ፕሬዚዳንት ዳንኤል ቻፖ፣ በአዲስ አበባ በተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ የመንግስት የደህንነት መመሪያዎችን በማክበራቸው ምክንያት የተጎጂዎች ቁጥር አነስተኛ መሆኑን መግለፃቸው ይታወሳል።
የግዛቱ ገዥ ፍራንሲስኮ ፓጉላም የመሠረተ ልማት ውድመት እንደደረሰ በመግለጽ የአደጋን ተፅእኖ ለመቀነስ የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ከአከባቢው ለቆ የመውጣት አስፈላጊነት ላይ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ደቡብ ምስራቅ አፍሪካ ከጥቅምት እስከ ሚያዚያ የሚቆይ ዓመታዊ ሞቃታማ ወቅት እንደሚያሳልፍ የሚታወቅ ሲሆን፥ በዚህም ወቅት በየዓመቱ ከፍተኛ ቁሳዊ ውድመት እና የህይወት መጥፋት እንደሚከሰት መረጃዎች ያሳያሉ።
ሰሞኑን የተከሰተው አውሎ ንፋስ የክልሉን ተጋላጭነት እና የቅድመ ዝግጅትን አስፈላጊነት፣ የተቀናጀ ምላሽ እና ዘላቂ የሆነ ዓለም አቀፍ ትብብርን የሚያሳይ ሌላ ትልቅ ማስታወሻ ሆኖ ያገለግላል ተብሏል።