ፈልግ

ሞዛምቢካዊያን ሴቶች የሁሉም ሰው መብት እንዲከበር እና እንዲጠበቅ ትክክለኛ እርምጃ እንዲወሰድ መጠየቃቸው ተነገረ ሞዛምቢካዊያን ሴቶች የሁሉም ሰው መብት እንዲከበር እና እንዲጠበቅ ትክክለኛ እርምጃ እንዲወሰድ መጠየቃቸው ተነገረ   (Marvellous Durowaiye)

ሞዛምቢካዊያን ሴቶች የሁሉም ሰው መብት እንዲከበር እና እንዲጠበቅ ትክክለኛ እርምጃ እንዲወሰድ መጠየቃቸው ተነገረ

በሞዛምቢክ ውስጥ የጤና አጠባበቅ ስርዓቱ እና ሌሎች እጅግ አስፈላጊ አገልግሎቶች መውደማቸውን ተከትሎ፥ በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የሴቶች ቡድን በዚህ ዓመት ለሚከበረው የሴቶች ቀን ባህላዊ ልብሶችን ለማሰራጨት የነበረውን ዕቅድ በመሰረዝ በምትኩ የወደሙ የጤና አጠባበቅ ሥርዓቶች በአስቸኳይ እንዲጠገኑ ጥሪ ማቅረቡ ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

መጋቢት 29 ቀን 2018 ዓ.ም. የሚከበረውን የዚህ ዓመት የሴቶች ቀንን ለማክበር ሞዛምቢክ በጉጉት እየተጠባበቀች መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ እንደ አንድ የክብረ በዓሉ አካል በሞዛምቢክ የሚገኘው የሴቶች ቡድን በጤና አጠባበቅ እና በዕለት ተዕለት ሕልውና ላይ የሚደርሰውን ቀውስ በማንሳት ድምፃቸውን እያሰሙ መሆኑ ተነግሯል።

የሴቶች ንቅናቄ ቡድኑ ለፕሬዝዳንት ዳንኤል ፍራንቺስኮ ቻፖ ባለቤት ለሆኑት ለቀዳማዊት እመቤት ጉዌታ ሴሌማኔ ቻፖ በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ ሴቶቹ የሞዛምቢካዊያን የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ በአገር አቀፍ ደረጃ በቀለማት ያሸበረቁ፣ በሃገሬው ነዋሪዎች ዘንድ ‘ካፑላና’ ተብሎ የሚታወቀው ባህላዊ አልባሳት እንደሚከፋፈሉ የሚገልጹ ዘገባዎች በመውጣታቸው የተሰማቸውን ቅሬታ መግለፃቸው ተነግሯል።

የቫቲካን የዜና ወኪል የሆነው ፊደስ ኒውስ እንደዘገበው ሴቶቹ ለሞዛምቢክ እናቶች፣ ሴት ልጆች፣ እህቶች እና አያቶች ጥብቅና እንደቆሙ የሚናገሩ ሲሆን፥ ሴቶቹ “እኛ የምንፈልገው ካፑላና ሳይሆን፥ የሁሉም ሴቶች መብት መከበር እና መጠበቅ ነው” ሲሉ ገልጸው፥ ተምሳሌታዊ ምልክቶችን እንደሚያከብሩ፣ ነገር ግን ሞዛምቢካውያን ትኩረት የሚሹ ትክክለኛ እና አስቸኳይ ስቃይን በተጋፈጡበት በዚህ ወቅት ይሄ እንደማያስፈልጋቸው ገልጸዋል።

የጤና እንክብካቤ
ሴቶቹ በሕዝብ ሆስፒታሎች ውስጥ ያለውን ከፍተኛ ፍላጎት እና አስቸኳይ ሁኔታ አጉልተው በማሳየት፥ በቂ የህክምና መሳሪያ ባለመኖሩ በርካታ ህፃናት እየሞቱ እንደሆነ ጠቅሰው፥ ነፍሰ ጡር እናቶች ያለ ፍራሽ እና አስፈላጊ መድሃኒት በባዶ አልጋ ላይ በምጥ እየተሰቃዩ እንደሚገኝ፣ ቤተሰቦች መሰረታዊ አገልግሎቶች እንደማያገኙ ገልጸው፥ በዓሉ ይህ ችግር ባለበት ወቅት መከበሩ ትርጉም እንደሌለው አስረድተዋል።

“በቂ ሆስፒታሎች በሌሉበት እና የህዝብ ሀብት ብክነትን በሚታይበት በዚህ ወቅት ቀኑን ማክበር አንችልም” ያሉት ሴቶቹ፥ ከዚህ ይልቅ በሃገሪቷ ኢፍትሃዊነት እና ጥቃት እንደነገሰ ገልጸው፥ አስቸኳይ እርምጃዎችን እና እውነተኛ መፍትሄዎችን እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

ገንዘቦቹን ለህይወት አድን ተግባራት ማዞር
የሴቶች ቡድኑ ካፑላናስን ለመግዛት የተመደበውን ገንዘብ ወደ ትክክለኛ የህዝቡ ፍላጎቶች በማዞር፥ በገንዘቡ በሆስፒታሎች ውስጥ መድኃኒት እንዲገዛበት፣ ትክክለኛ አልጋ እንዲቀርብ፣ የምግብ አቅርቦት እንዲኖር እንዲሁም የሴቶች፣ የሕፃናት እና የቤተሰብ ክብር እንዲጠበቅበት ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፥ “የካፑላናስ ተነሳሽነት የሚያጋጥሙንን እውነተኛ ችግሮች አይፈታም” ያሉት ሴቶቹ፥ የህይወት ሚዛኑ በተዛባበት በአሁኑ ወቅት ባህላዊ ልብሶቹን ማሰራጨት ሀብትን አላግባብ መጠቀም እንደሆነ ገልጸዋል።

26 Feb 2026, 12:12