ፈልግ

ከጋምቢያ የተነሳ አንድ ስደተኛ ከሳምንት በኋላ በስፔን በሚገኘው ላስ ፓልማስ የባህር ዳርቻ ላይ በእግሩ ሲጓዝ ከጋምቢያ የተነሳ አንድ ስደተኛ ከሳምንት በኋላ በስፔን በሚገኘው ላስ ፓልማስ የባህር ዳርቻ ላይ በእግሩ ሲጓዝ   (AFP or licensors)

በስፔን ውስጥ የሚገኙ ስደተኞችን ህጋዊ የማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩ ተነገረ

የስፔን መንግስት በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰነድ አልባ ስደተኞች ህጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ ለመስጠት በቅርቡ ያደረገውን ውሳኔ አስመልክቶ በኢየሱሳዊያን የስደተኞች አገልግሎት ውስጥ የዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ አማካሪ የሆኑት አማያ ቫልካርሴል ከቫቲካን ዜና ጋር በነበራቸው ቆይታ ገለፃ አድርገዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ባለፈው ወር የስፔን ካቢኔ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰነድ አልባ ስደተኞች ህጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ የሚያሰጥ አዋጅ ማጽደቁ የሚታወቅ ሲሆን፥ ስደተኞችን ወደ ሃገራቸው መመለስ እና ማሰር በተለመደበት በአሁኑ ወቅት በስደት ላይ የሚደረጉ ውይይቶች የሚበረታቱ መሆኑ ተገልጿል።

በስፔን ውስጥ መደበኛ ያልሆኑ ስደተኞች “ለዓመታት በጥላ ውስጥ ኖረዋል” ያሉት በኢየሱሳዊያን ማህበር የስደተኞች አገልግሎት ውስጥ ዓለም አቀፍ የጥብቅና አማካሪ የሆኑት አማያ፥ ከ500,000 እስከ አንድ ሚሊዮን ለሚገመቱት ተጎጂዎች ይህ ሰነድ አልባ ስደተኞችን ህጋዊ ማድረግ ማለት “ለሕልውናቸው እውቅና መስጠት” እና “የህጋዊ ደኅንነት እርምጃ” ማለት እንደሆነ አስረድተዋል።

አማያ ከቫቲካን ኒውስ ጋር በኢሜል ባደረጉት ቆይታ መደበኛ ያልሆኑ ስደተኞች በስፔን እንደ ግብርና፣ መስተንግዶ፣ ግንባታ እና የቤት ውስጥ ሥራ ባሉ ዘርፎች ውስጥ “የማይተካ ሚና” እየተጫወቱ እንደሚገኝ ገልጸው፥ ሆኖም ግን መደበኛ የሥራ ስምምነቶችን ወይም የደህንነት ጥበቃዎችን ሳያገኙ “በዘላቂ ስጋት” ውስጥ እንደሚኖሩ ጠቁመዋል።

የኢኮኖሚ ሳይሆን የሞራል ጉዳይ መሆኑ
ብዙውን ጊዜ ስደትን የሚደግፉ ሃሳቦች ከኤኮኖሚያዊ አንፃር የሚቀርቡ ሲሆን፥ የምዕራባውያን አገሮች ስደተኞች ለሠራተኛ ኃይል አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ በማንሳት እንደሚከራከሩ ይገለፃል።

በዚህ ወር መጀመሪያ በኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ላይ ቀርቦ ብዙ ውይይት የተደረገበት መጣጥፍ የስፔኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ ያቀረቡት ጽሁፍ ሲሆን፥ ሳንቼዝ እነዚህ ስደተኞች ቀድሞውንም የስፔን ማህበረሰብ አካል እደሆኑ እና በዚህ መልኩ ሊታዩ እንደሚገባ አስረድተው፥ ስደተኞቹን ህጋዊ የማድረግ ‘የመጀመሪያው እና በጣም አስፈላጊው’ ምክንያት ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ሞራላዊ ጉዳይ ነው’ ሲሉ አጥብቀው የገለጹት ሃሳብ መሆኑ ተገልጿል።

ሳንቼዝ በጽሁፋቸው “ስደተኞቹ በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት በፓርኮች ውስጥ ጉዞ እንደሚያደርጉ፣ ወደተለያዩ ምግብ ቤቶች እንደሚሄዱ እና በአካባቢው አማተር የእግር ኳስ ቡድን ውስጥ እንደሚጫወቱ” ጠቁመዋል።

ቫልካርሴል በበኩላቸው ይህ ሃሳብ “ስደተኞች የኢኮኖሚው ጠቃሚ ግብአቶች እንደሆኑ ብቻ ተደርገው ሊታዩ አይገባም” ከሚለው የካቶሊክ ማህበራዊ አስተምህሮ ጋር ያለውን አስፈላጊ ቁርኝት አጉልተው በማሳየት፥ ከእንደዚህ አይነት “የአገልግሎት ሰጪ” አቀራረቦችን በመቃወም፣ ቤተክርስቲያን “እያንዳንዱ ሰው በራሱ የተሟላ” እንደሆነ እና “የማይጣስ ክብር” ባለቤት እንጂ “የአጭር ጊዜ ፍላጎቶችን የሚያገለግል መሳሪያ” እንዳልሆነ ታስታውሰናለች ብለዋል።

ቀጣይ እርምጃዎች
ቫልካርሴል በማከልም ስደተኞችን ህጋዊ የማድረግ አካሄድ ብቻውን “የመጨረሻ መፍትሄ እንዳልሆነ” ጠቁመው፥ መጀመሪያ ላይ ለአንድ ዓመት ብቻ እንዲቆይ ተወስኖ እንደነበር፥ ይህ ደግሞ በተፈጥሮው በኋላ ላይ ስለሚመጣው ነገር ጥርጣሬን እንደሚፈጥር ገልጸው፥ ይህ ውሳኔ ጥልቅ መዋቅራዊ ማሻሻያዎችን አያስወግድም ብለዋል።

አስፈላጊ ከሆኑ ለውጦች መካከል የረጅም ጊዜ የውህደት ፖሊሲዎችን ማውጣት፣ ጠንካራ የሰው ኃይል ጥበቃዎችን ማድረግ እና ለህጋዊ ፍልሰት ግልጽ የሆኑ መንገዶች ሊኖሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

“ሲኖዶሳዊ የህዝብ ተሳትፎ”
ቫልካርሴል በመጨረሻም ከመለኪያው በስተጀርባ ያሉትን የውሳኔ አሰጣጥ ሂደቱን በማስታወስ፥ ስደተኞችን ህጋዊ የማድረግ ሂደቱ ከ700,000 በላይ ፊርማዎችን በማሰባሰብ እና የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን ጨምሮ ከ900 በላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ድጋፍ በማሰባሰብ እንደተጀመረ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳንቼዝ በኒው ዮርክ ታይምስ ላይ ባቀረቡት መጣጥፍ ላይ መግለጻቸውን ጠቁመዋል።

ከ17,000 በላይ በጎ ፈቃደኞች የእያንዳንዱን ሰው በር ማንኳኳታቸውን፥ ከዚህም በተጨማሪ ዩኒቨርሲቲዎችን፣ የማህበረሰብ ማዕከላትን እና አብያተ ክርስቲያናትን መጎብኘታቸውን፥ በጉዳዩ ዙሪያ ውይይቶችን ማስጀመራቸውን እና በፓርላማ ውስጥ ውይይት እንዲደረግበት አስፈላጊ የሆኑ ፊርማዎችን ማሰባሰባቸው ተገልጿል።

ቫልካርሴል በመጨረሻም ሂደቱ ከመላው የስፔን ማህበረሰብ የተውጣጡ ግለሰቦችን እና ድርጅቶችን በማሰባሰብ በቤተክርስቲያን ቋንቋ አገላለጽ “ሲኖዶሳዊ የህዝብ ተሳትፎ” የተደረገበት እና “ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ” ቅስቀሳ መደረጉን ገልጸዋል።

20 Feb 2026, 12:45